በዓለማችን ኃያላን ሀገራት መካከል የኑክሌር የጦር መሳሪያዎች ፉክክር የተጀመረው በጀርመን እና በሕብረ ብሔሩ ጥምር ኃይሎች መካከል ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ነበር። በዚህ የግጭት አንድምታ ነው በ1930 ዓ.ም ጀርመን ውስጥ በሚገኘው ኬይዘር ዊሊያም ተቋም ውስጥ ኦቶማን ሆን እና ዶር ፈሪትዝ ሰቲርስማን የተባሉ ሳይንቲስቶች የአተምን ቅንጣት በተሳካ ሁኔታ መነጠል የቻሉት። ጥቂት ቆይቶ ሊሴ ሜይትነር እና ኦቶ ሃን የአተም ቅንጣትን የመፈርከስ የተሳካ ስራ ወደ ኒኩሌር ማብላላት ደረጃ ማደጉን ይፋ አደረጉ።
የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ በዚህ የታሪክ መታጠፊያ ላይ፣ በአቶሚክ ጉዳይ ላይ የሚሰሩት ለታላላቅ አእምሮዎች አይሁድ እና ጀርመኖች ነበሩ።
በወቅቱ የጀርመኑ መሪ የሂትለር ፀረ ሴማዊነት አመለካከት ጀርመን ውስጥ የነበሩትን እነዚህን ብሩህ አእምሮዎች ገፍቶ ወርቅ አንጥፋ ወደ ተቀበለቻቸው አሜሪካ እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል። እነዚህ ተሳዳጅ ሳይንቲስቶች ስለጉዳዩ አውሮፓን በዓይነ ቁራኛ ይከታተል ለነበረው የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋም አሳወቁት። የዚህ እውቀት ባለቤት በመሆኗ ጀርመን የኒኩሌር ቦምብ በመስራት የመጀመሪያዋ ሀገር ትሆናለች የሚል ፍራቻ በመላው ዓለም ነግሶ ነበር። አልበርት አንስታይንም ከእነዚህ ስደተኞች አንዱ ነበርና የዚህን ግኝት ሚና ሙሉ በሙሉ ያውቅ ነበር:: ምክንያቱም የአቶምን ቅንጣት ያለውን ሚስጢራዊ አቅም ለዘመናዊው ዓለም የገለጠ የመጀመሪያው ሰው እርሱ ነበርና። እናም እርሱ ነበር ለወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጉዳዩን ያሳወቀው። አሜሪካ ከጀርመን ቀድማ ቦምቡን መስራት እንዳለባት በፅኑ አሳስቦ እንደነበር ታሪክ ያወሳል።
በወቅቱ ፕሬዚደንት ሩዝቬልት የሚመሩት ዓለማቀፋዊ አንድምታውን በተሟላ ሁኔታ ተገንዝበውት ነበርና ቦምቡን በቀዳሚነት ለመገንባት ሽቅድድሙን ጀመሩት። ሩዝቬልት በማንሃተን ደሴት ውስጥ በከፍተኛ ሚስጥር ቦምቡን እንዲገነባ ትእዛዝ ሰጡ። በሜጀር ጄኔራል ሌስሊ ግሩቭስ የሚመራ በሁለት ቢሊዮን ዶላር ታይቶ የማይታወቅ ሳይንሳዊ ምርምር ‘የማንሃታን ፕሮጀክት’ን ቦምቡን የመገንባት ስራውን በከፍተኛ ሚስጥር እንዲያከናውን ሀላፊነት ሰጡ። ሮበርት ኦፕንሄመር፣ ኤንሪኬ ፈርሚ፣ ኸርበርት ዮርክ፣ ኤድዋርድ ቴለር ሃንስ ቤዝ እና ሌሎች በርካታ የሳይንስ ሊቆች በመጀመሪያዎቹ ሦስት ኒኩሊየር ቦምቦች ግምባታ ስራ ላይ እንዲሳተፉ ተደረገ።
ቀልብን ከሚገዛው ከዚህ ቦምብ ግንባታ ጎን ምንም እንኳን ቦምቡ የተሰራላት የመጀመሪያዋ ጠላት ጀርመን ብትሆንም ቀስ በቀስ ወደ ሶቭየት ኅብረት መዞሩ ነበር።
በኒኩሊየር የጦር መሳሪያ ከአሜሪካ ጋር ፉክክር ውስጥ የገባችው የመጀመሪያዋ ሀገር ጀርመን በቀዩ ጦር በግንቦት ወር 1937 ዓ.ም ተሸነፈችና ሁሉም የኒኩሊየር ማብላያ ተቋሞቿ እንዲወድሙ ሆነ:: በዚሁ የኒኩሊየር የጦር መሳሪያ ፉክክሩን በመጀመሪያው ሂደት በውጥን አስቀረው። ቢሆንም ከአድማስ ባሻገር አዲስ ጠላት በመሆን ኮሚኒስቷ ሶቭየት ሩሲያ ብቅ አለች። የኮሚኒዝም መስፋፋት የፈጠረው ፍርሃት የአቶሚክ ቦምብ ግንባታውን በአስደንጋጭ ወጥነት አፋፋመው።
ከጀርመን መፈረካከስ በኋላ ኮሚኒስቷ ሶቭየት ሩሲያ አሜሪካን እና የምዕራቡን ዓለም አጋሮቿን ተገዳዳሪ ታላቅ ሀያል ሆነች። የምዕራባውያን አጋሮች አንዳች የኮሚኒዝምን ጉዞ የሚያስቆም የማያዳግም የጦር መሳሪያ መሰራት እንደሚገባ ተገንዝበው ነበር።
ከመነሻው ለጀርመን ታስቦ የተነደፈው እና በጃፓን ላይ የተሞከረው ያ አንዳች ነገር በኋላ ለኮሚኒስቷ ሶቭየት ሩሲያ ጥቅም ላይ ዋለ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአንድ ጎራ የሚበሩት አሜሪካ እና ሶሺያሊስት ሶቭየት ኅብረት ከጦርነቱ ማግስት በርእዮተ ዓለም ልዩነት በባላንጣነት መተያየት መጀመራቸው የጦር መሳሪያ ፉክክሩን በመቀጠል ወደ ሁለተኛው የፉክክር ሂደት አስገብቷቸዋል።
በኒው ሜክሲኮ፣ በአላማጎርዶ አካባቢ ሐምሌ 9 ቀን 1937 ዓ.ም ከሦስቱ ቦምቦች የመጀመሪያው ተሞከረ። ትሪኒቲ ቴስት በመባል ይታወቃል። የተሳካው የትሪኒቲ ሙከራ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የኒኩሊየር ቦምብ ውልደትን እና የኑክሌር ዘመን ጅማሮን አበሰረ። ለታዋቂው የፊዚክስ ሳይንቲስት ከዚህ ሙከራ አስራ ሦስት ቀናት በፊት ለፕሬዝዳንት ሩዝቬልት በፃፈው ደብዳቤ እንደጠቀሰው የዓለምን መጪውን የጦርነት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የሚቀይረው አቻ የሌለው የጦር መሳሪያ በመሰራት ላይ መሆኑን ገልጾላቸው ነበር። አንዳንድ ሳይንቲስቶችም በአሜሪካ እና በሶቭየት መካከል የሚደረገውን የኒኩሌር የጦር መሳሪያ ፉክክር አደጋ አስቀድመው በማየት የአሜሪካ መንግሥት የኒኩሌር ምስጢሩን ለሶቭየት ኅብረት እንድታጋራ በመገፋፋት የጦር መሳሪያ ፉክክሩ እንዲቆም ይመክሩ ነበር። ነገር ግን ይህ ምክራቸው ሰሚ አላገኘም። እናም ፉክክሩ ድልን ተስፋ በማድረግ ቀጠለ።
ሁለቱ ሀያላን ሀገራት ዓለምን በሁለት ጎራ ከፍለው ከፍተኛ የቃላት ጦርነቱን አጧጧፉት። ሁለቱም በየፊናቸው ፕሮፓጋንዳ በማራገብ ደጋፊ ሀገራትን በየጎራቸው ለማሰለፍ ጥረት አደረጉ። ከኢኮኖሚ ፉክክሩ ጎን ለጎን ሁለቱ ሀያላን በወታደራዊው መስክ ያደረጉት ፉክክር አንዱ የቀዝቃዛው ጦርነት አካል ነበር።
የጦር መሳሪያ ፉክክሩን አሜሪካ እንደ ጀመረችው ብዙዎች ይስማሙበታል። ጃፓንን ለማንበርከክ አሜሪካ የተጠቀመችው አቶሚክ ቦምብ በአንድ ድንጋይ… እንዲሉ አንድም አስከፊውን ጦርነት ደምድሞ እፎይታን ያጎናፀፈ፣ ሁለትም ለአሜሪካ ተቀናቃኞች የቀጣዩ ዓለም ልዕለ ሀያልነቷን አይቀሬነት ያረዳ ነበር። ለታሪክ ደግሞ ሌላ መታጠፊያ ሆኗል። አሜሪካ እና ሶቭየት ሕብረት መልሰው በባላንጣነት ጎራ ለይተው የሚቀናቀኑበት አዲስ ምእራፍ የተከፈተበት አዲስ አሰላለፍ።
በአሜሪካ ወታደራዊ የበላይነቱ የተወሰደባት መሆኑ የገባት ሶቭየት ህብረት ሙሉ ትኩረቷን ወደ ጦር መሳሪያ ግንባታ ከማዞር የተሻለ አማራጭ አልነበራትም። ሶቭየት ህብረት አስቀድማ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት የኒኩሌር ጦር መሳሪያዎችን የመገንባት ስራዋን የጀመረች ሲሆን አደገኛውን አቶሚክ ቦምብ እስከ ሞከረችበት 1941 ዓ.ም ድረስ በስራ ላይ ነበረች። ይህንኑ የሶቭየቶቹን ጥረት በሚገባ የተረዳችው አሜሪካም የኒኩሌር አረሮቿን ቁጥር አሳደገች። በመሆኑም ከ1939 – 1948 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ አሜሪካ የኒኩሌር አረሮቿን ወደ 2422 ስታሳድግ፣ እንዲሁም ሶቭየት ህብረት ከ200 በላይ ማሳደግ አልቻለችም። ሶቭየት ህብረት ይህን ከፍተኛ ልዩነት ለማጥበብ አንዳች ርምጃ እንድትወስድ በክሩሽቸብ ላይ ግፊቱ አየለ።
ጥቅምት 1953 ዓ.ም ሶቭየት ህብረት ኖቫያ ዛምሊያ በተባለች የደሴት ግዛቷ ላይ አንድ አስፈሪ የአቶሚክ ቦምብ ሙከራ ባደረገችበት ወቅት መላው ዓለም ደነገጠ። ምዕራባውያን ዛር ቦምበር፣ ሶቭየቶች ደግሞ ‘የኩዝማ እናት’ እያሉ የሚጠሩት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተገነባው ግዙፍ እና አደገኛ ቦምብ የተባለለት ነበር። ከሂሮሽማው ቦምብ 3800 እጥፍ ሀይለኛ ነው:: በሬክተር ስኬል 5.0 የሚለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ማስነሳት ይችላል፤ በፍንዳታው የሚፈጠረው የጅብ ጥላ አይነት ደመና እስከ 60 ኪሎ ሜትር ወደ ሰማይ ይነሳል:: ሰባት እጥፍ ከኤቨረስት ተራራ ይረዝማል ማለት ነው። ስፋቱ 1.5 ኪ.ሜ የሚረዝም፣ 335 ሜትር ጥልቀት ያለው ሀይቅ ይፈጥራል። በ37 ኪ.ሜ ራዲየስ ውስጥ ያለን ማንኛውንም ነገር ሙሉ ለሙሉ ያወድማል። አንድ ዛር ቦምበር ብቻውን በዓለም ጦርነቶች የሚሞተውን ያክል ህይወት የማጥፋት አቅም እንዳለው ተገምቷል። በአጠቃላይ ሶቭየት ህብረት ዘግናኝ ውድመት የሚያስከትለው የዚህ አስፈሪ ቦምብ ባለቤት በመሆን ከአሜሪካ ጋር በሚሳየል ብዛት ያለውን ሰፊ ክፍተት ለማካካስ የቻለችበትን አጋጣሚ እውን አድርጋለች።
ይህ ከመሆኑ በፊት አሜሪካ በሚሳይል ያላት ሰፊ ብልጫ የኒውክሌር ጦርነት ቢነሳ ቀድማ ወደ ሶቭየት በመተኮስ የአፀፋ ጥቃት ሳያሰጋት ማሸነፍ የሚያስችል የራስ መተማመን ነበራት። ሶቭየቶች ግን ቀድመው ቢተኩሱ ራስን በራስ እንደማጥፋት አይነት ውጤት እንደሚያስከትል እሙን ነው። ስለሆነም አሜሪካኖች ሚሳየሎቻቸውን እያመጡ በሶቭየት አፍንጫ ስር በዙሪያዋ ባሉ ሀገራት ሲተክሉ ተቃውሞዋን ከመግለፅ ውጭ ምንም ማድረግ አትችልም ነበር። ይህን አስመልክቶም ፕሬዝደንት ክሩስቼቭ ሀገራቸው ሶቭየት ህብረት በሚሳየሎች ብዛት ከአሜሪካ በሰፊ ልዩነት ወደ ኋላ ስለመቅረቷ ጉዳይ በጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ፦
“አዎ! ኬኔዲ አለኝ ስለሚለው ነገር አውቃለሁ። በጣም ትክክል ነው። ነገር ግን አላማርርም…እኛ አሜሪካን በአንድ ዙር ብቻ የመጨረስ አቅም ያለን በመሆኑ እንረካለን። አንድ ብቻ በቂ ነው። በአንድ ምት የወደመን ሀገር ሁለተኛ መድገም ምን ይረባል? እኛ ደም የጠማን ህዝብ አይደለንም።”
የሚል ምላሻቸው ለአሜሪካ እና ደጋፊዎቿ በመስጠት እንደ ከባድ ማስጠንቀቂያ የተቆጠረ መልዕክት አስተላልፈዋል። ዛር ቦምበር አሁን ይሄን ታሪክ ቀይሮታል። ከሶቭየት ህብረት ጋር በኒውክሌር እሰጥ አገባ ውስጥ መግባት በእሳት እንደመጫወት መሆኑን ጠላቶቿ እንዲገነዘቡት በማድረግ ተከባብሮ በመኖር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን እንዲቀጥሉ አድርጓል።
አሜሪካ የምትመራው የምዕራቡ ወታደራዊ ጥምረት እስከ 1941 ዓ.ም ድረስ ብልጫ ነበረው:: አሜሪካ የዓለማችን ግንባር ቀደም ልዕለ ሀያል ሀገር በመሆን፣ ሶቭየት ህብረት በሁለተኛነት እየተከተለች በባላንጣነት ፉክክራቸውን አጠናከሩት:: በተለይ ደግሞ ተቀናቃኝ ወታደራዊ ጥምረቶችን መፍጠራቸው በሁለቱ ልዕለ ሃያላን ሀገራት መካከል ወታደራዊ እሽቅድድሙን አጠናክረው::
ይሁን እንጂ እስከ 1941 ዓ.ም ድረስ ብቸኛ አቶሚክ ቦምብ የነበራት አሜሪካ ነበረች:: አሜሪካ በማንም የማትጠቃ ሀገር ሆና እንድትቀጥልም ዋስትና ሆኗት ቆይቷል::
ሆኖም በ1941 ዓ.ም ሶቭየት ሕብረት የመጀመሪያ አቶሚክ ቦንቧን ሙከራ እንዳደረገች የአሜሪካ ብቸኛ የዓለም ልዕለ ሀያልነት ዘመን አከተመ::
ከዚህ በኋላ የሩሲያም የአሜሪካም ሳይንቲስቶች እና መሀንዲሶች አውዳሚ ቦምቦችን ማስወንጨፊያ አዳዲስ መንገዶችን ለመፈለግ ሥራቸውን ቀጠሉ:: ቦምቦችን በአውሮኘላን በመጣል ፋንታ ሌላ ስልቶችን በመፈለግ የሁለቱም ሀገሮች ባለሙያዎች፤ በከፍተኛ ፍጥነት ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችሉ ሮኬት የተገጠሙላቸውን ሚሳየሎች መገንባት ፈለጉ:: በመጨረሻም በፉክክሩ ሶቭየት ሩሲያ አሸነፈች::
የሁለቱ ሀያላን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ግንባታ ፉክክር ከፍተኛ ውጥረት የተፈጠረበት ከባዱ ወቅት ነበር፤ በጥቅምት ወር 1955 ዓ.ም ላይ የተከሠተው አስደንጋጭ ክስተት:: ዓለም በቅፅበት ወደ ምንምነት የምትለወጥበት በደቂቃዎች ውስጥ የብዙ ሚሊዮኖች ሕይወት የሚቀሰፍበት በውድመት አይነቱ እና መጠኑ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አስጨናቂ አደጋ፤ በኑክሊየር የሚደረግ ጦርነት፤ ምናልባትም የዓለም ፍፃሜ እና ሌላም የተባለለት ክስተት፤ የኩባ ሚሳኤል ቀውስ በሚል ይታወቃል:: ዓለምን ሲያስጨንቁ፣ ሲያሸብሩ የቆዩ ሁለት ሳምንታት፣ አሥራ ሶስት የጨለማ ቀናት፣ ከጥቅምት 15 እስከ 27 ቀን 1955 ዓ.ም ድረስ የቆየ የጥቅምቱ ሚሣየል ፍጥጫ:: በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንደነዚህ አይነት አስጨናቂ ጊዜያት አልተመዘገበም::
ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ደግሞ ኃያላኑን በኑክሌር ገደል አፋፍ ያስቆመ አደገኛ የኒኩሊየር ጦርነት ስጋት በዓለማችን ላይ አርብቧል። ዩክሬን እና ሩሲያ ዳግም የኒኩሊየር ውዝግቡን ቀስቅሰውታል፤ አውሮፓውያን በሩሲያ ላይ ያደሙ ይመስላል፤ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ሊቀሰቀስ በደጅ ነው እየተባለም ይፈራል፤፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ቁርቁሱ በኒኩሊየር መሆኑ አይቀርም፤፤ ዓለማችን ጭንቀት ውስጥ ገብታለች:: መሪዎች እንደ ኬኔዲ እና እንደ ክሩስቼቭ ብልህ መሆን ይገባቸዋል፤፤ ነገ ምን እንደሚከከሰት አይታወቅም፤ ቸር ያሰማን እያልን አበቃን::
ምንጭ-
Lawrence Freedman: The Evolution of Nuclear Strategy.
P:M.S. Blackett: Atomic Weapons and East West Relations.
Hedly Bull : The Control of the Arms Race.
Freed Ikle : Can Nuclear Deterrence last out the country?
አትላንቲክ ካውንስል መፅሄት
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም