በንስር እሳቤ

0
159

የሰው ልጆች አኗኗር ከሌሎች ፍጥረታት ጋር የሚመሳሰልም የሚለያይም ባህሪ አላቸው። ከመመሳሰል አንጻር አንበሳ የጀግንነት፣ እባብ የተንኮለኞች፣ ርግብ የመልካምነት፣ ንብ የታታሪነት፣ ጉንዳን በብልህነቱ፣ ጅብ የሆዳምነት ምልክት ተደርገው ይወሰዳሉ።

59 ዝርያዎች ያሉት ንስር የብዙ ንግግሮች ምሳሌ ተደርጎ ይነሳል። የሰው ልጆች ከተፈጥሮ ብዙ ትምህርት ወስደው ራሳቸውን ለመቀየር ካላቸው መሻት፤ የንስር ተፈጥሮ እና ትጋት ለሰው ልጅ አኗኗር ጥሩ ጉልበት እና መነሳሳት ሆኖ ይታያል። ነገር በምሳሌ በሚል የማስተማር ስነ ዘዴ ስላለፍን የንስርን ችሎታ እና አቅም ለራሳችን ይሆን ዘንድ ዛሬ በንስር እሳቤ ስለ ማደግ እና መግዘፍ እንጽፋለን።

አንበሳ የምድር እንስሳት ንጉሥ እንደሆነው ሁሉ፤ የሰማይ  የአዕዋፍ ንጉሥም ንስር ነው። ሰማዩን በነጻነት የሚንሸራሸርበት እሱ ነው። ከከፍታው እስከ ዝቅታው ሰማዩን ያካልላል። ምግብ ሲፈልግ ዝቅ ብሎ መብረር ይችላል። ውሎው ሌሎች አዕዋፍ ጋር አይደለም። ብቸኛ ነው። ከወፍ መንጋ ራሱን የነጠለ፣ ጠንካራ፣ አስተዋይ፣ ብርቱ እና ጀግና ወፍ ነው። የሐይቅ አሳ፣ የተራራ ፍየል፣ ጥንቸል፣ ቀበሮ እና ሌሎች አዕዋፍን ይመገባል። ዝቅ ብሎ ምግቡን ይፈልጋል፤ ምግቡን ከበላ በኋላ ከፍ ብሎ ሌሎች ወፎች በማይደርሱበት የሰማይ ከፍታ አየሩን  ይቀዝፋል።

በአመራር ጥበብ እና ሰብዕና ግንባታ ላይ በርካታ መጽሐፍትን የጻፈው ዶክተር ማይልስ ሙንሮ ንስሮች ሰባት መርሆች አሏቸው ሲል የሰው ልጆችም እነዚህን መርሆች እንዲከተሏቸው በመጥቀስ  ጽፏል። ሰባቱን የንስር መርሆዎች እንመልከት።

 

ከፍ ብሎ ብቻውን መብረር ይችላል

ከደመናዎች በላይ ከፍ ብሎ በመብረር ከአዕዋፍ ዘር ሁሉ ንስርን የሚስተካከለው የለም። እንደ ርግብ ወይም ቁራ፣ ወይም ጥንብ አንሳ ከደመናዎች በታች አይቀመጥም።

መሪዎችም እንደ ንስሮች ሁሉ የተለዩ እና ብቻቸውን ለመሆን መፍቀድ አለባቸው ይላል ማይልስ ሙንሮ። መሪዎች በመርሆቻቸው ለመታወቅ ሲሉ ዋጋ መክፈል ይኖርባቸዋል። የሰው ልጆች መንጋው ከሚያስበው እና ከሚከተለው መስመር ለብቻቸው ለመቆም ድፍረት እና ጉልበት ሊኖራቸው ይገባል።

ማንም ሰው ባይደግፋቸውም እንኳን ላመኑበት እና ሕይወታቸውን ለሚለውጠው እና የስኬት ጫፍ በሚያደርሳቸው መንገድ መጓዝ አለባቸው። ማንም ሰው የራሱ ሕይወት መስመር አለው። ማንም ማንንም ለመደገፍ አልተፈጠረም። ሁሉም የራሱን ጉዳይ ይዞ ይቸኩላል፤ ይጣደፋል።

ስለዚህ የራስህን ሕይወት ለመምራት አጃቢ አያስፈልግህም። ከማይበጁህ ርቀህ መሄድ፤ ዝቅ ብለው ከደረጃ በታች ከሚውሉ ሰዎች፤ በሰዎች ሐሳብ ከሚነዱ ወዳጆች፤ የራሳቸው ግብ ከሌላቸው አጋሮች ተነጥለህ ከፍ ብሎ መጓዝ ያስፈልግሃል።

ንስር ቁራን ይፈራዋል ይባላል። ቁራም ንስርን አባሮ ጀርባው ላይ ይቀመጥና አብሮት ሊበርር ይሞክራል። ንስር ብልህ ነው። ቁራው ጋር አይገጥምም። ከፍ ብሎ መብረር ይጀምራል። ቁራው እሱ ለመብረር ጉልበት ስለሌለው በንስሩ ትክሻ ላይ ሆኖ አየር ሲቀዝፍ ደስ ይለዋል።

እናም ንስሩ መለኛ ነው። ከቁራዎች የዝቅታ አየር ክልል ከፍ ብሎ ሽቅብ አየሩን ሲቀዝፈው ቁራው አየር እያጠረው ይመጣል። በሒደት ቁራው ከንስሩ ትክሻ ላይ ወርዶ ቁልቁል ይፈጠፈጣል። ንስሩ መገኛ ቦታውን በማስጠበቅ ነው ራሱን የሚያስከብረው። ቁራ ደካማ ነው። በንስር ትክሻ መጓጓዝ ይወዳል። ንስር ከከፍታው ወርዶ መሬት ላይ መገኘቱ ለቁራ ባርነት ዳርጎታል።

ውሏችን፣ ጓደኞቻችን፣ መገኛችን ሕይወታችን የሚኖረውን መልክ ይወስኑታል። የሰው ልጆች ደረጃቸውን ረስተው በማይመጥናቸው ቦታ የተገኙ ቀን ሎሌያቸው ሎሌ  ያደርጋቸዋል። ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት በሰዎች ዘንድ እንዲናቁ ወይም እንዲከበሩ ያደርጋቸዋል። ንስር ራሱን ላለማዋረድ ነው ከመንጋው ተነጥሎ መሰሎቹ ጋር በከፍታ መኖር የመረጠው።

ማይልስ ሙንሮ ኔልሰን ማንዴላን በምሳሌነት ያነሳል። ማንዴላ በትግሉ ወቅት ብቸኛ ነበር። ብዙኀኑ አሜን ብለው የተቀበሉትን ባርነትን ተቃውሞ ተነሳ። መስዋእትነት ከፍሎ ከዓመታት በኋላ የማንዴላ ሐሳብ የብዙዎቻችን ሐሳብ ሆኗል። የነጻነት ታጋይ ተብሎ ስሙ የተጠራው ዓላማውን ለማሳካት የተጓዘበት መስመር እና ጽናት ነው።  ዝናብ እና ወጀብ ሲመጣ ሁሉም ወፍ መጠለያ ፍለጋ ይሮጣሉ።

ዛፍ እና ቤት ጥግ ይጠለላሉ። ንስር ግን ወጀብ እና ዝናብን አልፎ ከፍ ብሎ በመብረር ሌሎች የተቸገሩበትን ትርምስምስ ያልፈዋል። የወፎች ችግር ለንስር ችግሩ አይደለም። ሽቅብ ለመብረር እድሉ ነው። ብዙ ሰዎች ከአብዮት በኋላ ከተደበቁበት ወጥተው የትግሉ መሪ እኔ ነበርሁ ይላሉ። በትግል ወቅት ግን ተደብቀው ነበር። ንስር ይታገላል፣ አይደበቅም።

 

ንስሮች ጠንካራ ዕይታ አላቸው

ንስር ከወፍ ዘሮች ሁሉ የላቀ ዕይታ አለው። 340 ዲግሪ ማየት ይችላል።  በሰማይ የሚበርር አንድ ንስር ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ ከምድር ያለችን ጥንቸል እንቅስቃሴ ማወቅ ይችላል፤ በሚገባም ይለያታል። ንስር ሌላው የሚታወቅበት አቅሙ ትኩረቱ ነው። በሰማይ ክንፉን ዘርግቶ ሲንሳፈፍ አንዲት ነገር ላይ ለይቶ ካነጣጠረ እስከሚይዛት ድረስ ዓይኑን አይነቅልም። ጥሩ የማየት አቅም ከትኩረት ጋር የተሰጠው ንስር ለሰው ልጆች የሚያስተምረው ነገር አለው።

እኛ የሰው ልጆች አቅማችንን በሕልማችን እና ግባችን ላይ ብናደርግ ለስኬት ደጃፍ አንርቅም። ልዩነቱን የሚፈጥረው ትኩረት ማድረግ የሚገባንን መለየት እና አለመለየት ነው። ብዙ ጉልበት እና አቅማችን በማይመለከተን ሐሳብ እና ድርጊት ላይ ባክኗል። የሕይወት እቅዶችን እንደ ንስር ቀድመን አስበን አልሰራንም። ከአስር እና ሀያ ዓመታት በኋላ የሚኖረንን ሕይወት አስቀድመን በማየት አድራሽ የሕይወት አቅጣጫ መንደፍ ከንስር የምንማረው እውቀት ነው።

 

ንስር የሞተ አይበላም

ንስር እንደ ጥንብ አንሳዎች የሞተ ነገር አይበላም። የራሱን ግዳይ ጥሎ ትኩስ ስጋ ነው የሚመገበው። በተለይ መሪዎች ቀደም ብለው በተሰሩ ነገሮች ላይ እምነት እና ጥገኝነት ሊኖራቸው አይገባም። ሰዎች በሰሩት መንገድ ስንት ጊዜ እንመላለሳለን፣ አዲስ መንገድ አንሰራም እንዴ? ብሎ የሚጠይቅ አዕምሮ ለሰው ልጆች ከንስር ሕይወት የሚማሩት ቁም ነገር ነው። አዲስ ሕይወት፣ አዲስ አቅጣጫ፣ አዲስ ስልት እና ጥበብ ሁልጊዜ ያስፈልገናል።

ሁልጊዜ ወርቃማ እና አዲስ ስትራቴጂዎችን ይዘን መምጣት አለብን ሲል ማይልስ ሙንሮ የንስርን ተፈጥሮ ትርጉም ሰጥቶታል። በፋሽን እና ሰሞንኛ መነዳት ሳይሆን አዲስ ፋሽኖችን መፍጠርን መማር ያስፈልጋል።

በተለይ በመሪነት ላይ የሚገኙ ሰዎች አዲስ መንገድ የሚጠርጉ፤ ርምጃን የሚያመለክቱ፤ የጉዞ ዱካቸውን ለተከታዮች የሚያስቀምጡ መሆን አለባቸው። ለሰዎች መስጠት የጀመርነውን መስጠታችንን የምንቀጥል፤ በጽናት የምንጓዝ እና በማንም የማንተካ የግላችን አሻራ ያለን ሰዎች መሆንን ከንስር ልንማር ይገባል ብሏል ማይልስ። ጅብ ብዙ ጊዜ አንበሳ አድኖ እስኪበላ፣ በልቶም እስኪጠግብ፣ ትርፉን ጥሎለት እስኪነሳ ለመብላት ይጠብቃል።

በሰዎችም ዘንድ እንዲህ ዓይነት እሳቤዎች አሉ። የመስራት አቅም እና ጉልበት እያለን ሰዎች የሆነ ነገር እስኪያደርጉ፣ እስኪሰጡን ወይም ደግሞ ትርፍራፊ እስኪቀር እንጠብቃለን።

ያልሰሩበትን መብላት የተለመደ የሰነፍ አባዜ ነው። መስራት የሚፈልግ ሰው ትኩስ ምግብ ያገኛል። ሰነፍ የቀዘቀዘ፣ ትርፍ ይበላል። ያንንም የሚሰጠው ካገኘ ነው። ንስሩ ማንንም አይጠብቅም። ከከፍታው ቁልቁል ተምዘግዝጎ የዱር ፍየል፣ አይጥ፣ ጥንቸል፣ ወይም አሳ ይዞ ይመለሳል። ሰነፍ ሰዎች ሞፈር ከደጃቸው ሲቆረጥ፤ እድል ሲያልፋቸው፤ መለወጥ ሲሸሻቸው ዝም ብለው ያያሉ።

 

ንስር ማዕበል እና ነጎድጓድ ይወዳል

ዝናብ፣ በረዶ፣ መብረቅ፣ ነፋስ እና ውሽንፍር ሲመጣ ሁሉም ወፍ መደበቂያውን ይፈልጋል። የሚሞቱም ብዙ ናቸው። ንስር ግን ይህን ሲያይ ወደ ከፍታው ለመውጣት ስለሚጠቀምበት ደስታው ወደር የለውም። በችግሮች ውስጥ ሁሉም ሲደናበር እና መሸሸጊያ ሲያስስ ንስሮች በጥንካሬ መብረር ያውቁበታል። ማይልስ “እንደ መሪ አስቸጋሪ ጊዜዎች ይመጣሉ፤ አንተን የሚያጠፉ ግን መሆን የለባቸውም” ይላል። ንስሩ የሚጋፋውን ነፋስ እንደ ወራጅ ውኃ ተንሸራቶበት የሚፈልገው ቦታ ይደርሳል። ንስሩ ዝናብ እና ነፋሱን ችግር ማድረግ ባልጠፋው ነበር፤ ብልህ ስለሆነ የማደጊያ እና ወደ ከፍታው ስፍራ መውጫ እድል፤ አጋዥ ያደርገዋል እንጂ። ነፋሱ እና ደመናው ያለበትን ስፍራ በርሮ ያልፈዋል። ወደ  ጸጥታው መዳረሻ ያደርገዋል። ብዙ ጉልበት ሳያባክን በነፋስ እየተዝናና በረራ የሚያደርግበት ቦታ ላይ ይደርሳል።

“ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ለውጥ አይቀሬ ነው። ለውጥን ተቀበል። ማዕበሉን አትፍራው፤ መንሳፈፊያ አድርገው ወደ ጸጥታው ስፍራ ድረስበት። የማደጊያ ዕድል አድርገው፤ ወጀቡን አልፈህ አዲስ ሕይወት ላይ ትደርሳለህ” የሚለው ሐሳብ፤ ከንስር ማዕበል ወዳድነት የምናገኘው ትምህርት ነው። ብዙዎቻችን ችግር አንወድም። ፈተና አንወድም። ትንሽ እንቅፋት ካገኘን እሱን ሰበብ አድርገን ቆመን ማልቀስ እንወዳለን። ንስሮች ችግር ሲመጣ  እናቱን አይቶ ሳቅ ሳቅ እንደሚለው ሕጻን ይደሰታሉ።

ንስር ከማመኑ በፊት ይፈትሻል

ንስር ክንፍ አለኝ ብሎ በግብዝነት አይበርርም። ንስሮች ከፍ ብለው ሰማዩን የሚያስሱት ማዕበሉን ለከፍታቸው እንዴት እንደሚጠቀሙበት ስለሚያውቁ ነው። የነፋሱን አቅጣጫ ይፈትሹታል። እሱን ተከትለው እያታለሉ ወደ ሚፈልጉት ይጓዙበታል። ነፋስን ይጠቀሙበታል እንጂ አይጠቀምባቸውም።

ወቅት እና ጊዜን ማጤን ከብልህ ይጠበቃል። የተከፈተ በር ሁሉ ለእኛ አይሆንም። ጉልበት፣ ጊዜ እና ሀብትን የት ፈሰስ ማድረግ ያስፈልጋል የሚለውን ማወቅ፤ መመርመር እና በብልህነት ማየት ተገቢ ነው። ነገሮች ከመፈለግ ባሻገር አንዳች ዓላማ ይዘው መደረግ አለባቸው። ችግሮችን መጋፈጥ ተገቢ ነው። ችግሮችን ስንጋፈጥ ግን ጥቅም እና ጉዳቱን አስልተን መሆን አለበት። የተሰላ አደጋን የመጋፈጥ ልምምድ ያስፈልጋል።

ንስሮች ሌሎችንም በማሰልጠን ይተጋሉ

ንስሮች እንደተወለዱ ልጆቻቸውን ጠንካራ እንዲሆኑ ያሰለጥኗቸዋል። እናቷ ንስር ልጇን ከተኛችበት የቆጥ ጎጆ ገፍታ እንድትወድቅ ታደርጋለች። ልጆች ሕይወትን ብቻቸውን እንዲጋፈጡ ታዘጋጃቸዋለች። በሰማይ እንዴት መብረር እንዳለባቸው ታስተምራለች። ጫጩቶች ሲወድቁ እየደገፈች ጉዳት ሳይደርስባቸው መብረር እንዲለምዱ ታስተምራለች። በዚህ መልኩ ልጆቿን ታሰለጥናለች።

ሐቀኛ መሪዎችም ሌሎች መሪዎችን እና ተከታዮቻቸውን ያሰለጥናሉ። የእነሱ ስኬት በሚከተሏቸው ሰዎች ጥንካሬ እንደሚወሰን በሚገባ ያውቃሉ። መሪነት አንድ ሰው ላይ ከቆመ፤ ኪሳራ ነው። መሪነት በቀጣይ ትውልድ እና መሪዎች ሲታይ ነው ትክክለኛነቱ የሚረጋገጠው። አንድ መሪ የጀመረውን ሌሎች ተከታዮች ሲያስቀጥሉት ስኬታማ ቅብብሎሽ ይኖራል። ካልሆነ ግን አንዱ የጀመረውን የሚተካው ያፈርሰዋል። አንዱ ሰማይ የሰቀለውን ተተኪው አንኳሶ ይጥለዋል።

 

ንስሮች ራሳቸውን ያድሳሉ።

ንስር ሰባ ዓመታትን ይኖራል። አርባ ዓመት ሲሞላው ግን ሞት ወይስ ሕይወት የሚሉ ሁለት ምርጫዎች ይቀርቡለታል። በአርባ ዓመቱ ከተራራ ላይ ፍየል ተሸክሞ ሽቅብ የሚበርባቸው ጥፍሮቹ ይሟሽሻሉ። ሰማይ የሚቧጥጡት ክንፎቹ አይታዘዙትም። ሰውነቱ እርሱን ይጫጫነዋል። ለመብረር ይቸገራል። በዚህ ጊዜ ንስር ለ 150 ቀናት በስቃይ በማሳለፍ ሰላሳ ዓመት መቀጠል ወይም የመሞት ምርጫዎች መሐል ይወድቃል። ንስሩ ሞኝ አይደለም፤ በሕይወት መቀጠልን ይመርጣል። ሕመም የተሞላበትን የመታደሻ ሒደት ያልፋል። እናም ከመንጋው ተነጥሎ ለብቻው ጎጆ ቀልሶ ራሱን አፍርሶ ለመስራት ይዘጋጃል። በዚያም አሮጌ ምንቃሩን ከድንጋይ ወይም እንጨት ጋር እያጋጨ ያወልቀዋል። አዲስ ምንቃር እስኪበቅል በትዕግሥት መጠበቅ አለበት። ምንቃሩን አውልቆ አዲስ ማብቀል ሁለት ጊዜ ሕመም አለው። አሮጌው እንደ ጥፍር እስኪረግፍ ያማል። አዲሱ በቅሎ እስኪጠነክር ያንሰፈስፋል።

በመቀጠል ጥፍፎቹን መንቀል ይጀምራል። ለንስር ጥፍር ዋና የምግብ ማጥመጃው መሳሪያው ነው። በ150 ቀናት ውስጥ ለንስር በረሃብ ውስጥ ማለፍ ከባድ ነው። ከፍተኛ የሕመም ስቃይ እየገጠመው ጥፍሮቹን ያወልቃል።

ቀደም ብሎ በአዲስ በበቀለው ምንቃሩ እና ጥፍሩ ክንፎቹን መንቀል ደግሞ ይጀምራል። ክንፎቹን እያመመው ይነቅላል። መብረር ስለማይችል ለወራት ረሀብን መታገስ አለበት። በሒደት ክንፎቹ በአዲስ መተካት ይጀምራሉ። ከአምስት ወራት በኋላ ንስሩ አዲስ ወጣት ሆኖ ይወለዳል። ተጨማሪ ሰላሳ ዓመታትን ለመኖር በመከራ ውስጥ አልፏልና በደስታ ይኖራል።

አንዳንድ ጊዜ የድሮ ትዝታዎችን፣ ልምዶችን እና ድርጊቶችን ማስወገድ ግድ ይላል። ያለፉትን ሸክሞች አራግፈን ዛሬን  በአዲስ መኖር ያስችለናል። አስቸጋሪ ጊዜያት ጠንካራዎች እንድንሆን ይሰሩናል። የምቾት ጊዜያት በዚያው ልክ ያሰንፉናል። የንስሮች ሕይወት ብዙ የሚያስተምረን እውቀት አለ። ንስሮች በጥንድነትም ቢሆን አንድ ለአንድ በሚለው ያምናሉ። አንድ ጊዜ ሚስት ወይም ባል ካገቡ ጥንድነቱ የሕይወት ዘመን መጨረሻ ድረስ ዘላቂ ነው። ከሌላ ንስር ጋር ግንኙነት አይመሰርቱም።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here