በተራዘመ ጦርነት፣ ጊዜ በወሰደና ቶሎ ባልተፈታ ግጭትና ብጥብጥ ውስጥ ሞት፣ አካል
መጉደል፣ መፈናቀልና ስደት ሁልጊዜም አሉ:: ከዚህ በተረፉት ደግሞ አካላዊ፣ ስነልቦናዊና
ቁሳዊ እንዲሀም ቋሚና ጊዜያዊ ጉዳትን አስከትሎ ያልፋል::
ከነዚህ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች መካከል የትምህርት መቋረጥ አንዱ ነው:: በተለይም እንደኛ
ባለ ታዳጊ ሀገር ትምህርት የችግር ሁሉ መፍቻ፣ የዕድገት መሰረትና መውጫ መንገድ ነው::
በጦርነት ምክንያት ብዙ ሕጻናት መደበኛ ትምህርታቸውን መከታተል ያቆማሉ::
አንዳንዶቹ ከመኖሪያ ቀያቸው ይፈናቀላሉ:: በአካቢያቸው የቀሩት ደግሞ ከዛሬ ነገ ምን
ይፈጠራል በሚል ስጋት ውስጥ ይኖራሉ:: በትምህርት የመለወጥ ተስፋና ራዕይ የነበራቸው
ባለብዙ ሕልም፣ ችግር ፈችና መፍትሔ አፍላቂ ጭንቅላት ባለቤቶች ሁሉ የትም ተበትነው
በምን ይሆናል ስጋት ከነሕልማቸው በተስፋ መቁረጥ እንዲቀመጡ ምክንያት ሆኗል::
ምንም እንኳን በዓለም አቀፍ የጦር ሕግ ትምህርት ቤቶችና የሃይማኖት ተቋማት
ከጦርነት ኢላማነት የሚከለክል ህግ ቢኖርም ብዙ ትምህርት ቤቶች ፈርሰዋል፤ አብዛኞቹ
ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው አልተመለሱም:: የመጡትም ከፍርሃትና ከስጋት ነጻ
ሆኖ የመማር ስነልቦናዊ ዝግጅት አይኖራቸውም::
በጦርነትና በግጭት መሃል የሚያልፉ ሕጻናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም
ለመጨረስ አልቻሉም::
በተለያየ ጊዜ በተለያየ ምክንያት የትምህርት መቋረጥ በትምህርት የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ
ጥቅም ያሳጣል:: በጤና፣ በኢኮኖሚያዊና በፍትሀዊ ተጠቃሚነት፣ በማህበራዊ ደህንነትና
በዓዕምሮ ጤና መስክ የሚኖረውን እኩል ተጠቃሚነትና እድል በማሳጣት ለድህነትና
ለጉስቁልና የሚያጋልጥ ጉዳት አድርሶ ያልፋል::
በተለይም በአማራ ክልል ባለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ ክልሉ ውስጥ በነበረው ጦርነትና
አሁንም ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት ተስተጓጉሏል::
በግጭት ውስጥ ተማሪዎችን ፍርሃት፣ ስጋትና ቀጥሎ ስለሚከሰተው ነገር እርግጠኛ
አለመሆንና ተስፋ መቁረጥ ይጫናቸዋል:: ይህንን ስሜት ተቋቁመው በሚማሩትም ላይ
ቢሆን ውጤታማነታቸውን በመፈተን የጦርነቱና የግጭቱ ጠባሳ ጫና ያሳድርባቸዋል::
ይህንን ስሜት ለማከምም የስነልቦና ህክምናና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል::
በጦርነትና በግጭት ከሚደርሰው ዘርፈ ብዙ ችግር የሁሉም የስራ መስኮች የጀርባ
አጥንት የሆነው አንዱ የትምህርት ዘርፍ በዚህ መልክ መጎዳት ለሁለም መስክ መጎዳት፣
ለትውልድም ብሩህ እጣ ፋንታ መጨለም ነው:: በተለይም በተራዘመ ጦርነትና ግጭት ብዙ
ዋጋ የከፈሉ ሀገራት ስለሰላም አብዝተው የሚሰብኩት የህመሙን ክብደት በማየታቸው
ነው:: በርግጥስ የሰላምን ዋጋ ለመመዘንና ዋጋ ለመስጠት ምን ያህል ህይወት መስዋእት
ሲሆን ነው የሚገባን? ለውይይትና ለንግግር በር የዘጋ ልቦና ይዘን ሰላምን ለማምጣት
ከጦርት መማርን እንዴት መረጥን? አሁንም በንግግር የሰላም በር ይከፈት!