በአሜሪካ፡- የልጆች የእረፍት ጊዜ

0
66

ልጆች እንዴት ናችሁ? ሳምንቱስ እንዴት አለፈ? አሁን ላይ ከአፀደ ሕፃናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለእረፍት የተዘጉበት ወቅት ነው፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግ በውጪ ሀገራት ልጆች የእረፍት ጊዜያቸውን  እንዴት እንደሚያሳልፉ ልናሳውቃችሁ ፈለግን፡፡

በአሜሪካን ሀገር ትምህርት የሚዘጋው በበጋ ነው፡፡ የአሜሪካ አብዛኛው አካባቢ በበጋ በጣም ሞቃታማ የአየር ጸባይ ይኖረዋል፤ በዚህም ልጆች  ጊዜያቸውን ከሚያሳልፉባቸው ቦታዎች መካከል ”የበጋ ካምፕ” አንዱ ነው፡፡ ልጆች በካምፑ  የስፖርት፣ የሥነ-ጥበባት እና የሳይንስ  ክህሎታቸውን ያሳድጋሉ፡፡ እርስ በርስ መግባባትን ስለሚፈጥርላቸው በአብዛኛው በዚህ መልክ ያሳልፉሉ። አንዳንድ ወላጆች ደግሞ ሙሉ ጊዜያቸውን  በሥራ የሚያሳልፉ ከሆነ  ልጆቻቸውን በመዋዕለ ሕፃናት ወይም በሕፃናት ማቆያ ማዕከላት ያቆያሉ።

ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ደግሞ ሌላው ልጆች በእረፍት ጊዜ የሚያደርጉት ነው፡፡ ይህም ለማህበራዊ ልማት አስፈላጊ ነው፡፡ መናፈሻ መጎብኘት፣ የተለያዩ ጨዋታዎችን መጫወት ወይም በቀላሉ አብሮ ጊዜ ማሳለፍን ሊያካትት ይችላል፡፡

ትምህርታዊ ተግባራትንም ልጆች በእረፍት ጊዜያቸው ያካሂዳሉ፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው ቀላል ትምህርታዊ ክለሳን፣ ትምህርታዊ ጨዋታዎችን ወይም ወደ ሙዚየሞች ወይም ቤተመጻሕፍት ጉብኝት እንዲያደርጉ ያመቻቻሉ።

ያለ ወላጅ ፈቃድ እና እውቅና ከቤት ርቆ ሄዶ እና መኪና መንገድ ላይ መጫወት፣ ከአቅማቸው በላይ እና ያልተፈቀደላቸውን ተግባራት ከማከናወን ልጆች መቆጠብ አለባቸው፡፡ ረጅም ጊዜ ስልክ ወይም ቴሌቪዢን ላይ ማሳለፍ፣ ውኃ ወደሚያቁሩ ቦታዎች እና ወደ ወንዝ በመሄድ ለመዋኘት መሞከርም ለአደጋ ስለሚያጋልጥ ለአሜሪካዉያን ልጆች ከወላጅ ፈቃድ ውጭ ክልክል ነው፡፡

ምንጭ፡- ፓረንትስ (parents)፡፡

ሞክሩ

  1. ወተቷ የሚጠጣ ስጋዋ ማይበላ ምንድን ናት?
  2. አንድ ኪሎ ሜትር ስንት ሜትር ነው?
  3. የብራዚል ዋና ከተማ ማን ትባላለች?

 መልስ

  1. እናት
  2. አንድ ሺህ ሜትር
  3. ብራዚሊያ

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here