በአስቂኝ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ለሽልማት

0
35

የጃፓን የተመራማሪዎች ቡድን ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው የቤት እንስሳትን እንደ ሜዳ አህያ “ዜብራ” ወይም  ነጭ ቀለም በሰንበር ንድፍ ወይም ዥንጉርጉር እንዲሆን መቀባት ከተናካሽ ዝንብ መከላከል ማስቻሉን ባረጋገጠው የጥናት ውጤት “የኤልጂ”  ወይም አስቂኝ የፈጠራ ውጤት ሽልማት አሸናፊ ሊሆን ማስቻሉን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል::

የ “ኤልጂ” ሽልማት ሰዎችን የሚያስቁ “ፓራዶክስ” ወይም “አያዎ” በመጀመሪያ የማይመስሉ ኋላ ላይ ሲታሰቡ ግን ትክክል ለሆኑ የፈጠራ ውጤቶች የሚሰጥ  መሆኑ ነው ለንባብ የበቃው:: በያዝነው 2025 እ.አ.አ ዓመት ለዚህ ሽልማት የበቃውም  ከጃፓን አይቺ የግብርና ምርምር ማእከል የተሳተፈው ቡድን ሆኗል::

ቡድኑ ባቀረበው የምርምር ውጤት እንደ ሜዳ አህያ  “ዜብራ” ጥቁር ቀለም ያላቸው የጋማ ከብቶችን ነጭ ቀለም በተመጠነ ርቀት መቀባት ከተናዳፊ ዝንቦች ንክሻ 50 በመቶ መጠበቅ ማስቻሉ አመላክቷል::

ተናካሽ ዝንቦቹ ከብቶቹን ግጦሽ ወይም መኖ ሲበሉ  በመናደፍ ክብደታቸው እንዲቀንስ፣ የወተት ላሞች ደግሞ የሚሰጡት የወተት መጠን እንዲያንስ ያደርጋል:: ከዚህ ባሻገር  ይህንን ችግር በፀረ ተባይ ርጭት መከላከል በእንስሳቱ ሥጋም ሆነ የወተት ተዋፅኦ ጤናማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ቀደም ባሉ ጥናቶች መረጋገጡን አንስቷል- ቡድኑ::

የተመራማሪዎች ቡድኑ የጥናት እና ምርምር አድማሱን አስፍቶ ዓለም አቀፋዊ እውነትነቱን ለማረጋገጥ በሌሎች ለአብነት ሀንጋሪ፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድ በመሳሰሉት ሀገራትም ተሞክሮ ነጭ ቀለም የተቀቡት ካልተቀቡት 50 በመቶ ከመነደፍ መዳናቸውን አረጋግጠዋል::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here