“በአቋማችን ባሕር ዳርን እና ሕዝቧን ከጥፋት ታድገናል”

0
84

በክፍል አንድ ከሌትናል ኮሎኔል አለሙ መብራት ጋር የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሳን ቆይታ አድርገናል፡፡ አስተዳደጋቸውን እና ወደ ውትድርና የገቡበትን አጋጣሚ አንስተን ነግረውናል፡፡ በዚህ የመጨረሻ ክፍል ሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊትን፣ የቀይ ኮከብ ዘመቻን እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ እንደሚከተለው እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

መልካም ንባብ!

በዐፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከኢትዮጵያ ውጪ ለስለላ የወጡበት አጋጣሚ ምን ይመስል ነበር?

 

በአዋሳኝ የሱዳን እና ኢትዮጵያ አስተዳዳሪዎች በየጊዜው የሚያደርጉት ውይይት እንዳለ ሆኖ በሱዳን በኩል ተጨባጭ መረጃ እና መግባባት ባለመኖሩ በመካከላቸው ቅራኔው እየሰፋ መጥቶ ነበር፡፡ ከዚህ በመነሳት የተመረጡ የጦር መሪዎች ወደ ሱዳን ዘልቀው በመግባት የሱዳን ገዳሪፍ መልክዓ ምድርን  እንዲቃኙ  ተልከዋል፡፡ እነዚህን የጦር፣ መሪዎች አላውቃቸውም፣፡፡ እኔም ሱዳን ገዳሪፍ አንድ ሆቴል ውስጥ ሞርስ ሬዲዮ ጠምጄ ከእነርሱ የማገኘውን ምስጢራዊ መልዕክት ወደ አዲስ አበባ አደርሳለሁ፡፡ የእኔ  ተግባር ወታደራዊ መኮንኖቹ ሲሰልሉ የዋሉትን መረጃ ለሚመለከታቸው አካላት በሬዲዮ ማድረስ ብቻ ነው፡፡ ገዳሪፍ የቀን ሠራተኛ መስለው እንዲሁም ሌሎችም የእኛ ሰዎች መረጃውን እየሰበሰቡ ያደርሱኝ ነበር፡፡ ሁሉንም መልዕክት በሞርስ ሬዲዮ ቀጥታ ወደ ቤተ መንግሥት ነበር የማደርሰው፡፡ ምንአልባት በሱዳኖች ቢደረስብኝ አሊያም ብጠለፍ ተብሎ የመልዕክቱ ምስጢር ከእኔም የተሰወረ ነው፡፡

 

ለ13 ቀናት ገደማ አስፈላጊ ምስጢራዊ መረጃዎችን ካስተላለፍኩ በኋላ ግን አንድ አደገኛ ነገር መፈጠሩ ተነገረኝ፡፡ ካርቱም የሚገኘው ብሔራዊ መገናኛ ሬዲዮ መቆጣጠሪያ መምሪያ በምስራቃዊ ሱዳን  ገዳሪፍ ጫፍ የማይታወቅ እንግዳ ሞርስ ሬዲዮ ግንኙነት ላይ እንዳለ ደርሶበታል፡፡ ይህን መረጃ ደግሞ ሱዳን ያለው የኢትዮጵያ ሬዲዮ መቆጣጠሪያ ደርሶበታል፡፡

በወቅቱ በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ  የሞርስ ሬዲዮ ኦፕሪተር  ሻለቃ ባሻ አሻግሬ ይባላል፡፡ በእኛ ዘመን የሞርስ ሬዲዮን  ከሚራቀቁበት ባለሙያዎች አንዱ  ነበር፡፡ የሱዳን መንግሥት የሬዲዮ ክትትሉን እንደጠለፈ እና ጥንቃቄ እንዲደረግ ለአዲስ አበባ አስታወቋል፡፡ ያን ጊዜ በሱዳኖች ቁጥጥር ስር እንዳልወድቅ ጥበቃ የሚያደርጉልኝ የኢትዮጵያ ደህንነቶች ነበሩ፡፡ ከዚያም ከእነ ሞርስ ሬዲዮዮ እንድመለስ መልዕክት ተላከልኝ፡፡

 

ገዳሪፍ ሆቴል ውስጥ እንዳለሁ የክፍሌ በር ተንኳኳ፡፡ ማንነታቸውን ጠየኩ፤ የእኛ ሰዎች መሆናቸውን በሚስጥር መለያ አረጋገጥኩ፡፡ ከዚያ በላንድሮቨር ከገዳሪፍ ሁመራ ገባሁ፡፡ በንጉሡ ጊዜ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ድንበር ሁኔታ ልዩ ትኩረት ይሰጠው ነበር፡፡

ሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት በመጽሐፍዎ በደንብ ከተብራሩ የታሪክ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ምን ሠራ?

የሶማሊያ እብሪተኛ ወራሪ ኃይል ላይ ጠንካራ ክንዱን ያሳየው እና ድል የተቀዳጀው የኢትዮጵያ ሠራዊት ፊቱን ከምስራቅ ወደ ሰሜን ባዞረበት ወቅት ነበር፡፡ በወቅቱ ግንቦት 1970 ዓ.ም የሰሜን ኢትዮጵያ ገንጣይ አስገንጣይ ወንበዴዎችን ለመምታት ፀረ -አማጺ ዘመቻ ለመምራት ብሔራዊ አብዮታዊ ዘመቻ ዋና መምሪያ መቀሌ ከተማ ላይ ተቋቋመ፡፡ ታሪክ እንደሚዘክረው ያን ጊዜ ልዩ ልዩ የሠራዊት  ግብረ ኃይሎች ተዋቀሩ፡፡ ግብረ ኃይሎቹ 501ኛ ከሰቲት ሁመራ ተነስቶ በአሊ ጊደር እና  በተሠነይ በማድረግ ነበር የዘመተው፡፡ እንዲሁም 502ኛ፣ 503ኛ፣ 504ኛ፣ 505ኛ፣ 506ኛ እና 507ኛ በየአቅጣጫው ተሰማሩ፡፡

 

የሠራዊቱ ቁጥር ደግሞ 87 ሺህ ነበር፡፡ 503ኛ ግብረ ኃይል መነሻውን ከዓድዋ አደርጎ በኮሎኔል ካሳ ገ/ማርያም እየተመራ በራማ አድርጎ መረብን ከተሻገረ በኋላ  አዲ ኳላን፣ መንደፈራን፣ ዓረዛንኩዚ ያምረአማኒ እና ድባርዋን በቁጥጥር ስር አዋለ፡፡ በኋላም ከሸክቲ ላይ  ከ506ኛ ግብረ ኃይል ጋር ተገናኘ፡፡ የ503ኛ ግብረ ኃይል ለንዑስ ግብረ ኃይል አዛዥ በነበሩት ኮሎኔል ታሪኩ ዐይኔ መሪነት  በጎረ ሰናይ፣ በእንትጮ አንስቶ በጾረና  በኩል ደቀ መሃሪ ገባ፡፡ እኔም የ66ኛ ክፍለ ጦር የፖለቲካ ኃላፊ በመሆን በዚሁ ግንባር ነበር የተንቀሳቀስኩት፡፡

 

ሌላው 503ኛ ሐ ንዑስ ግብረ ኃይል ክንፍ ደግሞ በኮሎኔል ሰይፉ በመመራት አዲግራት ተነስቶ በሁለት አቅጣጫ  አዲ ቀይህን አቋርጦ ግራ እና ቀኝ የሚገኘውን እና የመሸገውን የሻዕቢያን ሸማቂ  በመደምሰስ አካባቢውን ነጻ አወጣ፤ ደቀ መሀሪንም ተቆጣጠረ፡፡ የትግሉ ዋነኛ ዓላማ በአስመራ ከተማ ለወራት በወንበዴ ተከቦ የከረመውን ሕዝብ እና ሰሜን ዕዝን ነጻ ማውጣት ነበር፡፡ በዚህ መሠረትም ወንበዴዎች ወደ ሳህል በረሃ ተበተኑ፡፡

በደርግ ዘመነ መንግሥት የታወጀው የቀይ ኮከብ ዘመቻ ለምን ከሸፈ?

ከግብጽ እሰክ ሊቢያ ያሉ ሀገራት የውስጥ ኃይሎችን በመመሥረት እና በማጠናከር ለኢትዮጵያ አንድነት ስጋት ፈጥረው ነበር፡፡ ስለዚህ የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ ታወጀ፡፡ ዘመቻው በጣም ሰፊ ነበር፡፡ በወታደራዊው፣ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው እና ሌሎች ዘርፎች ዘመቻ በማድረግ ኤርትራን ለማሳደግ እና የሰሜኑን ችግር ለመፍታት በረጅም ጊዜ ዝግጅት የተደረገ ነበር፡፡

 

ነገር ግን ላለመሳካቱ ብዙ ችግሮችን መጥቀስ እንችላለን፡፡ አንዱ በጦር አሰላለፍ ላይ ችግር ነበር፡፡ ለጦርነቱ የተመመለመሉ ክፍለ ጦሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ 18ኛ፣ 19ኛ እና 20ኛ ክፍለ ጦሮች ለዚህ ነበር ተመለመሉት፤ አዲስ ምልምሎች የበረሃ ውጊያ ላይ መሳተፍ ሳይሆን ቀለል ያለ ግዳጅ ሊሰጣቸው ነበር የሚገባው፤ የበረሃ እና የረዥም ጊዜ የውጊያ ልምድ የሌላቸው ልጆች መኖራቸው ሳይጠና ቅድሚያ ወደ ጦርነቱ ገቡ፡፡

ሁለተኛው ሚስጥር ሾልኮ መውጣቱ ነው፡፡ በተለይ የውጊያችን ስትራቴጂ ሚስጥር አውሮፓ ውስጥ በጋዜጣ ታትሞ ነበር፡፡ ይህ ለሻቢያ እና ለሌሎች ኃይሎች እንዲጠቀሙበት ሆኗል፡፡ የቀይ ኮከብ ሁለገባዊ አብዮታዊ ዘመቻ ዋና ጸሐፊ አማኑኤል አምደሚካኤል የሚባሉ ሰው ናቸው አሾልከው ያወጡት ተብሎ ይገመታል፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እና በሙሉ ሚኒስትሮች እና አታሼዎች ኤርትራ ገብተው ጦርነቱን ለመጀመር ቤተ መንንግሥት ውስጥ ጉባኤ ይካሄዳል፡፡ የጦር አሰላለፍ እና የቦታ አጠቃቀም ጉዳይ በተመለከተ ማብራሪያ የሚሰጡ ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ የተጠቀሱት ሰው እጃቸውን አውጥተው ምንም ለውጥ እንዳይደረግ ሀሳብ ሰጡ፤ እቅዱ በጋዜጣ ታትሞ ካለቀ በኋላ ነው ይሄን ሀሳብ የሰጡት፡፡ “ጓድ ፕሬዝደንት፣ ጦርነቱ አልቋል” አሏቸው፡፡ “ሠራዊቱ ሽንቱን ቢሸና የሻዕብያ ሠራዊት በማዕበል ሱዳን ይገባል” አሏቸው፡፡ ከሱዳን ጋር ምንድን ነው በቀጣይ የሚደረገው የሚለው ብቻ ነው የሚያሳስበው አሉ፡፡ ጦርነቱ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ አልቋል አሏቸው፡፡

 

ከዚህ በኋላ እቅዳቸውን ሊያቀርቡ የነበሩት ጄነራሎቹ ማቅረብ ፈሩ፤ ሊቀርብ የነበረው ሀሳብ እና እቅድ ሳይቀርብ፣ ጥያቄ እና መልስ ሳይካሄድበት ቀረ፡፡ ሻዕብያ የተለየ ንድፍ ነድፎ አደጋ አደረሰ፡፡ ሻዕብያ እንዲህም ሆኖ ይመታ ስለነበር በጀርባ ወያኔን ልኮ የኢትዮጵያን ሠራዊት መትቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ሶሻሊዝም እየመነመነ፤ ሚዛን እያጣ አሜሪካ የበላይነት እየያዘች ሄደች፡፡ ሻዕብያ እና ወያኔ ተቀባይነት እያገኙ መጡ፡፡

ሦስተኛው ምክንያት ለሠራዊታችን ይመጣ የነበረው መሣሪያ ጊዜ ያለፈበት መሆኑ ነው፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርንት የተሠራ ነበር፡፡ ቀለም እየቀባ ነበር ጎርቫቾቭ (የወቅቱ የሶቪየት ሕብረት ፕሬዝደንት) የሚልክልን፡፡ የሚላከው ቢኤም እና ታንክ ተኩሶ ኢላማውን  በደንብ አይመታም ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ የነበራት ቅርጽ፣ ክብር እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት እንዲጠፋ ሆነ፡፡

 

በመጽሐፍዎ ባሕር ዳርን እንደ ሄሮሺማ ሲሉ አነጻጽረዋል፤ በወቅቱ የያዙት አቋም ነበረ፤ ክስተቱ ምንድን ነበር?

የፍጻሜው ጦርነት  የካቲት 1982 ዓ.ም ባሕር ዳርን እጅግ ነው የናጣት፡፡ ወያኔ ሆነ ብላ ከምትነዛው ስነ ልቦና ሰባሪ የሽብር ፕሮፖጋንዳ በላይ የመንግሥት ሠራዊት በፊናው አግድሞ ተበትኖ ነበር፡፡ ሀሳቡ በእነጀነራል አስራት በኩል ወደ እኛ የደረሰ ከደርግ ወታደራዊ ባለሥልጣናት የወረደ እንደሆነ የሚገመት አጀንዳ የባሕር ዳር ዴፖ ነዳጅ  ጉዳይ ነበር፡፡ በመኮድ ምሽግ ውስጥ ምስጢራዊ ስብሰባ ስናደርግ  አንዱ አጀንዳ ዴፖውን በከባድ መሣሪያ መምታት የሚል ነበር፡፡ ያን  ጊዜ ዴፖውን ለማቃጠል  ቢሞከር ከተማዋ እንደ ጥንታዊ ሮም በእሳት ትጋይ ነበር፡፡ ወደ ሁለት ሚሊየን ሊትር የሚደርሰውን ነዳጅ ወያኔ አንዳትጠቀምበት የታለመ ነው፡፡ ሌላኛው አማራጭ ተብሎ የመጣልን ደግሞ ነዳጁን ጣና ሐይቅ ውስጥ ማፍሰስ የሚል ነበር፡፡ ይህ መንገድ የሐይቁ ብዝኃ ሕይወት ላይ ጥፋት የሚያደርስ ነበር፡፡

 

ሁለቱንም እቅዶች ተቃውሜ ሀሳብ ሰጠሁ፤ “ባሕር ዳርን ስናቃጥል፣ ከባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ አምልጠን የምንወጣበት አጋጣሚ አይኖርም፤ ገና ለገና በጠላት ኃይል ተከበናል ብለን ከጠላት ያልተሻለ ውድመት በመፍጠር ይህችን ታዳጊ ከተማ ማውደም ተገቢ አይደለም” በማለት የራሴን የሕይወት አድን ሀሳብ ሰንዝሬያለሁ፡፡  በወቅቱ ጀነራል ዋሲሁን ደገፉኝ፡፡ በስተመጨረሻ ባሕር ዳርን እንደ ችቦ ለማቃጠል፣ እንደ ጭራሮ እንደነደዱት  የጃፓኖቹ ሂሮሺማ አና ናጋሳኪ ለማድረግ የቀረበው ሀሳብ ቀርቶ እኔ በምክንያት ያቀረብኩት ሀሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ባሕር ዳር ከመንደድ ድናለች፡፡ ነዳጁ ወደ ጣና ሐይቅ ይለቀቅ የሚለውንም ሀሳብ ለብዝኃ ሕይወት እና በንፋስ አማካኝነት በሚነሳ ቃጠሎ ሳቢያ ለነዋሪው እና ለከተማው ጎጂ መሆኑን በመጥቀስ እኔ፣ ጀነራል ዋሲሁን እና ጀነራል ኃይሌ በጽኑ ተቃወምን፡፡ ጦሩ ከባሕር ዳር ቢያፈገፍግ የተሻለ መሆኑንም በማንሳት ሁለተኛውንም የጥፋት እቅድ ሻርነው፡፡ ጣናን፣ በአቋማችን ባሕር ዳርን እና ሕዝቧን ከጥፋት ታድገናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነዳጁ ቢቃጠል ጦርነቱን እናሸንፍ ነበር፡፡

ከደርግ መንግሥት ከሥልጣን መውረድ በኋላ ሕይወትን እንዴት ገፉ፤ የአካባቢ ጥበቃውን እና በጎ አድራጎቱንስ እንዴት ጀመሩ?

ከ1983 ዓ.ም በኋላ የነበረው ጊዜ ከባድ ነበር፡፡ ከአሮራ፣ ከፖርት ሱዳን፣ ጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ ሰሜን ሸዋ ድረስ ሰው እና ኢኮኖሚ ደቆብን የነበረበት ጊዜ ነው፤ ኢትዮጵያ የነበራት የሰው፣ የቁስ እና የታሪክ ሀብት እንዲጠፋ ተደርጓል፤ እኔም ከፖለቲካ ሕይወት ወጣሁ፡፡

 

የተወለድኩት እብናት ውስጥ በሚገኝ ጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ ነው፡፡ በደርግ መንግሥት ውስጥ በኃላፊነት እያለሁ  ሶቪየት ሕብረት ሉቮቭ የምትባል ቦታ ሄድኩ፡፡ በስልጠናው ወቅት ጫካ አስጎበኙን፤ የተወለድኩባትን ቦታ ነው የሚመስለው፤ ሰውነቴን ወረረኝ፡፡ ይሄን እናንተ ነው እንዴ የተከላችሁት? መትከል ይቻላል? ብየ ጠየኩ፡፡ እብናት አካበቢ ስመለስ ያደኩበት ጫካ ተመንጥሯል፤ በጣም አዘንኩ፡፡ ከሶቪየት ያሁትን ተሞክሮ ይዤ ችግኝ መትከል ጀመርኩ፡፡ ባመጣሁት ውጤትም በኢትጵያ አና በአፍሪካ ደረጃ ተሸላሚ ሆኛለሁ፡፡

በአንድ ወቅት ከፕሮፌሰር አዱኛ ወርቁ ጋር ተገናኝትን ስንጨዋወት የበጎ አድራጎት ሥራ ሀሳብ መጣ፡፡ በዚሁ ጀመርነው፤ እሱ ገንዘብ ከአሜሪካ እያሰባሰብ ይልካል፤ እኛ በጎ አድርጎቱን እንሠራለን፡፡ በዚህ ሂደት ትምህርት ቤቶች ገንብተናል፣  ወፍጮ ተክለናል፣ የውኃ ቁፋሮ አካሂደናል፡፡ በአጠቃላይ ከ260 ሚሊዬን በላይ የሚያወጡ የበጎ አድራጎት ተግባራትን ሠርተናል፡፡

ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

ለተሰጠኝ ዕድል እኔም አመሰግናለሁ!

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here