በአዲሱ የትምህርት ዘመን የልጆች ዕቅድ

0
5

ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? እንኳን ለ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መጀመር በሰላም አደረሳችሁ!

ልጆችዬ! አዲሱ የትምህርት ዘመን ሲጀመር በምትገቡበት ክፍል ምን ምን ነገሮችን ለማስቀጠል እና ምንድን ችግሮችን ለማስተካከል ዕቅድ አወጣችሁ? ልጆች ለዚህ ሳምንት ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ለ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ያስቀመጡትን እቅድ ነግረውናል፡፡

ተማሪ ቅዱስ አለበል በዚህ በ2018 ዓ.ም የኤዲኤም አካዳሚ የ6ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኝ ነው፡፡ ልጆችዬ! ቅዱስ ከዚህ በፊት በክፍል ደረጃ ለመያዝ ያጠናበት የነበረውን ስልት ቀይሮ ለሀገር አቀፍ ፈተና ተወዳዳሪ በሚሆንበት መልኩ ለመዘጋጀት ነው ያቀደው፡፡ የባለፈው ዓመት የእንግሊዘኛ ትምህርት ውጤቱን ከባለፈው ዓመት ከፍ ለማድረግ ከጓደኞቹ ጋር በጋራ የማጥናት ፕሮግራምም አውጥቷል፡፡

ሌላዋ ደግሞ ፍሬህይወት አበበ በደቡብ ጎንደር እብናት ወረዳ ነው የምትኖረው፡፡ በእብናት ወረዳ  አምቦ መስክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ናት፡፡በዚህ በያዝነው 2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን 4ኛ ክፍል ተማሪ ትሆናለች፡፡ ፍሬህይወት ከምትማረው የትምህርት አይነት እንግሊዘኛ ትምህርት በጣም ከብዷት እንደነበር ገልፃልናለች፤ የሳይንስ ትምህርት ደግሞ በቀጣይ ስትማረው እንደሚከብዳት በማሰብ የጥናት ሁኔታዋን ለማስተካከል አቅዳለች፡፡ እንግሊዘኛ እና ሳይንስ ጎበዝ የሆኑ ታላላቆቿን እንዲያግዟት በመጠየቅ ወጤት እና ደረጃዋን ለማሻሻል ነው ትልቁ እቅዷ፡፡

በረከት ቅዱስ ደግሞ ያለፈው አመት ቁልቋል ሜዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 6ኛ ክፍል ተማሪ ነበር፤ ሀገር አቀፍ ፈተናውን በመካከለኛ ውጤት አልፏል፡፡ በዚህ ዓመት ግን ብዙውን ጊዜውን በትምህርት እንዲያሳልፍ በማሰብ እና በትምህርቱ ከባለፈው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ቤተሰቦቹ ወደ ግል ትምህርት ቤት ስላዛወሩት ቀሪውን ጊዜ በምን መልኩ ማጥናት እንደሚገባው ዝግጅት አድርጓል፡፡

ተረት

አነጋገር ያተርፋል

በድሮ ጊዜ በአንድ መንደር የሚኖር አንድ ንጉስ ነበር። አንድ ቀን ንጉሱ በህልሙ ጥርሶቹ ሁሉ ሲረግፉ ያያል፡፡ በዚህ ጊዜ ህልም የሚፈታለት ሰው በሀገሩ ፈልጎ  ያስጠራና ህልሙን ይናገራል፡፡ ህልም ፈቺውም በመገረም…”ይህን ህልም ያየኸው አንተ ነህ? እርግጠኛ ነህ ሲል ይጠይቀዋል። ንጉሱም አዎ እኔ ነኝ ይለዋል። ህልም ፈችውም “ቤተሰቦችህ በሙሉ በፊት ለፊትህ አይንህ እያየ ይሞታሉ” ብሎ ፍችውን ይነግረዋል ፤ በዚህ ጊዜ ንጉሱ ተቆጣ…”ይሄን ቀባጣሪ እስር ቤት ወርውሩልኝ” ሲል አዘዘ። ትዕዛዙም ተግባራዊ ሆነ። ሌላ ህልም ፈቺ ተፈልጎ ይመጣና ሲነገረው ፍችው የመጀመሪያው አይነት በመሆኑ ንጉሱ ተበሳጩ፤ እሱንም ወደ እስር ላከው፡፡ ሶስተኛ ህልም ፈቺ ተጠራ፤ እንደተለመደው ንጉሱ ህልሙን ተናገረ፡፡ “ንጉስ ሆይ እርግጠኛ ነህ? አንተ ነህ ያየኸው”…በማለት ጠየቀው። ንጉሱም አዎን ምነው?”….ሲል አትኩሮ ተመለከተው “እንኳን ደስ አለህ”…በማለት ተናገረ። ለምኑ..ሲል ንጉሱ ጠየቀ።  “የዚህ ህልም ፍቺ ከቤተሰቦችህ  ሁሉ ረዥም እድሜ የምትኖረው አንተ መሆንህን ነው። እናም እንኳን ደስ አለህ በማለት በደስታ ተናገረ። በዚህ ጊዜ ንጉሱ ተደሰተ.. .ለህልም ፈቺውም ስጦታ በመስጠት በክብር አሰናበተው፡፡

የንጉሱ እድሜ ከቤተሰቡ በለጠ ማለት ቤተሰቦቹ ቀድመውት ይሞታሉ ማለት አይደለምን? ሆኖም ግን ሀሳቡ አንድ ሆኖ ሳለ የንግግር ስልት መለያየት ሊያናድድ እና ሊያስደስት ስለሚችል ሦስተኛው ህልም ፈቺ በአነጋገሩ ስልት ተረፈ ይባላል።

ምንጭ-ኢትዮጵያ ተረቶች

ሞክሩ

  1. የውሃ ኬሚካላዊ ምልክት ምንድነው ?
  2. በዓለም ላይ ትንሹ ወፍ ምንድን ነው?
  3. በሰው አካል ውስጥ ትልቁ አካል ምንድን ነው?

መልስ

  1. H2O
  2. ንብ ሀሚንግበርድ
  3. ቆዳው

 

ነገር በምሳሌ

-ሁሉ አማረኝን ገበያ አታውጣት፡፡

ፍላጎትን በልኩ ማድረግ ጥሩ ነው።

– ሀብት የጠዋት ጤዛ ነው፡፡ የሃብት መኖር ቋሚ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው።

–  ተቀመጥ በወንበሬ ተናገር በከንፈሬ፡፡  እንደኔ ሁነህ ተናገርልኝ፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here