የጭንቅላት እና የአንገት ካንሰር (ነቀርሳ)ን ምልክቶቹ ታይተው ከመስፋፋቱ ከ10 ዓመታት አስቀድሞ በሚደረግ ጥልቅ የደም ምርመራ ማወቅ መቻሉን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል፡፡
በአሜሪካ የማሳቹሴት ጠቅላላ ሆስፒታል ተመራማሪዎች የጭንቅላት እና የአንገት “ካንሰር”የሚያስከትለውን “ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ” ከአስር ዓመታት አስቀድሞ በሚደረግ ጥልቅ ምርመራ ማወቅ ችለዋል፡፡
አዲሱ ግኝት ቀደም ብሎ የነበሩ የካንሰር ምርመራዎችን እና የህክምና ስልቶችን ሊቀይር ይችላልም ተብሏል፡፡
እስካአሁን የጭንቅላት እና የአንገት ካንሰር የሚያመጣውን “ኤች ፒ ቫይረስ” ለመለየት የሚያስችል ምንም ዓይነት ምርመራ አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ቫይረሱ በሚሊዬን ከተበዛ እና ወደ “ሊንፍኖድ” ከተሰራጨ በኋላ ህሙማን ወደ ህክምና ተቋማት እንደሚሄዱ ተመራማሪዎቹ አመላክተዋል፡፡
ተመራማሪዎቹ በአዲሱ ሙከራቸው ለካንሰር የሚያበቃውን መንስኤ ቀደም ብለው ለማወቅ የሚያስችል ስልት መዘየድ ለህክምናው የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ አምነው የናሙና ምርመራ እና ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡
በዚህም 56 የደም ናሙናዎችን ለአዲሱ ምርምር መነሻ አድረገው ተጠቅመዋል፡፡ 28ቱ የአንገት እና የጭንቅላት ካንሰር ካጋጠማቸው ቀሪዎቹ 28ቱ ናሙናዎች ደግሞ የካንሰር ቫይረስ ካልተገኘባቸው የተሰበሰቡ ናቸው፡፡
“ኤች ፒቪ- ዲፕ ሲክ “በተሰኘው ምርመራም ከሰባት ነጥብ ስምንት ዓመታት በፊት ከተሰበሰቡ የፈሳሽ ናሙናዎች ከ28ቱ 27ቱ በትክክል ለካንሰር መጋለጣቸውን መገንዘብ ችለዋል፡፡ ቀሪዎቹ የካንሰር ህመም ካልታየባቸው የተወሰደው ናሙና ፈሳሽ ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
በመጨረሻም ከዓመታት በፊት ቀደም ብሎ በሚደረግ የደም ናሙና ጥልቅ ምርመራ የካንሰር ቅንጣቶችን ማወቅ እና መገንዘብ መቻል ህመሙ ከመጀመሩ አስቀድሞ የታካሚውን ውጤት እና የህይወት ጥራት ማሻሻል እንደሚያስችል ነው ያደማደሙት- ተመራማሪዎቹ፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


