በአፍሪካ በውኃ ግፊት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ከኃይል ማግኛ አማራጮች ተመራጩ እና ቀዳሚው ነው:: አንዳንድ ሀገራት ደግሞ ከቅሪት አካል ከሚገኝ ነዳጅ እና ከፀሐይ እና ከእንፋሎት በሚገኝ ኃይል ላይ እንደተመረኮዙ ናቸው::
ሀገራት ከብክለት ነፃ በሆነ የኃይል አማራጭ ላይ መመስረት እንደሚኖርባቸው ታምኖበት በዓለም አቀፍ ደረጃ ግብ ተጥሎ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው ፤ብክለትን ዜሮ ለማድረስ::
በአህጉራችን አፍሪካ በውኃ ግፊት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ቀዳሚዎቹን አሥር ግድቦች እንመልከት፤
10 . መገኛ ሀገር – ናይጀሪያ
የግድቡ መጠሪያ – ካይንጂ ግድብ
የሚያመነጨው የኃይል መጠን- 760 ሜጋዋት
ግድቡ በሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ገጠሩን በማዳረስ የኢንዱስትሪ እድገትን ያመጣል በሚል ታመኖበት ነበር የተሠራው:: ይሁን እንጂ፣ “በተርባይን” ወይም በመቅዘፊያ ችግር፣ በጥገና እጦት እና በደለል መሞላት ከአቅም በታች አገልግሎት እየሰጠ ነው::
- መገኛ ሀገር – ጋና
የግድቡ መጠሪያ – አኮሶምቦ ግድብ
የሚያመነጨው የኃይል መጠን -1020 ሜጋዋት
የጋናው ኦኮሶምቦ ግድብ በቮልታ ወንዝ ላይ በ1965 ተገንብቶ የተጠናቀቀ ነው:: ግድቡ በዓለማችን ትልቁን ሰው ሠራሽ ሐይቅ የቮልታ ሐይቅን አስገኝቷል::
ከግድቡ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ለሀገር ውስጥ እንዱስትሪዎች የብረት ፋብሪካን ለመሳሰሉት የኃይል ምንጭ ሆኗል:: በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ለቤኒን እና ቶጐ ጐረቤት ሀገራትም አገልግሏል::
- መገኛ ሀገር ኢትዮጵያ
የግድቡ መጠሪያ – ተከዜ ግድብ
የሚያመነጨው የኃይል መጠን – 1 ሺህ 200 ሜጋ ዋት
በ2009 እ.አ.አ በተከዜ ወንዝ ላይ የተገነባ ባለ ድርብ ቅስት ግድብ ነው::
ግድቡ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ቀጣና በተነሳው ግጭት ፈተና ቢገጥመውም የኢትዮጵያን የልማት እቅድ በመደገፍ ላይ ይገኛል::
- መገኛ ሀገር – ሱዳን
የግድቡ መጠሪያ – ሜሮዌ ግድብ
የሚያመነጨው የኃይል መጠን – 1 ሺህ 250 ሜጋዋት
በሀገሪቱ ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ነው፤ በዓባይ ወንዝ ላይ ነው የተሠራው::
በ2009 እ.አ.አ ሥራው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል:: ለሀገሪቱ ብሔራዊ የኃይል ቋት ከፍተኛ መጠንም ያበረክታል:: በወንዙ ዳር ላሉ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭቶ ከግድቡ በሚለቀቅ ውኃ ለመስኖ ልማት ውሏል::
ግድቡ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት የተገነባው ሀገሪቱ ከቅሪት አካል ነዳጅ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ መሆኑም ተጠቅሷል::
- መገኛ ሀገር – ዛምቢያ፣ ዚምባቡዌ
የግድቡ መጠሪያ – ካሪባ ግድብ
የሚያመነጨው የኃይል መጠን – 1 ሺህ 626 ሜጋዋት
በዛምቢያ እና ዚምባቡዌ መካከል ባለው የዛምቤዚ ወንዝ ላይ የተገነባ ድንበር ተሻጋሪ ትብብርን የሚያሳይ ነው፤ ካሪባ ግድብ:: ለሁለት ሀገራት የኃይል ምንጭ ሆኖም ያገለግላል::
ለዚምባቡዌም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመሰረተ ልማት ማከፋፈያ እና የውኃ መጠን መቀነስ ቢገጥማትም ወሳኝ ዓቅም ሆኖ ቀጥሏል::
- መገኛ ሀገር- ኮንጐ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ
የግድቡ መጠሪያ- የኢንጋ ግድቦች
የሚያመነጩት የኃይል መጠን- 1 ሺህ 775 ሜጋዋት
የኢንጋ ግድቦች በኮንጐ ወንዝ ላይ የሚገኙ ሁለት ትልልቅ ግድቦችን ያካተተ ነው::
ተስፋ ሰጪ የኢሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ተብሎም ነው የሚታሰበው:: በግድቡ ላይ ሌላ ሦስተኛ “ግራንድ ኢንጋ” የተሰኘ ግድብ ለመገንባት ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል፤ በፖለቲካ አለመረጋጋት እና በገንዘብ እጥረት እውን ሳይሆን ቢቀርም::
- መገኛ ሀገር- ኢትዮጵያ
የግድቡ መጠሪያ – ግልገል ጊቤ ሦስት ግድብ
የሚያመነጨው የኃይል መጠን -1 ሺህ 870 ሜጋዋት
ግድቡ በኢትዮጵያ በትልቅነቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል:: በኦሞ ወንዝ ላይ በ2016 እ.አ.አ ተገንብቶ የተጠናቀቀ ነው:: የግድቡ ግንባታ ሀገሪቱ በአፍሪካ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለቤት ለመሆን ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ልብ ይሏል::
- መገኛ ሀገር – ሞዛምቢክ
የግድቡ መጠሪያ – ካሆራ ባሳግድብ
የሚያመነጨው የኃይል መጠን -2 ሺህ 070 ሜጋዋት
ከደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ቀደም ብሎ በዛምቤዚ ወንዝ ላይ የተገነባ ግድብ ነው:: ሞዛምቢክ ከግድቡ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለደቡብ አፍሪካ በመሸጥም የምጣኔ ሀብቷን ትደጉማለች::
- መገኛ ሀገር – ግብፅ
የግድቡ መጠሪያ – አስዋን ግድብ
የሚያመነጨው የኃይል መጠን- 2 ሺህ 100 ሜጋ ዋት
የአስዋን ግድብ በ1970 እ.አ.አ ነው ግንባታው የተጠናቀቀው:: ግድቡ ከኃይል ማመንጫነት ባለፈ አገሪቱ በመስኖ የእርሻ መሬቷን እንድታለማ አስችሏታል:: ግድቡ በዓለም ላይ ካሉት ትልልቅ የውኃ ማጠራቀሚያዎች አንዱ ለመሆን በቅቷል፤ የናስር ሐይቅን ፈጥሮ:: ግድቡ የሀገሪቱ የጥንካሬ ተምሳሌት ነው::
- መገኛ ሀገር ኢትዮጵያ
የግድቡ መጠሪያ – ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ
የሚያመነጨው የኃይል መጠን – 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት
በዓባይ ወንዝ ላይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2011 እ.አ.አ ግንባታው ተጀምሮ በ2025 እ.አ.አ የጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል:: ኢትዮጵያ ግንባታውን አጠናቃ ኃይል መስጠት ሲጀምር ለሀገር ውስጥ፣ ጐረቤት ሀገራትን እና ሰሜን አፍሪካን በማድረስ ቀዳሚ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለቤት ያደርጋታል::
ምንጭ፡- አፍሪካን ኤክስፓነንት ድረገጽ
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጳጉሜን 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም