በኢትዮጵያ ሊፈጠር ይችላል የተባለዉ ውቅያኖስ

0
53

በኢትዮጵያ በአፋር ክልል በሚገኘው “ኤርታአሌ” የቀለጠ አለት ስር በሚገኘው የመካከለኛው የመሬት ክፍል (መንትል)እየሳሳ ስንጥቃትን አስከትሎ አዲስ ውቅያኖስ ሊፈጠር እንደሚችል ላይቭ ሳይንስ ድረገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል::

በሳውዝሃምኘተን ዩኒቨርሲቲ የምድር ተመራማሪዎች ቡድን ከጥልቅ መሀከለኛው የመሬት ክፍል ወደ ላይኛው (ክረስት) የሚወጣው የቀለጠ አለት ምቱ (ንዝረቱ) እየጨመረ መምጣቱን የሚያመላክት ማስረጃ አግኝቷል::

በአፋር ክልል የ”ኤርታአሌ” ንቁ እሳተ ገመራ ቅላጩ ወደ ውጪ እየፈሰሰ መሆኑንም ነው አረጋግጠዋል- ተመራማሪዎቹ:: ቀጣናው ማለትም የአፋር ምድር ሶስት የ  “ቴክቶኒክ” የውስጠኛው የመሬት ክፍል  የኢትዮጵያ ስምጥ ሽለቆ የቀይባህር እና የኤደን ባህረሰላጤ መገጣጠሚያ ብርቅዬ ቦታ መሆኑም ነው የተጠቆመው::

የምድር ውስጥ ተመራማሪዎቹ ሲከታተሉ የቆዩት የቀለጠ አለት   ከስር ምቱ በመጨመሩ ወደፊት አዲስ ውቅያኖስ መፈጠርን ሊያስከትል ይችላል የሚል ጠንካራ እምነታቸውን አብስረዋል:: ለዚህም  ቡድኑ  ከየቀጣናው 130 የእሳተገሞራ ቅላጭ አለት ናሙና መሰብሰቡን ነው በማስረጃነት ያሰፈረው::

ቡድኑ ከሰበሰባቸው ናሙና ከስር የቀለጠው አለት ወደ ላይ እየተገፋ በሚያገኘው ስንጥቃት በዙሪያው ካለ ውኃ ክፍተቱ ተሞልቶ አዲስ ውቅያኖስ ሊፈጠር እንደሚችል ነው ያረጋገጡት::

በተጨማሪም በአፋር ስምጥ ሸለቆ የሚገኘው የቀለጠ የአለት ስር ንቅናቄ የማይቆም  መሆኑን እና በሚፈጠሩ ስንጥቃት መካከል ሊከሰት የሚችለውን ሁነት መረዳታቸውን ነው ተመራማሪዎቹ ያሰመሩበት::

በአጥኚ ቡድኑ ውስጥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የሳውዝ ሃምፕተን ዩኒቨርሲቲ፣ የስዋንሲ ዩኒቨርሲቲ፣ የላንካስተር ዩኒቨርሲቲ እና ፒሳ ዩኒቨርስቲ፣ የጀርመን ጂኦማር፣ የደብሊን ከፍተኛ ጥናት ተቋም፣  የመሳሰሉ በአጠቃላይ ከ10 ተቋማት የተውጣጡ ባለሞያዎች መኖራቸው ተብራርቷል::

ከተቋማት የተውጣጡት ባለሙያዎች ነባር እና ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ እውነታዎችን ለመረዳት በምስለ ሙከራዎች ለድምዳሜ የሚያደርሱ ማስረጃ እና ውጤቶችን መቀመር ችለዋል:: የመሬት የውስጥ ቅርፊት ወይም ንጣፎች ውፍረታቸው የሚለያይ በመሆኑ በምን ያህል ፍጥነት ሊከሰት ወይም ውቅያኖሱ ሊፈጠር እንደሚችል ቁርጥ አድርጐ መናገር አስቸጋሪ መሆኑንም ጠቁመዋል::

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ላይቭሳይንስ፣ ሳይንስ ደይሊ እና ኒውሰር ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here