ኢንስትራክተር አድማሱ ፈንታ (እያያ ቦክስ) ይባላሉ። በቦክስ ስፖርት ተጫዋችነት፣ በአሰልጣኝነት እንዲሁም እስከ ኢንስትራክተርነት የደረሱ የሀገር ባለውለታ ናቸው።
በትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ትልቅ አሻራ ያላቸው የሀገር ባለውለታ ናቸው። የአማራ ክልል ቦክስ ፌደሬሸን ፕሬዘዳንት በመሆን በኢትዮጵያ ዉስጥ ካሉ የምርጦች ምርጥ 10 ኢንተርናሺናል የቦክስ አሰልጣኞች ዉስጥ አንዱ ናቸው። ብዙ ወጣቶችን ለክለቦች በማስመረጥና ብሔራዊ ቡድን ድረስ በማድረስ ጀግና የስፖርትና የሀገራዊ ልማት አርበኛ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። በኩር እንግዳ አድርጋቸዋለች።
ኢንስትራክተር አድማሱ ፋንታ ማን ናቸው? በምን አይነት ቤተሰብ ውስጥ አደጉ?
የተወለድኩት ባህር ዳር ቀበሌ 04 ነው። በተለምዶ ሽንኩርት ሰፈር ውስጥ ቤተሰቦቼ በኪራይ ቤት እያሉ ነበር የተወለድኩት። ነገር ግን እዚያው ቀበሌ ውስጥ ቤት ሰርተው መኖር ጀመሩ ። አንድ ቤት ውስጥ የእኛ ቤተሰብ እና የአባቴ ታናሽ ወንድም ቤተሰብ በጋራ እንኖር ነበር። አባቴና አጎቴ በጣም ከመዋደዳቸው የተነሳ አንድ ቤት ውስጥ አብረው በመኖር በፍቅር አሳድገውናል። ከመልካም ቤተሰብ ውስጥ ነው የወጣሁት። አባቴ ጥሩ ስነምግባር ይዤ እንዳድግ እየቀጣ፣ እየመከረ እና መስመር እያስያዘ አሳድጎኛል።
አጎቴ አቶ ልብሴ ምህረቱ ወታደር ቀመስ በመሆኑ እኔን ገና ከሦስት እስከ አራት ባለው እድሜየ ጀምሮ ቀለል ያለ ስፖርት ያሰራኝ ስለነበር የስፖርትን ፍቅር ገና በለጋው ልቤ ውስጥ ተከለብኝ። በአጭሩ ከቤተሰቤ መልካምነትን፣ ፍቅርን እና ስፖርትን ተምሬ አድጌያለሁ።
የቦክስ ስፖርት በተጫዋችነትም በአሰልጣኝነትም ትልቅ አሻራ ያሳረፉ እንደሆኑ ይነገራል፣ እስኪ በስፖርት ሕይወትዎ ዙሪያ ያጫውቱን?
ቀደም ሲል እንደተናገርኩት ስፖርትን የተማርኩት መጀመሪያ ከቤተሰቤ ውስጥ ነው። አጎቴ ከልጅነት ጀምሮ ስፖርት እያሰራ ለስፖርት ፍቅር እንዲያድርብኝ አድርጓል። ሲቀጥል ሰው አካባቢውን ጎረቤቱን ይመስላል ነውና ከጎረቤታችን ተስፋሁን አያልነህ የሚባል ወጣት በክብደት የዳበሩ ጡንቻዎች እና የጥሩ ስነምግባርና ባህሪ ጌታ መሆኑ እኔ በልጅነቴ ልክ እንደ እርሱ ለመሆን አብሬው ስፖርት መስራት እንደምፈልግ ስጠይቀው እርሱም በደስታ ክብደት በማንሳት የሠውነቴን የጡንቻ ክፍሎችን እንዳዳብር ስፖርታዊ ስልጠናዎችን በመስጠት በቦክስ ስፖርት የተሻለ ቦታ ለመድረስ ጥሩ መነሻ እና መሠረት ሆነኝ።
ክብደት እያነሳን የተለያዩ የአክሽን ፊልሞችንም እናይ ነበር። እንደ ቢግ ዳዲ ፣ ብሩስሊ የመሳሰሉ በዘመኑ እውቅ አክተሮች ያሉበትን ፊልም እያየን እንደ እነርሱ ለመሆን እንሠራ ነበር። አሸዋ ሞልተን እንደበድብ ነበር። እንዳሁኑ ጊዜ ዘመናዊ ጂምናዚየሞች ባልተስፋፉበት በተለምዶ ቤት ውስጥ በምንሠራቸው የስፖርት ቁሳቁሶች እየተጠቀምን ሰውነታችንን እናስተካክል ነበር።
ጥሩ ስፖርተኛ የመሆን የልጅነት እምነቴ ወደ ስኬቱ የመጀመሪያ ምእራፍ የመጣው በ1985 ዓ.ም ነበር። በዚህ ወቅት የአማራ ክልል መንግሥት ስፖርተኞችን ለማሰልጠን ማስታወቂያ ያወጣል። እናም የስፖርት ፍላጎቴን እና የቡጢ ስፖርት ፍላጎቴን፣ የአካሌን በስፖርት መዳበር የሚያውቁ የሰፈር ሰዎች ሄጄ እንድመዘገብ ነገሩኝ። የሚያልፈኝ ሁሉ መስሎ ስለተሰማኝ ወዲያው ተጣድፌ በመሄድ ተመዘገብኩ። ያኔ በቃ የስኬት ጣሪያውን የደረስኩ ያህል ነበር ደስታ የተሰማኝ።
የቦክስ ስፖርት ስልጠናውን 1985 ዓ.ም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስፖርት ጽ/ቤት ምዝገባውን አድርጎ ስልጠናውን ከኩባ በመጣ የቀድሞ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ በነበረ ምርጥ አሠልጣኝ በማስተር ወንድወሠን ብርሃኑ ጥሩ የቦክስ ስፖርተኛ ለመሆን የሚያበቁ ሙሉ ሥልጠናዎችን ወሰድን። ከዚህ በኋላ ምዕራብ ጎጃምን እና ባህርዳር ልዩ ዞንን እንዲሁም የአማራ ክልልን በመወከል በኢንስትራክተር አብርሃም አበበ እና በኮሎኔል ወርቁ ገሠሠ አሠልጣኝነት ከ1986 እስከ 1993 ዓ.ም በተለያዩ ዞኖች ባህርዳር ከተማን እና ክልሉን በመወከል ጥሩ ውጤት አስመዝግቤያለሁ። ሆኖም በ1993 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቻምፒዮን ውድድር ላይ ክልሉን ወክየ በ54 ኪሎ ግራም ለመወዳደር ጎንደር ከተማ ላይ በተካሄደው የዞኖች ቻምፒዮን ውድድር ላይ ሁለት ማጣሪያዎችን አሸንፌያለሁ ሦስተኛውን ለወርቅ እና ለብር ፋይናል ውድድር ላይ እያለሁ ቀኝ እጄን ስለተጎዳሁ ውድድሩን ሳልጨርስ ለማቋረጥ ተገደድኩ። ከዚያም በኋላ በእጄ ላይ በደረሠብኝ ጉዳት ተነስቼ በእኔ ያልተሳካውን ሀገሬን ኢትዮጵያን ወክየ ኦሎምፒክ ላይ የመድረስ እና ወርቅ መዳሊያ የማምጣት ዕቅዴን በማሠለጥናቸው ታዳጊ የቦክስ ስፖርተኞች የተሻለ ውጤት ለማምጣተት የሁልጊዜ ህልሜ ሆኖ የበኩሌን ጥረት በማድረግ ላይ እገኛለሁ። በአሁኑ ወቅት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ቦክስ ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ስሆን በኢትዮጵያ ካሉ ምርጥ 10 ሰከንድ ስታር ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተሮች መካከል አንዱ ነኝ።
ከሁሉም ክልሎች እና ከአዲስ አበባ ከተማ ካሉ የክለብ ቦክስ ስፖርት አሠልጣኞች ጋር የ ፊርስት ስታር ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ሥልጠና ላይ የተሻለ ውጤት ካመጡ 15 ምርጥ አሠልጣኞች ውስጥ አንዱ ነኝ። ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ አስራ አምስቱ ፈርስት ስታር ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተሮች ለተሻለ ሙያዊ ሥልጣና ለ ሰከንድ ስታር ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ስልጠና ዕድሉን አግኝቶ ስልጠናውን ከወሠደ በኋላ በጥሩ ውጤት ካለፉ 10 ምርጥ የቦክስ ስፖርት አሠልጣኞች ውስጥ አንዱ ከመሆኑም በላይ ሙያዊ ሥልጠናዎችን ለቦክስ ሰፖርተኞች ብቻ ሳይሆን ስፖርቱን ለሚወዱና ስልጠና ለሚፈልጉ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ዕድሜ እና ፆታ ሳይለይ በየቀበሌው ባሉበት ቦታ የቦክስ ስፖርትን ለማሳደግ ሁሌም የምችለውን ሁሉ ጥረት አደርጋለሁ።
ከዚህ ጎን ለጎንም ትምህርት ቀጥየ በ2001 ዓ.ም ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በስፖርት የመጀመሪያ ድግሪየን አግኝቼ በዘርፉ ያለኝን እውቀት ለማሳደግ ሞክሬያለሁ።
የባሕርዳር ወጣቶችን በስፖርት ገምብቶ ብቁ ጤናማና በስነምግባር የታነፁ ጨዋ እንዲሆኑ በማድረግ ብዙ ከሰሯቸው በጥቂቱ ያጫውቱን?
ውድድር ካቆምኩ በኋላ ወጣቶችን ከታዳጊ ጀምሮ እያሰባሰብኩ አሰለጥን ገባሁ። በየቀበሌው ያሉ ወጣቶችን ከያሉበት በመሄድ እንዲሁም በቴዎድሮስ ስታዲየም እየወሰድኩ አሰለጥናለሁ። ጥዋት ማታ እሰራለሁ። ደከመኝ ሰለቸኝ አልልም።
ስፖርተኞችን ማፍራት እፈልጋለሁ። በእኔ ያልተሳካውን ህልሜን በሌሎች ስፖርተኞች ተሳክቶ ማየት እፈልጋለሁ። እና በተለያዩ ደረጃዎች በሴትም በወንድም ጥሩ ጥሩ ውጤት ያመጡ ስሜን ማስጠራት የቻሉ ስፖርተኞችን ማፍራት ችያለሁ። ደመወዝ እየተከፈለኝ ሳይሆን ለስፖርቱ ካለኝ ፍቅር የተነሳ በነፃ ነው የማሰለጥነው። ደመወዜ የሰው ሀብት ነው፣ ሰዎች በአካል ተገንብተው፣ ጤነኛ እና በጥሩ ስነ ምግባር የተገነቡ ሰዎች ሆነው ማየት ነው። ብዙ ወጣቶችን ከሱስ እያወጣሁ ብቁ ስፖርተኞች በማድረግ ለትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ የበኩሌን ሰርቻለሁ፤ ወደፊትም እሰራለሁ።
ከዚያ በተጨማሪ ባሕር ዳር የአባይ ድልድይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሳለሁ ከሥራው ጎን ለጎን ስፖርት አሰለጥን ነበር። ብዙ በሱስ ተጠምደው ወደ ማያስፈልግ መስመር የገቡ ወጣቶችን ከዚያ ሕይወት ወጥተው ለራሳቸው አልፈው ለሰው የሚተርፉ እንዲሆኑ በፕሮጀክቱ እንዲቀጠሩ አደርግ ነበር። የሀብታም ልጆች ሆነው እንኳ የቤት እቃ ሁሉ እያወጡ የሚሸጡ ነበሩ። እና ወላጆቻቸው እየደወሉ እባክህን ሰው አዋዋሉን ይመስላል እና ከአንተ ጋር ወስደህ አውላቸው ይሉኝ ነበር። እኔም ተሯሩጬ አለቆቼንም አስፈቅጄ አስቀጥራቸውና እነርሱን ለመቅረጽ ልዩ ክትትል አደርግላቸው ነበር። እንደ ወንድም ከገዛ ኪሴ እያወጣሁ እንከባከባቸዋለሁ። ስርቆት በፍፁም እክዳይፈፅሙ መክሬ ብዙዎችን መልሻለሁ። በዚህ ደስ ይለኛል። እነርሱ ተለውጠው እኔን ሲያመሰግኑ ሳይ የህሊና እርካታን አገኛለሁ።
በትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በተለያዩ ሀላፊነቶች እንደተሳተፉ ስለእርስዎ በቅርበት የሚያውቁ ሰዎች ነግረውናል፤ እስኪ በዚህ ዙሪያ ያጫውቱን።
አባቴ በልጅነቴ “ዝቅ ካልተባለ ከፍ አይባልም። ስራን ዝቅ ብለህ ከጀመርክ አልፈህ ትሄዳለህ። ስራውን ከታች ከመሰረቱ እያወቅኸው በራስህ እየተማመንክ ስትመጣ ትርፋማ ትሆናለህ። ስለዚህ ከአንድ ድርጅትም ሆነ ከአንድ ተቋራጭ ገብተህ በጉልበት ስራም ቢሆን ከታች ተነሳ። የማይገባህን አትጠይቅ” እያለ ይመክረኝ ነበር። ይህን በልቤ ይዤ ከጣና በለስ ሱሉልታ ሰብ ስቴሽን ድረስ የ400 ኬቪ የመብራት መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ላይ በጉልበት ስራ ለመቀጠር ጥያቄ አቀረብኩ። ኃላፊው ግን ካለኝ አለባበስ እና ፈርጣማ ተክለ ሰውነት አንፃር እያሾፍኩ ነበር የመሰለው። ሌላ ተንኮልም ይዤ የመጣሁ ያህልም ተሰማው። ባይሆን በፎርማንነት እንድትሰራ ልቅጠርህ አለኝ። እኔ ግን የአባቴን በልቤ ታትሞ የቀረውን ምክር ነግሬው፣ ዝቅ ብየ ጀምሬ ስራውን እያወቅሁት ማደግ እንደምፈልግ ስነግረው ተገርሞ ቀጠረኝ። ከስምንት ወር በኋላም ጄኔራል ፎርማን እንድሆን ተደረገ።
ከሦሥት ዓመታት በኋላ ይህንን ፕሮጀክት በሚገባ አጠናቀቅን። ፕሮጀክቱ እንዳለቀ ከጣና በለስ ሰብ-ስቴሺን እስከ ህዳሴ ግድብ የመብራት ፓወር ዝርጋታና ፋዉንዴሺን የመስራት አዲስ ፕሮጀክት የሻንጋይ ኤሌክትሪክ ካምፓኒ ውል ወሰደ። በመጀመሪያው ፕሮጀክት ወቅት የነበረኝ እንቅስቃሴ እምነት ስላሳደረባቸው ዋና ስራ አስኪያጅ እንድሆን በመሾም ከፍ አደረጉኝ። ኃላፊነቴን በላቀ ትጋት እና መግባባት በስኬት አጠናቀቅሁ። በመቀጠልም ከጊቤ 2 ወላይታ ሶዶ መብራት ታወር ዝርጋታና ፋዉንዴሺን፣ ከዚያም ከገላን ስብስቴሺን ግቤ 3 መብራት ታወር ዝርጋታና ፋዉንዴሽን፣ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታን፣ የወልቃይት ጠገዴን የመብራት ዝርጋታ፣ ከግቤ 3 ኮይሻ መብራት ታወር ዝርጋታና ፋዉንዴሺን በመሳሰሉ በርካታ ፕሮጀክቶች ላይ በዋና ስራ አስኪያጅነት ሰርቻለሁ።
በሌላ በኩል በባህር ዳር የተገነባውን በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ በሆነው የአባይ ወንዝ ድልድይ ፕሮጀክት ላይ በዋና ስራ አስኪያጅነት ሰርቻለሁ። ከቀደሙት የስራ ልምዴ አንፃር የቻይንኛ ቄንቋን ስለምችል አስተረጉምላቸው ነበር። የስራ ደህንነቱን ጉዳይ በማስጠበቅ፣ የተለያዩ ችግሮች እንዳይፈጠሩ፣ ስርቆት እንዳይፈጸም እና ስራው እንዲቀለጥፍ የበኩሌን ሚና ተጫውቻለሁ።
በእነዚህ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ሁሉ ከቻይናዎቹ ጋር በቋንቋም በባህሪም ተግባብቼ ሰርቻለሁ። ቻይናዎቹ ስራየን አክብሬ መስራቴን፣ ቅልጥፍናየን እና ታማኝነቴን ስለሚያውቁ ትልቅ አመኔታ አሳድረውብኛል። ሰራተኞች ስራውን እስኪለምዱ እና አቅም መገንባት እስኪችሉ ድረስ በምክርም ከኪሴም አንዳምድ ድጋፍ አደርግላቸውና አለማምዳቸው ነበር።
በ14 ዓመታት ከሻንጋይ ኤሌክትሪክ ካምፓኒ ጋር በነበረኝ ቆይታ ብዙ ተጠቅሜያለሁ። የስራ ፍቅርን፣ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል፣ እውቀትን እና ለወደፊት ተቋራጭ መሆን የሚያስችል ልምድ እና አቅምን ገንብቻለሁ። ለአስራ አራት ዓመታት ከእነርሱ ጋር ለነበረኝ ቆይታ ልዩ ትዝታ እና አክብሮት አለኝ። ከእነርሱ ፕሮጀክት ለቅቄ ወደ ሌላ ስሄድ ቻይናዊው አለቃየ አመስግኖ በካምፓኒው ስም አንድ ፒካፕ መኪና ሸልሞኛል። ለዚህም ለድርጅቱ እና ለቻይናዊው አለቃየ ምስጋናየ ትልቅ ነው።
በከተማዋ ያሉትን የቡድን እና የግል ፀቦችን በመሸምገል፣ በማስታረቅ እንዲሁም በጎ ተግባራትን በማድረግ ይታወቃሉ፣ እስኪ ስለዚህ ይንገሩን፤
ትክክል ነው። ለምሳሌ መሳሪያ ይዞ ርስ በርስ በቡድን ፀብ ወንድም ከወንድሙ፣ ጓደኛ ከጓደኛው ለመጠፋፋት የተጋበዙባቸውን ትልልቅ ግጭቶች ከዚህም ከዚያኛውም ወገን ደውየ ፕሮግራም ሳስይዛቸው እግዚአብሔር ይስጣቸው በጣም ያከብሩኛል። እኔን ምሳሌ እያደረግኩ ከቡድን ፀብ እንዲወጡ እመክራቸው ነበር። በእኛ ምክንያት ሌሎችን በእኛ ዙሪያ ያሉትን የቅርብ ዘመዶቻችንን ለምን እናሳዝናለን? ጠላቶችንን ከማፍራት በፍቅር ወዳጆችን አፍርተን ለእኛም ለእኛ ለሆኑም ሰዎች በነፃነት የትም ቦታ ሄደን፣ ብንታመምም ሆነ የሆነ ችግር ቢደርስብን ተሯሩጦ ከችግራችን ሊያወጣን የሚችልን ኅብረተሰብ የራሳችን ማድረግ እየቻልን ለምን ሏላ ውስጥ እንገባለን እያልኩ እመክራቸዋለሁ። እነርሱም ቆም ብለው ያለየነው ነው እንድናይ ያደረግከን እናም ወንድምነት ፍቅር ያሸንፋል አንድነት ነው የሚበልጠው በሚል ይረዱኛል ። በብዛት ሰዎች አያስቸግሩኝም፤ አክብረው ይሰሙኛል። እናም ታርቀው ሰላማዊ ሕይወት ይመራሉ። እንደዚህ አይነት የማስታረቅ እና የመሸምገል ስራ ስሰራ እውላለሁ ሁሌ።
አልፎም ከባልደረቦቼ ጋር አስተባብረን ልጆቻቸው ሞተው አሁን ረዳት የላቸውን አቅመ ደካሞች እየዞርን እንጠይቃለን። የታመመን እንጠይቃለን። የታሰረም ካለ ካለ በዋስትና ወጥቶ ከድርጊቱ እንዲፀዳ እና ወደ ስራ የሚሰማራበትን መንገድ እናመቻቻለን። እንዲህ ያለው ነገር በከተማው ያለህን ተሰሚነት ከፍ ያደርገዋል። ለአንተም የህሊና እርካታን ታገኝበታለህ። የሰማዩንም ቤትህንም ትሰራበታለህ። መልካም ማድረግ ለራስ ነው። መልካምነት ትርፉ ብዙ ነው ትላለች እህቴ። በቀርቡ መኖሪያ ቤታችን በእሳት ሲቃጠል ሕዝቡ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ተረባርበው ቤታችንን እንደገና ሲሰሩልኝ ሳይ እውነትም መልካምነት ለራስ ነው! የሚባለው እውነት ነው አልኩኝ። የሰው ፍቅር ከምንም ነገር ይበልጣል። በዚህ አጋጣሚ በችግር ጊዜ ከጎኔ የነበሩትን ሁሉ ምስጋናየ በያሉበት ይድረሳቸው።
ባህርዳር በቅርቡ ልዩ የእውቅና ስነ ስርአት አዘጋጅታ አመስግናዎታለች፣ ምን ተሰማዎ?
በእውነቱ በጣም ደስ ብሎኛል። “ባሕር ዳር የበኩር ልጇን ታመሰግናለች። ማንም እንዳይቀር፣ ኢንስትራክተር አድማሱ ፋንታ!” የሚለውን ማስታወቂያ ሶሻል ሚዲያ ላይ ሳይ በእርግጥ የደስታ እንባ እስኪመጣብኝ ድረስ ተገረምኩ። ምን አድርጌ ነው? ለከተማዋስ ምን አደረግሁ? ብየ ባስብም ስለተደረገልኝ ክብር እግዚአብሔር ያክብርልኝ። ቀብሬም ሰርጌም አሁን ነው እስከማለት የደረሰኝ ልዩ ደስታ ሰጥታችሁኛል አመሰግናለሁ። እንዳከበራችሁኝ እግዚአብሔር ያልብርልኝ።
ኢንስትራክተር አድማሱ ፋንታ ጥሪያችንን አክብረው የሕይወት ልምድዎን ስላጋሩን በበኩር ጋዜጣ ዝግጅት ስም እናመሰግናለን።
እኔም አመሰግናለሁ።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የታህሣስ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


