እ.አ.አ በ1940 በአሜሪካ ከስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁት ቨርጂኒያ ሂስሎፕ ከ83 ዓመታት በኋላ በ105 ዓመታቸው ሁለተኛ (ማስትሬት) ዲግሪያቸውን ማግኘታቸውን ዩፒ አይ ድረ ገጽ አስነብቧል::
በ1936 የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ያገኙት ቨርጂኒያ ሂስሎፕ በዛው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ወይም የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ይቀጥላሉ:: ቨርጂኒያ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለው እና አጠናቀው የመመረቂያ ጥናታዊ ፅሁፍ ማቅረብ ሲቀራቸው ከትዳር አጋራቸው ጋር የጫጉላ ሽርሽር ሊያደርጉ ዝግጅት ላይ ነበሩ::
የቨርጂኒያ ሂስሎፕ አዲሱ የትዳር አጋር ጆርጅ ሂስሎፕ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በውትድርና እንዲያገለግል ጥሪ ይቀርብለታል:: ይሄኔ ከሁሉም በላይ የአገር ጥሪ ይቀድማልና ባለቤታቸው ወደ ግዳጁ እንዲያመራ ያደርጋሉ::
ቨርጂኒያ ሂስሎፕ የጫጉላ የሽርሽር ቦታቸው ምርጫ በተፈጠረው ሁነት ተወስኗል:: ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም፤ ባለቤታቸው በዘመተበት በጃፓን ኦክላሃማ አደረጉ:: በሎስ አንጀለስ ያደጉት ሂስሎፕ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ በዋሽንግተን የባለቤታቸው የጆርጅ ሂስሎፕ ቤተሰብ የከብት ርባታ ስራን ተቀላቅለዋል፤ በትዳር ያገኟቸውን ሁለት ልጆችም አሳድገዋል::
ቨርጂኒያ ሂስሎፕ በ2018 እ.አ.አ የያኪማ ትምህርት ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ለመሆን ተወዳድረው አሸንፈዋል:: በዋሽንግተን ግዛት ራሳቸውን የቻሉ የማህበረሰብ ኮሌጆች እንዲቋቋሙም ጥረት አድርገዋል::
ቨርጂኒያ “ያቋረጥኩትን የማስተርስ ዲግሪዬን ባላጠናቅቅም ለትምህርት ድጋፍ በአደረኩ ቁጥር ደስተኛነት ይሰማኛል” ሲሉ ነው የገለጹት:: በ2018 እ.አ.አ በዋሽንግተን ግዛት የማህበረሰብ ኮሌጆች እንዲከፈቱም ጥረት አድርገዋል::
በሴቶች ለሚመራው ሄሪቴጅ ዩኒቨርስቲ ማጠናከሪያ ገንዘብ ለማሰባሰብ ተመርጠውም ሰርተዋል:: በዚሁም ስድስት ሚሊዬን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማሰባሰብ ችለዋል:: በት/ቤቱ የቦርድ አመራር አባል ሆነውም ለመምረጥ በቅተዋል::
በሰኔ 19/2024 እ.አ.አ የስታንፎርድ ድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ላለፉት 20 ዓመታት ያለመታከት ለሰሩት ጠንካራዋ አዛውንት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን “የፍትሀዊነት ጠንካራ አቀንቃኝ እና ለሁሉም እኩል የመማር እድል ተሟጋች” በሚል መጠሪያ አሞካሽቶ አበርክቶላቸዋል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም