ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ ለመስኖ ልማት፣ ለዓሳ ሀብት ልማት፣ ለእርሻ ሥራ እና ለሌሎች ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ሰፊ የውኃ ሀብት አላት። ይህ ፀጋዋም የአፍሪካ የውኃ ማማ የሚል ተጨማሪ መገለጫ አስገኝቶላታል:: ዳሩ ግን በውኃ ፀጋችዋ ልክ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም።
በኢትዮጵያ በተፈጥሮ ከሚገኘው የውኃ ሀብት ከፍተኛው በሐይቆች የተሸፈነ እንደሆነ በጣና ሐይቅ ዙሪያ ለረጅም ዓመታት በርካታ የምርምር ጽሑፎችን የጻፉት ዶክተር እሸቴ ደጀን በ1998 ዓ.ም “የጣና ሐይቅ ዓሳ ሀብት እና ዘላቂ ልማት” በሚል መጽሐፋቸው አስነብበዋል:: ኢትዮጵያ የበርካታ ሐይቆች፣ ወንዞች፣ ኩሬዎች እና ምንጮች ባለቤት ብትሆንም ብዙም ያልተጠቀመችበት የዓሳ ሀብት የሚገኘው ከነዚሁ የውኃ ክፍሎች እንደሆነ መጽሐፉ ያትታል::
አብዛኛው የውኃ ሀብቷ ዓሳን ለማምረት ምቹ ቢሆንም ባሕላዊ በሆነ የዓሳ ማስገር ዘዴ እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የዓሳ ምርቱ ሊያድግ አልቻለም:: በአሁኑ ወቅት ዘርፉ ለጠቅላላ የሀገር ምርት (GDP) የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከሁለት ነጥብ ሰባት በመቶ እንደማይበልጥ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ያብራራሉ::
በሌላ በኩል ተፈጥሯዊ የውኃ ሀብት የሌላት አፍሪካዊቷ ሀገር ግብጽ ለዘርፉ በሰጠችው ትኩረት ከፍተኛ የዓሳ ምርት ታመርታለች። “ከኢትዮጵያ ድንበር ተሻግሮ የሚሄደውን የዓባይ ወንዝን ተጠቅማ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ገንብታ በዓመት ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ ዓሳ በማምረት ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ዓሳ አምራች ለመሆን በቅታለች” ሲል እ.አ.አ በ2021 ሪሰርች ጌት (Reserch Gate) የተባለ የመረጃ ምንጭ አስነብቧል::
ኢትዮጵያ ሌሎች ሀገሮች በስስት የሚያዩዋቸው ወንዞች እና ሐይቆች ባለቤት ብትሆንም ሀብቷን ግን በሚገባው ልክ መጠቀም እና ህዝቦቿን መመገብ አልቻለችም:: ለዚህም ነው በኢትዮጵያ በዓመት የሚመረተው የዓሳ ምርት ከ70 ሺህ እስከ 90ሺህ ቶን እንደማይበልጥ የሚነገረው:: ዘርፉ ብዙም ትኩረት ባለማግኘቱ ለምጣኔ ሀብቱ ምርት የሚያበረክተው አስተዋጽኦም ዝቅተኛ ነው::
ዶክተር እሸቴ በመጽሐፋቸው እንዳብራሩት በዓለም ላይ እየጨመረ የመጣውን የምግብ እጥረት ለማቃለል ዓሳ ከፍተኛ ድርሻ አለው:: ዓሳ የያዛቸው የምግብ ይዘቶች /ፕሮቲኖች/ ለሰው ልጆች እጅግ አስፈላጊ ናቸው:: የዓሳ ተረፈ ምርት ለእንስሳት መኖ በማዘጋጀት ተጨማሪ ጥቅም ይሰጣል::
ጣና ሐይቅ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ስጋት ውስጥ ከገባ ውሎ አድሯል። በሐይቁ ላይ በዓሳ ማስገር ሥራ የተሰማሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ታዲያ የተጋረጠውን አደጋ መከላከል ካልተቻለ ከሐይቁ ኅልውና ባሻገር ሕይወታቸው ላይ የከፋ ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው::
አስማረ ይርዳው ለበርካታ ዓመታት ከጣና ሐይቅ ዓሳ እያሰገረ በሚያገኘው ገቢ ህይወቱን እየመራ ይገኛል:: የሦስት ልጆች አባት የሆነዉ አስማረ “ጣና የኔ ባለውለታየ ነበር” ይላል:: ነበር ያለውም ባለፉት ዓመታት የተሻለ ምርት በማግኘት የተሻለ ገንዘብ ያገኝ እንደነበር በማስታወስ ነው:: ከጣና ሐይቅ ከመዝናናት እና ንጹህ አየር ከማግኘት ባለፈ በልዩ ሁኔታ ልጆቹን የሚያስተዳድርበት ነው:: ለበርካቶች መተዳደሪያ የሆነው ጣና ሐይቅ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዓሳ ምርቱ ቀንሷል ይላል::
የዓሳ ማስገር ሥራውን ከጀመረ 20 ዓመታትን ያስቆጠረው አስማረ የጣና ሐይቅ የዓሳ ምርት በእጅጉ እየቀነሰ መምጣቱን ነው የሚናገረው:: ባለፉት ዓመታት በአንድ ሳምንት ከሦስት ሺህ እስከ አራት ሺህ ብር ይሸጥ እንደነበር በማንሳት “በአሁኑ ወቅት ሠራሁ ብል ከሦስት መቶ ብር አይበልጥም” ብሏል:: ለዚህ ምርት መቀነስ እንደምክንያት የሚያነሳቸው ደግሞ ሕገ-ወጥ ዓሳ አስጋሪዎች መስፋፋት፣ የዓሳ ማስገሪያ መረቡ ትክክለኛ አለመሆን፣ በጣና ዙሪያ የሚለቀቀው ፈሳሽ ቆሻሻ፣ የእንቦጭ አረም መስፋፋት፣ ደለሎች እና ሌሎች መጤ አረሞች ናቸዉ:: ሆቴሎች እና ሌሎች ተቋማት ወደ ሐይቁ የሚለቁትን ቆሻሻ ማቆም አለባቸው ብሏል::
ሌሎች ሐሳባቸውን ለበኩር የሰጡ በጣና ሐይቅ በዓሳ ማስገር ሥራ የተሰማሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከእጅ ወደ አፍ ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት ህይወታቸዉን ሲመሩበት መቆየታቸውን ተናግረዋል:: የቀጣይ እጣ ፋንታችን ግን ስጋት ውስጥ ጥሎናል:: በመሆኑም ሁላችንም ለጣና ጤንነት መጠበቅ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል::
ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የዓሳ ነጋዴዎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ የዓሳ ምርቱ እየቀነሰ መሆኑን ምስክሮች ናቸው:: ከአሁን በፊት የተሻለ ምርት በአስጋሪዎች በኩል ይቀርብላቸው እንደነበር የሚያስታውሱት በአሁኑ ወቅት ግን ዝቅተኛ እንደሆነ ነው የሚናገሩት:: ከደንበኞቻቸው ተሰብስበው የሚመጡ ዓሳዎች በእጅጉ ቀንሷል:: ጣና ሐይቅ የኔ ሀብት ነው ብሎ የሚቆጣጠረው አካል ሊኖር ይገባል:: መንግሥት ሕገ ወጦችን ወደ ሕጋዊ ዓሳ አስጋሪነት ቢያስገባቸው ለምጣኔ ሀብቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው:: ጣና ሐይቅ አካባቢ የሚኖሩ እና የሚሰሩ ግለሰቦች መጤ አረሞችን መንቀል፣ ቆሻሻን ባለመልቀቅ ከብክለት መጠበቅ ይኖርባቸዋል::
በኢትዮጵያ ከ200 የማያንሱ የዓሳ ዝርያዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል 28 የሚሆኑት መገኛቸው በአማራ ክልል ጣና ሐይቅ ነው:: ይሁን እንጂ እነዚህ የዓሳ ዝርያዎች በተለያዩ ምክንያቶች እየተመናመኑ እንደሆነ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ::
በኢትዮጵያ ከ40 እስከ 50 በመቶ የዓሳ ምርት የሚሸፍነው የአማራ ክልል እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት የዓሳ ሀብት ባለሙያው አበበ ፈንታሁን ናቸው:: ክልሉ ለዓሳ ሀብት ልማት ምቹ የአየር ንብረት እና በቂ የውኃ ሀብት ያለው ነው ብለዋል:: ከነዚህ መካከልም እንደ ሀገርም እንደ ክልልም በዋናነት የሚጠቀሰው ጣና ሐይቅ ነው::
ጣና ሐይቅ በውስጡ በርካታ ብዝኃ ህይወት የያዘ ሐይቅ ነው:: ከመዝናኛነቱ፣ ከንፁህ አየሩ እና ከመሰል ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ባሻገር በዓሳ ማስገር ለተሰማሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ መሠረታቸው ነው:: በአብዛኛው በሐይቁ እየተመረተ ለገበያ የሚቀርቡ የዓሳ ዝርያዎች ቀረሶ፣ አምባዛ /ቀይ ዓሳ/ እና ነጭ ዓሳ ይገኙበታል:: ዶክተር እሸቴ ደጀን የተለያዩ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው በመጽሐፋቸው እንዳስነበቡት ጣና ሐይቅ በዓመት ከሰባት ሺህ እስከ 15 ሺህ ቶን ዓሳ የማምረት አቅም አለው::
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በ2012 ዓ.ም ባሳተመው “ፊሽስ ኦፍ ሌክ ጣና (Fishes of Lake Tana)” በተሰኘው መጽሐፍ ላይ የጣና ሐይቅ በዓመት እስከ 20 ሺህ ቶን ዓሳ የማምረት አቅም ቢኖረውም እየተመረተ የሚገኘው የዓሳ መጠን ግን ከ10 ሺህ ቶን በታች እንደሆነ ተገልጿል:: ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ወቅት በጣና ሐይቅ እየተመረተ ያለው ዓሳ ከስድስት ሺህ ቶን እንደማይበልጥ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ:: ለዓሳ ምርቱ መቀነስ ባልተፈቀደ የማስገሪያ መረቦች ማስገር እና ሐይቁ በተለያዩ ምክንያቶች መበከሉ ተጠቅሷል::
እንደየዝርያቸው ቢለያዩም አንድ ዓሳ ለምግብነት ለመድረስ ከአራት ወራት እስከ አንድ ዓመት ጊዜ መቆየት እንዳለበት ባለሙያዎች ይመክራሉ:: ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በጣና ሐይቅ ለምግብነት የማይውሉ ዓሳዎች በጠባብ መረቦች እየታነቁ ይገኛሉ:: በዘርፉ ለተሰማሩ ዓሳ አስጋሪዎች እንዴት ማስገር፣ ማምረት እና ማጓጓዝ እንዳለባቸው በቂ ስልጠና መስጠት እንደሚገባ የዓሳ ሀብት ባለሙያው አቶ አበበ ያብራራሉ:: የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ከፍ እንዲል ብሎም ሕዝቡ በቂ የዓሳ ምርት እንዲያገኝ አዳዲስ የአመራረት ዘዴዎችን መከተል እንደሚገባም አስገንዝበዋል:: መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ሕዝቡ በባለቤትነት ሐይቁን እንዲጠብቅ እና እንዲንከባከብ ማድረግ ይገባልም ብለዋል::
የጣና ሐይቅም ሆነ የዓባይ ተፋሰስን ተከትሎ ዓሳን ማርባት ቢቻል ዘርፉ ለምጣኔ ሀብት ማበርከት የሚገባውን ድርሻ ይወጣል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚናን ይጫወታል። ሰፊ የሥራ ዕድልም ይፈጥራል:: ባለሙያው ለበኩር እንዳብራሩት የአማራ ክልል በተፈጥሮ የውኃ አካላት ብቻ ከ30 ሺህ እስከ 40 ሺህ ቶን ዓሳ ምርት ማምረት የሚችል አቅም አለው::
በክልሉ ሰባት አነስተኛ እና ከፍተኛ ሐይቆች ይገኛሉ:: በ22 ግድቦች እና በ16 ወንዞች ላይ የዓሳ ጫጩት በመጨመር የዓሳ ምርት ለማምረት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ባለሙያው ገልፀዋል:: በሐይቆች እና በወንዞች ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች በዓሳ እርባታ ሥራ እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል::
ዓሳ የማስገር ዝግ ወቅት እንደየ ውኃማ አካላት ቢለያይም በአብዛኛው በክረምት ወቅት ዓሳ የሚራባበት በመሆኑ ዝግ ይደረጋል የሚሉት አቶ አበበ፣ በዚህም በወጣው አዋጅ እና መመሪያ መሠረት ከግንቦት 15 አስከ ሐምሌ 15 ድረስ የጣና ሐይቅ ከዓሳ ማስገር ሥራ ነፃ እንደሚደረግ ተናግረዋል:: ከዚህ በተጨማሪም በገባር ወንዞች ላይ ከሐምሌ ወር መጀመሪያ እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ዓሳዎች እንዲራቡ ዝግ የሚደረግበት ወቅት መሆኑን አክለዋል። ቢሆንም ግን አዋጅ እና መመሪያውን በትክክል ለመተግበር ብዙ ሥራ ይጠይቃል ነው ያሉት::
በሐይቆች፣ በግድቦች እና በወንዞች የዓሳን ምርት በቋሚነት በብዛት ማምረት፣ የዓሳ ማስገር ዝግ ወቅቶችን ማስከበር፣ ሕጋዊ የዓሳ ማስገር ፈቃድ የሌላቸው ዓሳ አስጋሪዎችን የማስገሪያ ፈቃድ እንዲኖራቸው ማድረግ፣ የዓሳ ግብርና በማስፋፋት አርሶ አደሮች እንዲሳተፉ ማድረግ፣ ሕጋዊ የዓሳ ማስገሪያ መረቦችን ማቅረብ፣ ዓሳ የማይመረትባቸውን የውኃ አካላት እና አዳዲስ ግድቦችን በመገንባት የዓሳ ጫጩት መጨመር ወይም ማራባት የዘርፉ ትኩረቶች ናቸው::
እንደ ባለሙያው ገለጻ በክልሉ ከ21 ሺህ በላይ ዜጎች በዓሳ ማስገር እና ተያያዥ ዘርፎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል:: ጣና ሐይቅ ውስጥ ደግሞ ከስድስት ሺህ በላይ ዜጎች ዓሳ በማስገር እንደሚተዳደሩ ተናግረዋል::
እንደ ሀገር የዓሳ ምርት በበቂ ሁኔታ እየተመረተ አይደለም፤ ለዚህም ማሳያው በኢትዮጵያ በአማካኝ አንድ ሰው ዜሮ ነጥብ አምስት /ግማሽ/ ኪሎ ግራም ብቻ እንደሚመገብ አቶ አበበ ያብራራሉ:: ጎረቤት ሀገር ግብጽ ግን በአማካኝ ከሰባት ኪሎ ግራም በላይ አንድ ሰው እንደሚመገብ አስረድተዋል:: እንደ ሀገር ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ እና የዕውቀት ክፍተት መኖሩ ባለን ሀብት ልክ መጠቀም እንዳልተቻለ አብራርተዋል:: አዳዲስ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ደረጃውን የጠበቀ መረብ በማቅረብ፣ የዓሳ ዝርያዎችን በማስፋፋት በቂ የዓሳ መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በመገንባት፣ የሚወጡ ሕጎችን፣ መመሪያዎችን እና አዋጆችን መተግበር፣ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችንም በመቆጣጠር የዓሳ ምርትን ማሳደግ እንደሚገባ አመላክተዋል::
በአጠቃላይ የክልሉ መንግሥትም በጣና ሐይቅ አዋሳኝ አካባቢዎች የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ከማቋቋም ባለፈ የሐይቁን ህልውና መጠበቅ ግድ ይላል:: የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል ማድረግም ይኖርበታል::
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም