ለሃያ ሦስት ቀናት ሲደረግ የነበረው የ2025 የቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ውድድር ባለፈው ሳምንት ተጠናቋል። ይህ ታላቅ መድረክ ከጂሮ ዲ’ኢታሊያ ቀጥሎ እና ከቩኤልታ አ ኤስፓኛ በፊት የሚካሄድ ሲሆን ከሶስቱ ታላላቅ የብስክሌት ውድድሮች (Grand Tours) መካከል ሁለተኛው ነው። የዘንድሮው ውድድር 21 ደረጃዎች የነበሩት ሲሆን አጠቃላይ ሦስት ሺህ 320 ኪሎሜትሮችን ሸፍኗል።
ውድድሩን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የብስክሌት ቡድንን ወክሎ የተሳተፈው ስሎቫኔያዊው ታዴይ ፖጋቻር አሸናፊ ሆኗል። የ26 ዓመቱ ብስክሌተኛ መድረኩን ለአራተኛ ጊዜ ነው ያሸነፈው። ታዴይ ፖጋቻር ከዚህ በፊት በ2020፣በ2021 እና በ2024 እ.አ.አ በመድረኩ መንገሡ አይዘነጋም። ታዴይ ፖጋቻር የአጠቃላይ የደረጃ አሸናፊ በመሆኑ ዝነኛውን ቢጫ መለያ አጥልቋል። ከቢጫው መለያ በተጨማሪ የተራራ ላይ ብቃቱን በማሳየት የነጠብጣብ መለያውን አሸንፏል።
ፖጋቻር ለአራተኛ ጊዜ ተቀናቃኞቹን መርታቱን ተከትሎ ጥንካሬውን የተጠራጠሩ ሰዎች ብስክሌቱ እና እርሱ በጥብቅ እንዲመረመር ጠይቀዋል። አወዳዳሪው አካልም የ26 ዓምቱ ወጣት ምንም ዓይነት አበረታች ንጥረ ነገር አለመጠቀሙን አረጋግጧል። ብስክሌቱ ጋርም ምንም ዓይነት የተደበቀ ሞተር አለመኖሩን በኤክስሪይ ማሽን ጭምር በመጠቀም ማረጋገጡ ተዘግቧል።
ዴንማርካዊው ብስክሌተኛ ጆናታን ቪንገጋርድ ሁለተኛ እና ጀርመናዊው ፍሎሪያን ሊፓዊትዝ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው መጨረሳቸው የሚታወስ ነው። ጆናታን ቪንገጋርድ በ2022 እና በ2023 እ.አ.አ በተከታታይ ማሸነፉ አይዘነጋም።
በአጠቃላይ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ፍሎሪያን ሊፓዊትዝ ከ26 ዓመት በታች ለሆኑ ምርጥ ወጣት ተወዳዳሪ የሚሸለመውን ነጭ መለያም ማጥለቁን የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል። ጣልያናዊው ጆናታን ሚላንም የነጥብ ደረጃን ማሸነፉን ተከትሎ የአረንጓዴ መለያን አጥልቋል። በቡድን ደረጃ ደግሞ በአጠቃላይ ደረጃ አሸናፊ የሆነው ጆናታን ቪንገጋርድ የረታ ሲሆን የውድድሩ ምርጥ ተፋላሚ ደግሞ አየርላንዳዊው ቤን ሂሊ ሆኗል።
በቱር ደ ፍራንስ ታሪክ አሜሪካዊው ላንስ አርምስተሮንግ ሰባት ጊዜ በማሽነፍ ባለክብረወሰን የነበረ ቢሆንም አበረታች ንጥረ ነገር ተጠቅሞ በመገኘቱ ሽልማቱን ተነጥቋል፡፡ አሁን ላይ አራት ብስክሌተኞች በተመሳሳይ አምስት ጊዜ መድረኩን በማሸነፍ ከፖጋቻር በፊት ስማቸውን በታሪክ መዝገብ አስፍረዋል፡፡
በውድድሩ አዳዲስ የመጪው ዘመን ጠንካራ ብስክሌተኞች የታዩበት መድረክ ጭምር ነበር። ጣሊያናዊው ጆናታን ሚላን በመጀመሪያው የቱር ደ ፍራንስ መድረኩ የአረንጓዴ መለያ ያሸነፈ ወጣት ብስክሌተኛ መሆን ችሏል። ሌላኛው ወጣቱ ብስክሌተኛ ጀርመናዊው ፍሎሪያን ሊፓዊትዝም በዚህ በታላቁ መድረክ አስደናቂ ብቃቱን በማሳየት ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል። በተጨማሪም በርካታ አውስትራሊያውያን የብስክሌት ስፖርተኞች በእነዚህ የፈረንሳይ ሰንሰለታማ ተራሮች እና ኮረብታዎች ላይ አስደናቂ ብቃታቸውን ለዓለም ሕዝብ አሳይተዋል።
ብስክሌተኞች በሰዓት በአማካይ 43 ኪሎ ሜትር ጋልበዋል። ይህም በታሪክ ፈጣን ከሆኑ ውድድሮች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል። በዘንድሮው መድረክ 23 ቡድኖች ተሳትፈዋል፤ ይህን ያህል ቡድኖች ሲሳተፉም ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል። የ2025ቱ የቱር ደ ፍራንስ ውድድር ከሌሎች ጊዜያት ለየት ያደርገዋል ነው የተባለው፡፡ ሙሉ በሙሉ በፈረንሳይ መካሄዱ፣ በርካታ የከፍተኛ ተራራ ጫፍ ፍጻሜዎች የነበሩት መሆኑ፣ በፓሪስ አዲስ ፈታኝ እና አድካሚ ፍጻሜዎችን ማካተቱ ከቀደሙት ጊዜያት ለየት ያደርገዋል።
እንዲሁም በፍጥነቱ እና በአድካሚነቱ በመድረኩ ታሪክ ቀዳሚው ነው። ውድድሩ ከወትሮው በተለየ ውጥረት እና ፉክክር የበዛበት ነበር ተብሏል። የዘንድሮው 112ኛው ምዕራፍ የቱር ደ ፍራንስ ውድድር ከአምስት ዓመታት በኋላ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉም ደረጃዎች በፈረንሳይ ግዛት ውስጥ የተደረጉት።
መነሻው በፈረንሳይ ሊል ከተማ የነበረ ሲሆን ከተማዋ ውድድሩን ስታስጀምር ለአምስተኛ ጊዜዋ ነው። ብስክሌተኞች በመጨረሻው የፓሪስ ፍጻሜ ውድድር የሞንማርት ኮረብታዎችን እንዲወጡ መደረጋቸው ፍጻሜውን የተለየ አድርጎታል። በዚህ መድረክ በአልፕስ ተራሮች ላይ በተከሰተው የከብቶች በሽታ ወረርሽኝ ምክንያት አንድ የውድድር መድረክ እንዲያጥር ተደርጓል። ይህም በቱር ደ ፍርስንስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ውድድሩ እንዲያጥር ሆኗል። ተወዳዳሪዎች እስከ ሁለት ኪሎ ሜትር ከፍታ ያለው ተራራ መውጣታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ታዲያ ይህን ያህል ከፍታ ሲወጡም እ.አ.አ ከ1986 ወዲህ አዲስ ክስተት እንደሆነ ነው የተሰማው። ዝነኛውን እና ትልቁን የአልፕስ ተራራ ጨምሮ ብስክሌተኞች አምስት የተራራ ሰንሰለቶችን ወጥተዋል።
ከሳምንት በፊት የተጠናቀቀው ውድድር የሕግ መሻሻሎችም ተደርጎበት ነበር። በመጨረሻዎቹ ኪሎ ሜትሮች ላይ በሚደርስ አደጋ ወይም የቴክኒክ ችግር በአጠቃላይ የደረጃ ለውጥ እንዳይኖር ሦስት ኪሎሜትር የነበረው የመጨረሻው ርቀት ወደ አምስት ኪሎ ሜትር መደረጉንም መረጃዎች ያመለክታሉ። የብስክሌተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ እና ውድድሩን ለማዘመን ዘመኑ የደረሰበትን ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ምርቶችን ተጠቅመዋል። የተወዳዳሪዎችን የልብ ምት፣ የጉልበት መጠን፣ ፍጥነት እና ትክክለኛ ቦታ የሚያሳይ ቴክኖሎጂ መጠቀማቸውን መረጃዎች አስነብበዋል። የመጀመሪያው የቱር ደ ፍራንስ ውድድር የተጀመረው 1903 እ.አ.አ ነው። ላኦትዎ የተሰኘው ጋዜጣ ስርጭቱን ለማሳደግ ባወጣው ሀሳብ ነበር። በአጠቃላይ ሁለት ሺህ 428 ኪሎ ሜትር ሸፍነዋል።
ተወዳዳሪዎች በከባድ እና ምቹ ባልሆኑ መንገዶች ላይ ይጋልቡ ነበር። የመጀመሪያው አሸናፊም ፈረንሳዊው ብስክሌተኛ ሞሪስ ጋሪን ነው። ከ1920ዎቹ መጨረሻ እስከ 1960ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ቱር ደ ፍራንስ የሚካሄደው በተቋማት ቡድኖች ሳይሆን በብሔራዊ ቡድኖች ነበር። እ.አ.አ 1950ዎቹ አስከ 1990ዎቹ ድረስ ስፖርቱ የዘመነበት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የተዋወቁበት፣ ዘርፉ ከአጽነፍ አጽናፍ የተስፋፋበት እና ስፖረተኞችም ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ የተሸጋገሩበት ወቅት ነው። አሜሪካዊው ግሬግ ሌሞንድ እ.አ.አ በ1986 ውድድሩን በማሸነፍ ለበርካታ አስርት ዓመታት በአውሮፓውያን ተወዳዳሪዎች ተይዞ የነበረውን የበላይነት የገታበት ወቅት ጭምር ነው።
ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ደግሞ የቴሌቪዥን መስፋፋትን ተከትሎ የቱር ደ ፍራንስ ተወዳጅነት ጨምሯል። አሁን ደግሞ ውድድሩ ይበልጥ ፕሮፌሽናል እየሆነ መጥቷል። በመድረኩም ቀስ በቀስ ገድላቸው እንደ አፈ ታሪክ የሚነገር ስፖርተኞች ተፈጥረውበታል። የቱር ደ ፍራንስ ታላቁ መነሻ (Grand Départ) አሁን ከፈረንሳይ ውጪ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ኔዘርላንድስ፣ ጀርመን እና ዴንማርክ ባሉ ሀገራት በተደጋጋሚ መካሄድ ጀምሯል።
በታሪክ ረጅሙ የቱር ደ ፍራንስ ውድድር የተካሄደው በ1926 ሲሆን ተወዳዳሪዎች አምስት ሺህ 745 ኪሎ ሜትሮችን ጋልበዋል፡፡ ይህ ርቀት ከ63 ሺህ የእግር ኳስ ሜዳዎች ጋር እኩል ነው። የቱር ደ ፍራንስ ውድድር የተወዳዳሪዎችን አካላዊ ጽናት ብቻ ሳይሆን የብስክሌቶችንም ጥንካሬ ይፈትናል። ውድድሩ ለ23 ቀናት የሚቆይ ሲሆን ተወዳዳሪዎች ለሁለት ቀናት ብቻ ነው እረፍት የሚያደርጉት።
የሴቶች የቱር ደ ፍራንስ ከ1984 እስከ 1989 እ.አ.አ ለማዘጋጀት ሙከራዎች ተደርገው ነበር። ነገር ግን በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። በ2022 “ቱር ደ ፍራንስ ፌም” (Tour de France Femmes) የተባለ አዲስ ውድድር ተጀምሯል። ይህ ውድድር ለስምንት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የሚጀምረውም የወንዶቹ ውድድር ሲጠናቅቅ ነው፡፡ የዘንድሮው ውድድርም ተደርጎ መጠናቀቁ ይታወሳል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም