በከተማዉ ተስፋ የተጣለበት የውኃ ዋና ፕሮጀክት

0
82

ባሕር ዳር ከተማ ከዚህ በፊት ትታወቅባቸው ከነብሩ ስፖርቶች መካከል አንዱ የውሃ ዋና ስፖርት ነው። በቀደሙት ዓመታት ክልሉ እና ሀገራችንን ወክለው የተወዳደሩ እና ውጤታማ የሆኑ ስፖርተኞች ከባሕር ዳር ከተማ ወጥተዋል። ምንም እንኳ በከተማው ሁለት የውሃ ዋና ስፖርት ክለቦች ቢኖሩም በአጠቃላይ ስፖርቱ ግን አሁን ላይ ተዳክሟል።

በርካታ የማዋኛ  ገንዳ፣ ጣና ሀይቅ እና ለውሃ ዋና ስፖርት  አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ባሉበት ከተማ የስፖርቱ መቀዛቀዝ ብዙዎቹን አስቆጭቷል። በርካቶቹም ምክንያቱ ምንድነው? ሲሉ ይጠይቃሉ። በላቸው መላክ አሁን ላይ የውሃ ዋና ስፖርት ዓለም አቀፍ ዳኛ ሲሆን በባሕር ዳር ከተማ በእነርሱ ዘመን የነበረውን የውሃ ዋና ስፖርት ፉክክር እንዲህ ያስታውሳል።

እንደ ቀድሞው ዋናተኛ ገለጻ በቀደሙት ጊዜያት ስፖርተኞች እና አሰልጣኞች ለስፖርቱ ጥልቅ ስሜት እና ፍላጎት እንደነበራቸው ያስታውሳል፤ስነምግባር የነበራቸው እና ስፖርቱን የሚወዱ ነበሩ፤ ስፖርተኞቹ በክልል እና ሀገር አቀፍ ደረጃ ውድድሮች ውጤታማ የነበሩ ሲሆን ብሄራዊ ቡድኑን ወክለው በተለያየ መድረኮች ይሳተፉ እንደነበረም ይናገራል። አሁን ላይ ግን  ስፖርቱ የለም በሚባል ደረጃ መዳከሙን ዓለም አቀፉ ዳኛ ያስረዳል።

በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙት የአማራ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ እና የባሕር ዳር ከተማ ውሃ አገልግሎት ክለቦችም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሲሆኑ ተፎካካሪ ስፖርተኞች እየወጡባቸው አለመሆኑን የቀድሞው ዋናተኛ በላቸው መላክ ተናግሯል። ለዚህ ማሳያ ደግሞ ባሳለፍነው ጥር ወር በአርባ ምንጭ ከተማ ስምንተኛው የታዳጊ ወጣቶች የውሃ ዋና የምዘና ውድድር ሲካሄድ አማራ ክልል ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ አይዘነጋም።

በዚህ መድረክ ከሁለቱ የባሕር ዳር ከተማ ክለቦች ጨምሮ ከኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ እና ከአለፋ ጣቁሳ የውሃ ዋና ክለቦች የተውጣጡ ስፖርተኞች ክልሉን መወከላቸው የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ክለቦች የወጡ ስፖርተኞች አንድም ሜዳሊያ አላስመዘገቡም። ለውሃ ዋና ስፖርት ምቹ ፀጋ በተሰጣት ባሕር ዳር ተተኪዎች ላይ በደንብ አለመሠራቱ ስፖርቱን አቀዛቅዞታል። ክለቦች ፕሮጀክቶችን አለማያዛቸው ተተኪዎች እንዳይወጡ እና ስፖርቱ እንዲዳከም አድርጓል። በርካታ ዋናተኞች እና የዘርፉ አሰልጣኞች የወጡበትን ስፖርት በከተማው ለማነቃቃት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑንም ዓለም አቀፉ የውሃ ዋና ስፖርት ዳኛ በላቸው ይጠቁማል።

ከዚህ በፊት አቶ ኤሊያስ ዮሐንስ የተባሉ ግለሰብ በባሕር ዳር ከተማ ተጨማሪ የውሃ ዋና ስፖርት ክለብ ለማቋቋም ብዙ ጥረቶችን ቢያደርጉም በተለያዩ ምክንያቶች አልተሳኩም። አሁን ላይ ግን በአሰልጣኝ አበበ ዘሪሁን ተነሳሽነት ባሕር ዳር ከተማ በውሃ ዋና ስፖርት በቀደሙት ጊዜያት የነበራትን ስም እና ዝና ለመመለስ እየሠራ ይገኛል። የቀድሞው ዋናተኛ በባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማህበር የውሃ ዋና ፕሮጀክት ይዞ ከነሐሴ 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየሠራ ነው።

በፕሮጀክቱም ከሰባት ዓመት እድሜ እስከ 16 ዓመት እድሜ ያላቸው 94  ታዳጊዎች በሁለቱም ጾታዎች ስልጠናቸውን እየወሰዱ ነው። ሰልጣኞች አሁን  ላይ ስልጠናቸውን በሚገባ እየተከታተሉ መሆናቸውን የፕሮጀክቱ አሰልጣኝ አበበ ዘሪሁን ከአሚኮ በኵር ስፖርት ዝግጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። “ፕሮጀክቱ አንድ ዓመት ስላልሞላው እንጂ በዘንድሮው የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር ላይ መሳተፍ ይችሉ ነበር” ሲል ተደምጧል።

በባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ግቢ በሚገኘው የመዋኛ ገንዳ ስልጠና እየወሰዱ ያሉት ታዳጊዎች የስፖርት ቁሳቁስ እጥረት አለባቸው፤ የላብ መተኪያ እንደሌላቸውም አሰልጣኙ ነገሮናል። የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ፣ የከተማ አስተዳደሩ ስፖርት መምሪያ ድጋፍ እና ክትትል እናደርጋለን ብለው ቃል ቢገቡም እስካሁን ግን ቃል የገቡትን መፈጸም አልቻሉም። የሚመለከታቸው አካላት በመደበኛነት መዋኛ ገንዳውን ሙሉ ጊዜ እንዲጠቀሙበትም ጥያቄ አቅርበዋል። ባለሀብቶች ድርጅቶች እና ለስፖርቱ ፍቅር ያላቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም አሰልጣኙ ጠይቀዋል።

በባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ የውሃ ዋና ፕሮጀክት እየሰለጠነች ያገኘናት ሶሊያና በላቸው የ11 ዓመት ታዳጊ ስትሆን የውሃ ዋና ስልጠና ከጀመረች 11 ወራት ማስቆጠሯን ነግራናለች። በስልጠና ቆይታዋም ሁሉንም  የዋና ዓይነቶች በመልመድ ትልቅ ለውጥ አምጥቻለሁ ብላለች። “ጓደኞቼን ጨምሮ ወደዚህ ፕሮጀክት ስንመጣ ምንም ዓይነት የውሃ ዋና ልምድ አልነበረኝም፤ አሁን ላይ ግን በአሰልጣኞች ጥረት ጥሩ ዋናተኛ መሆን ችያለሁ” ብላለች። ታዳጊዋ ዋናተኛ በዘርፉ ሀገሯን ወክላ በሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች መታየት ህልሟ እንደሆነም ትናገራለች። “ህልሜን ለማሳክትም አስፈላጊው የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደረግልን” ስትል ትጠይቃለች።

ሌላኛው ታዳጊ ስሜነው ብርሃኑም በዚህ ፕሮጀክት እየሰለጠነ ያለ ታዳጊ ሲሆን በውሃ ዋና ስፖርት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የማድረግ ህልም ይዞ እየሠራ ነው። ታዲያ ህልሙን እውን ለማድረግ ጠንክሮ ስልጠናውን እየወሰደ መሆኑን ያስረዳል። የላብ መተኪያን ጨምሮ የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቋል።

ፕሮጀክቱ ሲጀመር የስልጠና ቦታ የማመቻቸት ሥራዎችን የሠራው የከተማ አስተዳደሩ ስፖርት መምሪያ በቀጣይም ድጋፍ እንደሚያደርግ በስፖርት መምሪያው የስልጠና እና ውድድር ባለሙያ የውሃ ዋና አማካሪ አቶ አደም መሀመድ ተናግሯል። ሰልጣኞች በተገቢው መንገድ ስልጠናቸውን እንዲከታተሉ የሚያግዙ የስፖርት ቁሳቁስ እና የላብ መተኪያ የሚያገኙበትን መንገድ እንደሚመቻች አቶ አደም መሀመድ ነግረውናል።

በተደጋጋሚ በውሃ ዋና ስፖርት ሰልጣኞች ስልጠና ጀምረው በተለያየ ምክንያት ስልጠናውን ያቋርጣሉ። በዚህ ምክንያት በዘርፉ ተተኪዎች እየጠፉ መሆናቸውን የተናገሩት በስፖርት መምሪያው የስልጠና እና ውድድር የውሃ ዋና አማካሪው አቶ አደም እነዚህ ታዳጊዎች ለሁለቱ ክለቦች ግብአት እንዲሆኑ እንሠራለን ብለዋል። በተጨማሪም ሰልጣኞች የውድድር እድል እንዲያገኙ ከወዲሁ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

ከብዛታቸው አንጻር እስካሁን በቂ የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው ያመኑት አቶ አደም በቀጣይ የስፖርት ቁሳቁስ እና የላብ መተኪያ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። የውሃ ዋና ፕሮጀክቱን ወደ ክለብ ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን የባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማህበር ክለቡን ለማያዝ ፈቃደኛ መሆኑን እና ወደ ተግባር ለመግባትም ሰነዶችን መፈራረማቸውን የፕሮጀክቱ  አሰልጣኝ አበበ ዘሪሁን ተናግሯል። በቅርቡም በባሕር ዳር ከተማ ሦስተኛው የውሃ ዋና ክለብ እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል።

(ስለሺ ተሸመ)

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here