በኩር በ30 ዓመታት ጉዞዋ

0
130

መንግሥትን እና ሕዝብን እንደ ድልድይ ሆነው ከሚያገለግሉት መካከል መገናኛ ብዙኃን አንዱ ነው። ለዚህም በኵር ጋዜጣ ሐምሌ 9 ቀን 1986 ዓ.ም  ጀምራ በአንድ  እና በሁለት ወር በልዩ ዕትም ዘገባዎችን ማዘጋጀት ጀመረች። ታኅሳስ 7 ቀን 1987 ዓ.ም በአማራ ክልል ማስታወቂያ ቢሮ በአንድ የሥራ ሂደት ሥር መታተም የጀመረችው በኵር ጋዜጣ ዝግጅት ለአሁኑ የአሚኮ መሠረትም ናት። ልክ እንደ ስሟ ሁሉ የአሚኮ የበኵር ልጅ ናት። ጋዜጣዋ ኅብረተሰቡን በማስተማር፣ በማዝናናት እና በማሳወቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።

ከ30 ዓመታት በፊት ከ10 በማይበልጡ ጋዜጠኞች፣ ቴክኖሎጂ በሌለበት እና በማይመች የሥራ ሁኔታ በኵር ጋዜጣ እየተዘጋጀች እና እየታተመች መሰራጨት ጀመረች። ታኅሳስ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ደግሞ 30ኛ ዓመቷ ነዉ ።

በኵር ጋዜጣ በቋሚነት ህትመት ከጀመረችበት ታኅሳስ 7 ቀን  1987 ዓ.ም  ጀምሮ አምዶቿን እና ይዘቶቿን በማሻሻል በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ እና በፓለቲካዊ ዘርፎች ሰፊ ትንታኔን በመሥራት ለአማራ ክልል ሕዝብ ብሎም ለሀገሪቱ የመረጃ ምንጭ ሆና እያገለገለች ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ቀድማ በመዘገብ፣ ችግሮች ከተፈጠሩ ደግሞ ለችግሮች መፍትሔዎችን በማመላከት የላቀ አስተዋፅኦ ስታበረክት ቆይታለች።

ለልማት መፋጠን እና ለዲሞክራሲ ግንባታ በኵር በትጋት ዘግባለች። በወቅቱ በስድስት አምዶች እና በስምንት ገፆች፦ የፊት ገፅ ዜና፣ ፓለቲካዊ፣ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የአንባቢዎችን አስተያየት እና የዞን ዜና በማካተት ለአንባቢያን በማድረስ ጉልህ ሚናዋን በማበርከት ዓመታትን ተሻግራለች። በኵር ጋዜጣ ህትመት በጀመረችበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የፊት ገፅ ዜናን ጨምራ በውስጧ ትኩረት፣ ማህበራዊ፣ አውደ ባህል፣ ከልማት ዙሪያ እና ስፖርት አምዶች በዋናነት በየሳምንቱ እየታተሙ ለአንባቢያን የሚቀርቡ ፅሑፎች ነበሯት። በወቅቱም በየሳምንቱ አራት ሺህ ቅጅ ስርጭት ነበራት።

በኵር ጋዜጣ በ30 ዓመታት ጉዞዋ በይዘት፣ በገፅ፣ በቅርፅ እና በአምድ ብዛት ሳምንታዊ ህትመቷን በማከናወን ዛሬ ላይ ደርሳለች። በውስጥ ገፆቿ የሚስተናገዱ አምዶች በየጊዜው የሥያሜ ለውጥ፣ በሌላ የመተካት እና የነበረውን በማስቀጠል መረጃዎችን ለሕዝብ ታደርሳለች። ከእነዚህ መካከልም የልማት ሥራዎችን በመዘገብ በክልሉ ልማት እንዲፋጠን  ከልማት ዙሪያ፣ ገጠር ልማት፣ ኢኮኖሚ እና ምጣኔ ሀብት በሚል ማሻሻያዎችን እያደረገች አሁን ላይ ላለችበት የምጣኔ ሀብት አምድ ደርሳለች።

በክልሉ የሚገኙ ሠው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን በማስተዋወቅ እና ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ በትኩረት ሥትሠራ ቆይታለች፤ እየሠራችም ትገኛለች። የክልሉ ግብርና እንዲዘምን (ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲስፋፋ) የአርሶ አደሩ የእርሻ ሥራ ከበሬ ጫንቃ እንዲላቀቅ ሰፊ ሥራ አከናውናለች። በኢንዱስትሪው፣ በኢንቨስትመንቱ፣ በቱሪዝሙ፣ በንግዱ፣ በግብር አሰባስቡ፣ በግብርናው፣ በማንፋክቸሪንጉ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታው እና በሌሎች ጉዳዮች በትኩረት በመዘገብ ለውድ አንባቢያን ያለመታከት መረጃዎችን አጋርታለች። የሀገራችን ኢኮኖሚ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪው እንዲሸጋገር ሰፊ ሽፋን ሰጥታ ዘግባለች።

በአማራ ክልል ብሎም በሀገራችን የሚገኙ የውኃ ሀብቶችን በአግባቡ መጠቀም እና መንከባከብ እንዲቻል፣ የህብረት ሥራ ማሕበራት እና ዩኒየኖች እያበረከቱት ያሉትን አስተዋፅኦ በማሳየት እና ጉድለቶች እንዲስተካከሉ በማድረግ፣ በእንስሳት ሀብት ልማት የሚስተዋሉ ችግሮችን እና ጥንካሬዎችን በማሳየት፣ የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ እንዲቀርብ የአርሶ አደሩ ድምፅ በመሆን፣ ቴክኖሎጂ እንዲስፋፋ፣ የአፈር ለምነት እንዲጠበቅ፣ ግብርናው እንዲዘምን፣ ድርቅን ሊቋቋሙ የሚችሉ አዳዲስ ምርጥ ዘር እንዲመረት፣ ሙስና በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ የሚያሳድረውን ከፍተኛ ጫና በማሳየት በትጋት ዘግባለች።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ለሀገራዊ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ በማስገንዘብ፣ በተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ በንብ ማነብ፣ በእንስሳት እርባታ፣ የቁጠባ ባሕል እንዲዳብር፣ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ዘላቂነት እንዲኖረው እና በትኩረት እንዲሠራ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ እንዲፋጠን፣ የኑሮ ውድነቱ በማኅበረሰቡ ላይ እያደረሰው ያለውን ጫና በማሳየት እና የመፍትሄ መንገዱን በመጠቆምም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክታለች። እኛም ልክ የዛሬ 30 ዓመት ታትማ ወደ አንባቢያን የደረሰችው በኵር ጋዜጣ ለክልሉ ብሎም ለሀገራችን ያበረከተችውን አስተዋፅኦ  ከብዙዎች በጥቂቱ ለማስታወስ ወደናል፡፡

በኵር ጋዜጣ በ30 ዓመት ታሪኳ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በመተንተን እና ሐሳብ በማንሳት ስትዘገብ ቆይታለች። ለአብነትም ታኅሳስ 7 ቀን 1987 ዓ.ም “ከልማት ዙሪያ” በሚል አምዷ የተፈጥሮ አደጋዎችን እና ሰው ሠራሽ ችግሮችን በመቋቋም እና በማስወገድ የልማት ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ በዘገባዋ አስነብባለች።

ሐምሌ 7 ቀን 1987 ዓ.ም “ግብርና በቴክኖሎጂ ሲመራ ውጤቱ ይሰምራል” በሚል ርዕሰ ጉዳይ የቴክኖሎጂን ጠቀሜታ በማንሳት ለአንባቢያን አድርሳለች። ጥቅምት 14 ቀን 1992 ዓ.ም “ከተረጅነት ለመውጣት ልማትን ማፋጠን” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዜጎች ጊዜና ጉልበታቸውን ለልማት እንዲያውሉ ምክረ ሐሳቧን አስቀምጣለች።  “በሥራ አጥነት ላይ የዘመተ ተቋም” በሚል በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሥር የዕደ ጥበባት ማስፋፊያ የሚሰጠውን ስልጠና በኅዳር 5 ቀን 1993 ዓ.ም የተቋሙን ጥንካሬ ዘግባለች።

ከልማት ዙሪያ የሚለው የበኩር ጋዜጣ አምድም የክልላችንን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ፣ የግንባታ ሥራን፣ ኢንቨስትመንትን፣ ግብርናን፣ የተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃን.፣ ቱሪዝምን፣ ንግድን፣ ፋይናንስን እንዲሁም የኢንዱስትሪ ልማትን የተመለከቱ ዘገባዎችን አስተናግዳለች።

በየጊዜው የቅርፅ እና የይዘት ማሻሻያ እያደረገች እና አምዷን እያሰፋች ለአንባቢያን በየሳምንቱ የምታደርሰው በኵር ጋዜጣ  ጥቅምት 17 ቀን 2001 ዓ.ም ቀደም ብሎ “ከልማት ዙሪያ” የነበረውን የአምድ ስያሜ “ገጠር ልማት” በሚል ተቀይሯል፡፡ በአምዱ  “ምቹ የአየር ንብረት ለዘላቂ ልማት” በሚል ርዕስ እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል መሠራት ስላለበት ጉዳይ ሽፋን አግኝቷል።

በክልሎች ታሪክ ፈር ቀዳጇ በኵር ጋዜጣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የውኃ አካላት በስፋት ትልቁ ሐይቅ እንደሆነ የሚነገርለት እና ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዋና የውኃ ምንጭ፣ ለቱሪስቶች መዳረሻ፣ ለኤሌክትሪክ ኀይል ማመንጫ፣ ለብዙዎች መተዳደሪያ እና ለመስኖ ልማት ሥራ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚሰጠውን የጣና ሐይቅ ጉዳይ በትኩረት ዘግባለች።

የእንቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ከተከሰተ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የሐይቁን ህልውና ለመታደግ ከሀገር ቤት እስከ ውጭው ዓለም፣ ከሀገር በቀል እውቀት እስከ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማሻገር፣ ከተማሪ እስከ ከፍተኛ ምሁራን፣ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ርብርብ እንዲደረግ በየጊዜው ተከታታይ ዘገባ ለአንባቢያን አድርሳለች። ዳሩ ግን እንቦጭን በማስወገድ ጣና ሐይቅን ከገጠመው ፈተና ማላቀቅ አለመቻሉን እየዘገበች ቆይታለች። አሁንም የጉዳቱን ጥልቀት በመረዳት ሰፊ ሽፋን ሰጥታ በዘገባዎቿ ትዳስሳለች። የጣና ሐይቅ ዋነኛ ጠላቱ እና ሕመሙ እንቦጭ ቢሆንም ወደ ሐይቁ በሚገባ ደለል እና በሚለቀቁ ቆሻሻ ውጋጆች ህልውናው አደጋ ላይ መሆኑን በተከታታይ አሳይታለች።

በኩር ጋዜጣ የእንቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ አያሌ ተከታታይ ዘገባዎችን ሠርታለች። በዘገባዎቿም መጤ አረሙ የሐይቁን መጠን እያመናመነው መሆኑን፣ በሐይቁ ውስጥ በሚገኙ ብዝኃ ህይወት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያለጣና ሐይቅ ሕልውናው አደጋ ላይ የሚወድቅ ስለመሆኑ፣ አረሙ በዓሳ ሐብት ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት፣ በሐይቁ ውስጥ በሚገኙ ገዳማት እና በውስጣቸው በሚገኙ ቅርሶች ላይ ስለሚያደርሰው ዘርፈ ብዙ ችግር፣ በአየር ፀባይ ለውጥ ላይ ስለሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ችግሩን ለመፍታት መወሰድ ስላለበት ርምጃ… ነዋሪዎችን፣ ባለሙያዎችን፣ ምሁራንን፣ ፓለቲከኞችን፣ ጣናን የመጠበቅ እና የመንከባከብ ኃላፊነት የተሰጣቸውን ተቋማት… እያነጋገረች ሐሳባቸውን ለአንባቢያን አጋርታለች።

ለአብነትም በታህሳስ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ዕትሟ “ሃምሳ ሺህ ሄክታር የሚሸፍን የጣና ሐይቅ ዙሪያ በእንቦጭ አረም ተወሯል” የሚል ዘገባ አስነብባለች። አረሙ አድማሱን ሳያሰፋ መከላከል እንደሚገባም ጠቁማለች። በኵር መስከረም 3 ቀን 2008 ዓ.ም እትሟም አርሶ አደሮች በመቶ ሜትር ርቀት ያሰግሩት የነበረውን ዓሳ የእንቦጭ አረም በመስፋፋቱ ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው ለማምረት እየተገደዱ ስለመሆኑ መግለፃቸውን ዘግባለች።

“በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም በተናጠል ለመከላከል የተደረገው ጥረት ውጤታማ ባለመሆኑ በቀጣይ ሥራው በተቀናጀ መንገድ መከናወን እንዳለበት ተጠቆመ” ስትል ደግሞ በሰኔ 26 ቀን 2009 ዓ.ም ዕትሟ ነበር ያስነበበችው። በሚያዚያ 1 ቀን 2010 ዕትሟ “ከሀገር አልፎ የዓለም ሀብት የሆነው ጣና ሐይቅ ተንከባካቢ ባለቤት አጥቶ በፀና ታሟል እንድረስለት” ስትልም ጥሪ አቅርባለች።

በኵር ስለጣና መወትወቷን በመቀጠል በጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም ዕትሟ “ ጣና ሕልውናውን እያጣ ነው” በሚል ርዕስ የጣና ሕመም የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን በመግለፅ አስነብባለች። “እንቦጭ ከጣና አልፎ ዓባይን እየወረረ ነው” ስትል ያስነበበችው ደግሞ በኅዳር 22 ቀን 2012 ዓ.ም ዕትሟ ነበር። በኵር ስለ ጣና ሐይቅ መወትወቷን በመቀጠል መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም “ ከሕመሙ ጋር የሚታገለው_ ጣና ሐይቅ” በሚል ርዕስ ሰፊ ትንታኔን ለአንባቢያን አጋርታለች።

በኩር የእንቦጭን ጉዳይ በምጣኔ ሀብት አምዷ በሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም  እትሟ  ዋና አጀንዳ ስላደረገችው በጣና የተደቀነውን  ስጋት  “ሐይቁን እንዳናጣው” በሚል አስነብባለች፡፡ በኩር ከምጣኔ ሀብት አምዷ በተጨማሪ  ነሀሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም   “ዕያየነው ወደ መሬትነት በመቀየር ላይ ያለው ጣና ሐይቅ” በሚል  ርዕስ  የኔሃሳብ በተባለው አምዷ ታዝባለች።

በኵር ለጣና ሐይቅ ይህን ያህል በየጊዜው በሠራቻቸው ዘገባዎች  ያለ ጣና ዓባይ ወንዝም ሆነ ዓባይ ግድብ፣ ያለ ጣና የጎርጎራ ፕሮጀክት፣ ያለ ጣና ታሪክና ውበት፣ ያለ ጣና ሽርሽር፣ ዓሳ ማስገር በአጠቃላይ ያለ ጣና ሐይቅ መኖር እንደማይቻል አስገንዝባለች፡፡

በኵር በሰሜኑ ጦርነት በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በቦታው ዘጋቢዎችን በመላክ በኢኮኖሚው ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት አሳይታለች። የተቀዛቀዘው ቱሪዝም እንዲነቃቃም ዘግባለች። እንዲህ እንዲያ እያለች በኩር ጋዜጣ ከተመሠረተችበት ታኅሳስ 7 ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ ልማት እንዲፋጠን፣ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ሀብቶች እንዲጠበቁ፣ ፀጋዎችን በአግባቡ እንድንጠቀም፣ መሠረተ ልማት እንዲስፋፋ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ግብርናው እንዲዘምን፣ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ፣ ኢንቨስትመንቱ እንዲጎለብት… በትኩረት ሠርታለች፤ እየሠራችም ነው።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የታኅሳስ 7  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here