በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኝ ማዘጋጀቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል። ለዚህም 205 ሺህ ሄክታር የተከላ ቦታ ተለይቶ ወደ ሥራ ተገብቷል። የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሐምሌ 01 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ አሁን ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ ዝግጁ ተደርገው እየተተከሉ ነው። አስካሁንም ከ900 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ቢሮው አስታውቋል።
በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረቱ ለበኩር እንደገለጹት፤ እስካሁን (እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2017 ዓ.ም) 119 ሺህ ሄክታር መሬት በችግኝ ተሸፍኗል።
“በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ የሚገኘው የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በተያዘለት ዕቅድ መሠረት እየተካሄደ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኝ ተከላ የሚሳተፈው ኅብረተሰብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍል ተሳትፏል ብለዋል።
ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደዉ ሀገራዊ የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በአማራ ክልል 290 ሚሊዮን ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡ ከተዘጋጁ ችግኞች መካከል የአትክልት እና ፍራፍሬ፣ ሀገር በቀል የደን ችግኞች፣ ለከተማ ውበት የሚያገለግሉ፣ የእንስሳት መኖ እና ሌሎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
እንደ ሀገር ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም 700 ሚሊዮን ችግኞች በአንድ ጀንበር ይተከላሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪ ቀርቧል። ኢትዮጵያ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል አቅዳ እየሠራች ነው።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም