አንዳንድ በሽታዎች ወቅት የማይለዩ እና በማንኛውም ጊዜ ሰውን ሊያጠቁ የሚችሉ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በፊትም የነበሩ ነገር ግን ክረምት መግባቱን ተከትሎ የሚባባሱ እና የስርጭታቸው መጠንም የሚጨምር ነው፡፡ ታዲያ በክረምት ከሚከሰቱ በሽታዎች ለመጠበቅ ሕብረተሰቡ የቁጥጥር እና የመከላከል ሥራን ሳይሰለች እንዲያከናውን ከሰሞኑ የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥሪ አስተላልፏል፡፡ በክልሉ በክረምት ጥንቃቄ ከሚያስፈልጋቸው በሽታዎች መካከልም ኮሌራ፣ ወባ እና ውኃ ወለድ በሽታዎች ይገኙበታል፡፡
ኮሌራ በረቂቅ ጀርሞች አማካኝነት የሚተላለፍ ወረርሽኝ ነው፡፡ አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት በማስከተል ሕሙማን በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋማት ካልሄዱ ሞት ሊያስከትል እንደሚችል ነው የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ የተናገሩት፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት እንደ አማራ ክልል የኮሌራ ወረርሽኝ ታኅሳስ 23 እና 24 ቀን 2017 ዓ.ም የመጀመሪያው ኬዝ በቋራ አካባቢ ከተመዘገበ በኋላ ከመከላከል አቅም ጋር ተያይዞ ቁጥሩ መጨመር እና መቀነስ ያሳያል። በዚህም ሙሉ በሙሉ ኮሌራን ማጥፋት አልተቻለም፡፡
በአማራ ክልል ከታኅሳስ 23 እና 24 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ሁለት ሺህ 316 ሰዎች በኮሌራ የተያዙ ሲሆን 15 ሰዎች ደግሞ ሕይዎታቸው አልፏል፡፡ ኢንስቲትዩቱ እንዳስታወቀው የኮሌራ ወረርሽኝ አበቃ ወይም የለም የሚባለው ለ30 ቀናት ዜሮ ሪፖርት ሲደረግ ነው፡፡ ባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ፣ ደራ፣ ቋራ፣ ጃዊ እና ቡሬ ከተማ አሁንም ወረርሽኙ በየቀኑ እና አልፎ አልፎ ሪፖርት የሚደረግባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ በቋራ ወረዳ በርሜል ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በአንዳሳ ቅዱስ ጊዮርጊስ የጸበል ቦታዎች በተደጋጋሚ ኮሌራ ሪፖርት የሚደረግባቸው ስፋራዎች መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ የጠቆሙት፡፡ ሆኖም ግን ሙሉ በሙሉ በሽታውን ማጥፋት ባይቻል እንኳን ቁጥሩን ግን መቀነስ እንደተቻለ ነው የገለጹት፡፡
ቁጥሩ ሊቀንስ የቻለውም ሁለገብ የሆኑ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች በመሠራታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የበሽታ ቅኝት፣ ሕሙማንን አግኝቶ በፍጥነት እንዲታከሙ በማድረግ፣ ንጹህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እንዲኖር በማስቻል እንዲሁም ወደ ጸበል ቦታ የሚወስዱ የጉዞ ወኪሎችን በተቻለ መጠን ለአንድ ወር ሰዎችን እንዳያመጡ መከልከል በመቻሉ ነው፡፡ በቀን ከ10 እስከ 15 አውቶቡስ ሰው ወደ ቋራ ወረዳ የጸበል ቦታ ይሄድ እንደነበረ የገለጹት ዳይሬክተሩ ይህን ማስቀረት ቢቻልም ሰዎች ከጉዞ ወኪል ውጭ በራሳቸው ስለሚሄዱና በጸጥታ ችግር ምክንያት በሽታውን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንዳልተቻለ ነው የጠቆሙት፡፡ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ሁሉም ሰው አለመተግበሩንም በምክንያትነት አንስተዋል።
ከመጸዳጃ ቤት ውጪ ሜዳ ላይ የሚጸዳዱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆን፣ አሁንም ቢሆን ለሁሉም በቂ የንጹህ ውኃ አቅርቦት አለማዳረስ እንዲሁም ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ወረርሽኙን ዜሮ ማድረግ እንዳልተቻለ ነው የገለጹት፡፡ ሆኖም ከቁጥጥር ውጪ ግን አልሆነም ነው ያሉት፡፡
አሁን ደግሞ ወቅቱ የክረምት ስለሆነ ሕብረተሰቡ የግል እና የአካባቢ ንጽሕናውን መጠበቅ አለበት፡፡ እንዲሁም ወረርሽኙ አለ ተብሎ በተገለጸባቸው አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እና መጸዳጃ ቤት መጠቀም አለበት ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት በክልሉ 54 የሚደርሱ የጸበል ቦታዎች አሉ፡፡ እነዚህ የጸበል ቦታዎች በቀን 500 እና ከዚያ በላይ ሰዎችን የሚያስተናግዱ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ 22 ዋና ዋና የጸበል ቦታዎች ተለይተው አራት አባላት ያሉት ተንቀሳቃሽ የጤና ቡድን ተመድበው እየሠሩ ነው፡፡
ነገር ግን አሁን ዝናብ ከመዝነቡ ጋር ተያይዞ በርካታ ቦታዎች ላይ ኮሌራ ሊፈጠር ስለሚችል ከጤናው መዋቅር ጋር ሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንዲያከናውኑ አሳስበዋል፡፡ ማሕበረሰቡ ኮሌራን ብቻ ሳይሆን በሌሎች ውኃ ወለድ በሽታዎች እንዳይጠቃም ንጽህናውን መጠበቅ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
‘‘የጉዞ ወኪሎች ወደ ጸበል ቦታዎች ሰዎችን መውሰድ ለጊዜውም ማቋረጣቸው ጥሩ ነው፤ አሁንም ቢሆን በሽታው እስካልጠፋ ድረስ ወደእነዚህ ቦታዎች ሰዎችን እንዳይወስዱ እንመክራለን። የጸጥታ መስሪያ ቤቶችም በዚህ ዙሪያ ክትትል እና ቁጥጥር እንዲያደርጉ እናሳስባለን” ነው ያሉት፡፡
ሌላው ዳይሬክተሩ እንደ ክልል ከክረምት መግባቱ ጋር ተያይዞ ለጤና ጠንቅ የሚሆነው የወባ በሽታ እንደሆነ ጠቁመው ሕብረተሰቡ ከወባ እንዲጠበቅ የመከላከል ሥራ እንዲያከናውን ነው የመከሩት፡፡ ዳይሬክተሩ እንደገለጹት አሁን ያለንበት ወቅት መለስተኛ የወባ በሽታ መተላለፊያ ወቅት ነው፡፡ በሳምንታዊው የወባ በሽታ ቅኝትም ቁጥሩ ጨምሯል፡፡ ከመስከረም ወር ጀምሮ ጭማሪው ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ ነው፡፡ በየሳምንቱም ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች በወባ ይያዛሉ፡፡ አሁንም ዝናብ ከመዝነቡ ጋር ተያይዞ ቁጥሩ ሊጨምር ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
ከሐምሌ 01 ቀን 2016 እስከ ግንቦት አጋማሽ 2017 ዓ.ም ድረስ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች በወባ ተይዘው ሕክምና አግኝተዋል፡፡ 91 ሰዎች ደግሞ ሕይዎታቸው አልፏል፡፡
ዳይሬክተሩ አያይዘው እንደገለጹት በክልሉ 40 ወረዳዎች ትኩረት የሚሹ በሚል ተፈርጀው ወባን የመከላከል ሥራ እየተሠራባቸው ነው፡፡ እነዚህ ወረዳዎች የክልሉን 70 በመቶ የወባ ጫና የሚሸፍኑ ናቸው፡፡ ሌሎች በርካታ ወረዳዎችም የወባ በሽታ የሚተላለፍባቸው አሉ፡፡
ወባን ለመከላከል ከሚያስችሉ ሥራዎች አንዱ አጎበር ማሰራጨት ሲሆን በ2015 ዓ.ም ከሦስት ሚሊዮን በላይ አጎበር ተሰራጭቶ እንደነበር ነው የጠቆሙት፡፡ በ2016 ግን እንደ ሀገር አልተሰራጨም፡፡ ይሁንና አሁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አጎበር አላቸው ተብሎ ስለሚታሰብ አጎበርን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በ2017 ዓ.ም መጨረሻም አራት ሚሊዮን አጎበር ይሰራጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሌላው ወባን ለመከላከል የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ መሥራት እንደሚገባ ነው አቶ በላይ በዛብህ የተናገሩት፡፡ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ውኃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስና የማዳፈን ሥራዎች መከናወን አለባቸው፡፡ ባለሙያዎች የወባ ትንኝ የት አካባቢ እንዳለች እና እንደምትራባ ስለሚያውቁ ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ሕብረተሰቡ የራሱን ጤና ራሱ እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡
የወባ በሽታ ምልክቶች የታየበት ሰው ደግሞ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት መሄድ እንደሚኖርበት ነው የመከሩት፡፡ ወደፊት ከፌደራል የጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የፀረ-ወባ ኬሚካል ርጭት በተለዩ እና በጣም ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ ወባ ሁሉንም የሚያጠቃ በመሆኑ ሁሉም በጋራ መከላከል እና መቆጣጠር አለበት ነው ያሉት፡፡
ኩፍኝ እና ትክትክን ጨምሮ ሌሎች ክትባትን በመከተብ መከላከል የሚቻሉ በወረርሽኝ መልክ የሚነሱ በሽተዎች እንዳሉ የገለጹት አቶ በላይ በዛብህ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የተቀናጀ የፀረ-ኩፍኝ ክትባት ዘመቻ በመደረጉ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ (ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም) ድረስ ከሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ተከትበዋል፡፡
በመጨረሻም የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተሩ አቶ በላይ በሀገራችን ስለተከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ማሕበረሰቡ ከበሽታው እንዲጠበቅ የራሱን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም