እስከ አሁን በዓለማችን ከተሰሩ ቴሌቪዥኖች ወይም የምስል እና ድምፅ ማሳያ ቁሶች በሶኒ ኩባንያ የተሰራው 181 ኪሎ ግራም የሚመዝነው በክብደቱ ቀዳሚ መሆኑን ኦዲቱ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል::
ቴሌቪዥኑን የጃፓኑ ኩባንያ 20ኛ የምስረታ ዓመቱን ለማክበር በልዩ ሁኔታ ያመረተው መሆኑ ነው የተገለፀው:: በክብደቱ ቀዳሚ የሆነውን ቴሌቪዢኑን አብዛኛው ሰው ለመግዛት የሚመኘው ግን ደግሞ ዋጋው ውድ እንደነበር ተጠቁሟል::
የቴሌቪዥን ማሳያው ቁስ በጃፓን ለእይታ በበቃበት 1988 እ.አ.አ ዋጋው 2,430,000ዬን ወይም 17500 ዶላር ነበር:: ቴሌቪዥኑ የፊት ለፊት ማሳያው ወይም “ስክሪን” ለተመልካች ዓይን የማያንፀባርቅ፣ ጥርት ያለ ምስልን ከፍ ባለ መጠን ለማሳየት በላቀ ፈጠራ ባለሙያዎች የተጠበቡበት መሆኑ ነው የተጠቆመው::
ከባዱን ቴሌቪዥን ቁስ በግራና ቀኝ ሦስት ሦስት በአጠቃላይ ስድስት ሰዎች ወይም በቁስ ማንሻ “ማሽን” ”ፎርክሊፍት” ብቻ ነው ማንሳት የሚቻለው::
የቴሌቪዥን ቁሱን በሰው ኃይል ለማንቀሣቀስ ይቻል ዘንድም አምራቹ ኩባንያ በእጅ ለማንሳት ማያዣ ቦታዎችን ንድፍ አውጪዎቹ ቀድመው አስበው በስሪቱ ላይ ማካተታቸው ነው የተገለፀው::
በጃፓኑ ሶኒ ኩባንያ የተመረተው ከባዱ የቴሌቪዥን ቁስ በ1990 እ.አ.አ አሜሪካ ሲገባ በዓይነቱ ከባዱ እና በመጠኑም ትልቅ ብቻ ሣይሆን ዋጋውም ውድ በትእዛዝ ለማሰራትም ዓቅምን የሚፈትን ነበር:: በወቅቱ የገበያ ዋጋ 17,500 ዶላር ነበርና::
ኩባንያው በወቅቱ ያመረታቸው ሁለት ብቻ መሆናቸው እና ከዋጋው ውድነት አንፃር በትእዛዝም ሆነ በገበያ ተጨማሪ ምርት አለመቅረቡ ነው በማጠቃለያነት በድረ ገጹ የሰፈረው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም