በኲር እና የውጪ ዘገባዎቿ

0
161

ታኅሳስ 07 ቀን 1987 ዓ.ም የተመሰረተችው በኩር ጋዜጣ ለክልሉ ሕዝብ የክልሉን የልማት መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ ከተቋቋመችበት ዋና ዓለማ በተጓዳኝ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መረጃዎችን ለአንባቢያን ተደራሽ እያደረገች ሦስት ዐሥርት ዓመታትን አልፋለች።

ከ1987 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ያለው የበኩር የ30 ዓመታት የውጭ ዘገባ ጉዞዋ እንደሚያሳየው የተለያዩ የእድገት ደረጃዎችን አልፏል። ከአጫጭር የውጭ ዜናዎች ሽፋን እስከ ትንታኔ የደረሰ እድገት ከጊዜ ጊዜ የተመዘገበባት በኩር ከሀገራዊ ፋይዳው እና ጠቀሜታቸው አንፃር የተመረጡ የውጭ ዜናዎችን ሽፋን ሰጥታለች። ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ (በዋናነት አፍሪካ) ወቅታዊ ክስተቶችን በማነፍነፍ ለአንባቢ ተደራሽ ይደረግ እንደነበር ያለፉ ሕትመቶች ዋቢዎች ናቸው።

ጋዜጣዋ ሕትመት ከጀመረችበት ዘመን ጀምሮ በአግባቡ ተሰድረው የሚገኙት ጋዜጣዎች እንደሚያስረዱት በተለይ ከ1990ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ያሉት እትሞች ሰፋ ያለ ወቅቱን የተንተራሰ የውጭ መረጃ ከዓለም ዙሪያ በሚለው አምድ ውስጥ ይስተናገድ ነበር። ከዚህ አኳያ በወቅቱ እየተከሰቱ ከነበሩ ተፈጥሯዊ አደጋዎች አንፃር የባሕር ውስጥ ተራሮች ሰንሰለቶች ከታሪካዊ ዳራው በመንደርደር አሁን ያለውን ሁኔታ ለማስቃኘት የተቻለበት ዘገባ ቀርቦ ነበር። ታላቁ የሱናሜ አደጋን የተመለከተ መጣጥፍም ተስተናግዷል።

ተጨማሪ በ30 ዓመታት ጉዞ ውስጥ የውጪ ሀገር ዘገባ አብነቶችን እናንሳ፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ በተፈጥሮ የታደላቸውን ፀጋ በመጠቀም በኢንዶኔዥያ የደረሰውን የመሬት መንቀጥቀጥ ከርቀት በመስማት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ስለታደጉት ዝሆኖች የተሠራው ዘገባ ይገኝበታል፤ ታሪክ በአውዳሚነቱ በመዘገበው በዚህ የተፈጥሮ አደጋ ወደ ተራራሮች ባልተለመደ መልኩ እየተጯጯሁ የሚሮጡትን ዝሆኖች በመከተል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማትረፋቸውን አስመልክቶ ዝሆኖች ትኩረት ይሻሉ የሚል እንድምታን አጣምሮ የያዘ ሰፊ ትንታኔ አስነብባለች።

ከ2000 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ በኩር ማሻሻያ በማድረግ የውጭ ዜናዎች እና ከዓለም ዙሪያ በአንድ ገፅ የሚታተሙበት ዘመን መጣ። ከ2006 ዓ.ም አንድ የበኩር እትም ላይ እንደተመለከትነው በውጭ ዜናዎች አምድ ስር በወቅቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበሩትን የቀድሞው የፍልስም ፕሬዝዳንት ያሲር አራፋት በተፈጥሯዊ ሞት መሞታቸውን የተመለከተ እና ዘመናዊ ባርነት ሊቆም እንደሚገባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማሳሰቡን የተመለከተ ዘገባ ተዘግበው እናገኛለን።

ያሲር አራፋት በጭንቅላት ዕጢ እና በአንጀት ቁስለት መሞታቸው ተገልፆ የነበረ ቢሆንም ከዓመታት በኋላ ግን በአደገኛ ጨረር ተመትተው እንደሞቱ መወራት ጀምረ። ይህን ውዝግብ ለማጥራት ታዲያ የተለያዩ አጥኚ ተቋማት የተሳተፉበት ምርመራ ከተደረገ በኋላ ያሲር አራፋት ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ መሞታቸው መረጋገጡን ይፋ በማድረግ በኩር ከቀዳሚዎቹ የመረጃ ምንጮች አንዷ በመሆን ወቅታዊ መረጃን አስነብባ ነበር።

በሌላ ዜናም በዓለም እየተስፋፋ የመጣው ዘመናዊ ባርነት ሊቆም እንደሚገባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማሳሰቡን በኩር በዚያው እትም ተንትናለች። የወቅቱ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን እንዳሳወቁት በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሴቶች፣ ወንዶች እና ሕፃናት ለተለያዩ አካላዊ እና ፆታዊ ጥቃት እንዲሁም የጉልበት ብዝበዛ  እንዲዳረጉ በመሆን ለዘመናዊ ባርነት ተዳርገዋል በማለት ነበር የችግሩን አሳሳቢነት ያብራሩት። በእነዚህ ወገኖች የማያቋርጠው የስቃይ ጩኸት እንደቀጠለ እና ተሰሚነት እንዳጣም ተዘግቧል።

ከዚህ ጋር በተገናኘ በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለሴተኛ አዳሪነት እና ለጉልበት ብዝበዛ መዳረጋቸውን የዓለም አቀፍ ስደተኞችን መረጃ ዋቢ በማድረግ የችግሩን አሳሳቢነት በመግለፅ አሁኑኑ በቃ ሊባል እንደሚገባ በመጠቆም በኩር ተንትናለች።

አወዛጋቢውን የፌስቡክ መረጃ ዘረፋን በተመለከተ በኩር በውጭ ትንታኔ አምዷ ላይ በ2010 ዓ.ም እትሟ ሰፊ መረጃዎችን በማካተት አስነብባለች። በፌስቡክ ተጠቃሚዎች ላይ የተደረገውን ጥናት መነሻ በማድረግ በዘገባው እንደተመላከተው የመረጃ ዘራፊዎቹ የሰዎችን የፌስቡክ መረጃ የሚፈትሽ መተግበሪያ በመፍጠር ወደ ሥራ መግባታቸው ታውቋል፤ በዚህም ከ87 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች የግል መረጃ ተጎርጉሯል ነው የተባለው። ይህም የፌስቡክን የግለሰብ መረጃ በቀላሉ እንደሚበረበር ማሳያ ከመሆኑም በላይ መስራቹን ማርክ ዙከርበርግን ለክስ ዳርጎት እንደነበር ተዘግቧል።

እ.አ.አ መስከረም 11 ቀን 2001 በተለይ በአሜሪካዊያን ዘንድ በክፉ የምትታወስ ዕለት ናት፤ ይህ ቀን አሜሪካ እጅግ አሰቃቂ የሽብር ጥቃት  ያስተናገደችበት እና በርካታ ዜጎቿንም ያጣችበት ዕለት ነበር፡፡ ይህን አሰቃቂ ክስተት ለአንባቢያን በማድረስም በኩር ከግንባር ቀደሞቹ የመረጃ ምንጮች ትጠቀሳለች፡፡

ከክስተቱ በኋላ ተከትለው የመጡ ዓለም አቀፋዊ ክስተቶችንም በኩር ተከታታይ ሽፋን ተሰጥታለች ነበር። በተመሳሳይ የአሜሪካ ጦር በአፍጋኒስታን እና በኢራቅ ያደረጋቸውን የፀረ ሽብርተኝነት ጦርነቶች እና ያስተለውን መዘዝ በመዘገብ ሽፋን ሰጥታለች። በተጨማሪም የአረቡን የፀደይ አብዮት በመዘገብ ረገድ በኩር ዓለም አቀፍ ሽፋን ሰጥታለች። የአይ ኤስ አይ ኤስ የሽብር ጥቃቶችን ተከታትሎ በመዘገብም የራሷን ሚና ተጫውታለች።

በአጠቃላይ በኩር በ30 ዓመታት ጉዞዋ ከሀገራችን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ በመነሳት እና ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ባስከበረ መልኩ በርካታ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ስትዘግብ ቆይታለች፤ በዘገባዎቿም ከመገኛችን የአፍሪካ ቀንድ እስከ ሩቅ ምሥራቅ በመሻገር ጥልቅ ዘገባዎችን ለንባብ ስታበቃ ቆይታለች፡፡ ይህንን ጉዞም አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የታኅሳስ 7  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here