በኵር – የአሚኮ የ30 ዓመታት ጉዞ መነሻ

0
192

ለዛሬው ግዙፍ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተቋም መመስረት መሠረት የተጣለው በታኅሳስ 7 ቀን 1987 ዓ.ም ነው፡፡ በኵር ጋዜጣ ደግሞ መሠረቱ ናት፡፡

በእርግጥ የመጀመሪያው የበኵር ጋዜጣ ህትመት ጅማሮውን የሚያደርገው በልዩ እትም ሐምሌ 19 ቀን 1986 ዓ.ም ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያዋ ክልላዊ ጋዜጣ እንደሆነች የሚነገርላት በኵር ጋዜጣ በወቅቱ በፊት ገጿ  “የክልል ሶስት አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ተከፈተ” በሚል አብሥራለች። በኵር በልዩ እትሟ የዜና ገጽን ጨምሮ በስድስት አምዶች ዘገባዎቿን ተደራሽ ስታደርግ በአሥር ሺህ ቅጂዎች ከሚሊዮኑ ሕዝብ ጋር እንደተገናኘች የበኵር ጋዜጣ መዝናኛ አምዶች ምክትል ዋና አዘጋጅ አቶ አባትሁን ዘገዬ አስታውቋል፡፡

ጋዜጣዋ መደበኛ ህትመቷን የጀመረችውም በልዩ እትም ከሕዝብ ጋር ከተወዳጀች ከአምስት ወራት በኋላ ታኅሳስ 7 ቀን 1987 ዓ.ም መሆኑን ጋዜጠኛ አባትሁን አስታውሷል፡፡ ዘገባዎቿን በስምንት ገጽ ሰንዳ በሳምንት በአራት ሺህ ቅጂዎች ለሕዝብ ታደርስ እንደነበርም ጠቁሟል፡፡

በወቅቱ የሁሉም ዐይኖች ማረፊያ በኵር ጋዜጣ እንደነበረች፣ ለዚህም ማሳያው የምስረታ አንደኛ ዓመቷን ስታከብር በአንድ ዓመት ብቻ 800 ደብዳቤዎች እንደደረሷት ጋዜጠኛ አባትሁን ጠቁሟል፡፡ ይህ ሁሉ ሕዝባዊ ልሳንነት ዕውን የሆነው ግን በቂ እና የሰለጠነ የሰው ኀይል ባልነበረበት፣ የተመቸ ቦታ በሚናፈቅበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንደነበር አስታውሷል፡፡ በኵር በምስረታ ዘመኗ በአራት ሺህ ቅጂ ብቻ ለሕዝብ ትደርስ የነበረው ስርጭቷ ዛሬ ላይ ዓለም አቀፍ መሆኗን ከዓመት ዓመት እየታየው ላለው ለውጧ ማሳያ በማድረግ አመላክቷል፡፡

በጋዜጠኛ መዝሙር ሀዋዝ  “የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ዕድገት” በሚል በተጻፈው መጽሐፍ የበኵር ጋዜጣ ተቀዳሚ ዓላማ ለረዥም ጊዜ የቆየውን ትልቅ የመልማት ጥያቄ እልባት በመስጠት ረገድ አጋዥ መሳሪያ ሆና ታገለግላለች በሚል ታምኖባት እንደሆነ ያመላክታል፡፡

የበኵር ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ ጌታቸው ፈንቴ በበኩሉ ጋዜጣዋ “በኵር” የሚል ስያሜን ያገኘችው በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የመጀመሪያዋ ክልላዊ ጋዜጣ መሆኗን ተከትሎ ነው፡፡ ጥቁር እና ነጭ ቀለም የህትመቱ መልክ እንደነበርም  አስታውሷል፡፡ መረጃዎችን በህትመት ለብዙኃኑ ለማድረስ ‘ታይፕ ራይተር’ መጠቀም ግድ ይላል። ከዚያም በ’ከተር’ መቆራረጥ፣ በሙጫ ማላጠቅ (ማጣበቅ)፣ እንደ ቂጣ ጋግሮ በተዘጋጀለት ወረቀት ላይ ተለጥፎ ወደ ማተሚያ ቤት መላኩ የሥራውን አድካሚነት ማሳያ አድርጎ አንስቷል፡፡

የጋዜጣ ህትመት ቁጥር አናሳ መሆን፣ የስርጭት ተደራሽነቱ ተሽከርካሪ በሚገባባቸው አካባቢዎች ብቻ መወሰኑ በኵር በምስረታ ዘመኗ ወቅት የተስተዋሉ ውስንነቶች እንደነበሩ ጋዜጠኛ ጌታቸው ገልጿል፡፡

የህትመት ሥርጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ሄዶ አሁን ላይ እስከ 10 ሺህ ቅጂ መድረሱን፣ በዓለም ላይ በኵርን ፈልገው ለሚያነቧትም በዲጅታል ሚዲያ አማራጭ ተደራሽ መሆኗን ደግሞ ለዕድገቷ ማሳያ አድርጎ አንስቷል፡፡

በኵር ጋዜጣ በ30 ዓመት ጉዞዋ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ ባህል እንዲሆን፣ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ መጫወቷንም የሚያረጋግጡት በርካቶች ናቸው፡፡ ለአብነት በኵር ጋዜጣ ሀገሪቱ የምትከተለውን ግብርና መር ስትራቴጂ ዕውን ለማድረግ በከፍተኛ ትጋት መሥራቷን ጋዜጠኛ ጌታቸው አረጋግጧል፡፡ ምርት እና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ አዳዲስ አሠራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በአርሶ አደሩ ዘንድ ለማስረጽ ጋዜጠኞች ረጅም መንገድን በእግር እና በፈረስ ተጉዘው ሽፋን ይሰጡ የነበረበትን ሂደት ለሥራ የመሰጠት ማሳያ በማድረግ አስታውሷል፡፡

በኵር ለአሁኑ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) መመስረት ትልቅ አቅም መሆኗንም ጋዜጠኛ ጌታቸው ያስታውሳል፡፡ በሕትመት ዘርፍ ወደ ሕዝብ ይደርስ የነበረው መረጃ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ በሚያደርግ አግባብ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ በሬዲዮ፣ ቴሌዥን እና ዲጅታል ሚዲያ ዕውን መሆን ችሏል፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የምልክት ቋንቋን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች መረጃዎችን እና ማስታወቂያዎችን በመላው ዓለም ለሚገኙ አንባቢያን፣ አድማጮች እና ተመልካቾች እንዲያስተጋባ መሠረቱ 1987 ዓ.ም መሆኑንም አስታውቋል፡፡ የሀገሪቱን ዕድገት ዕውን ለማድረግ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 859 ሠራተኞችን አሰባስቦ እየሠራ መሆኑ ሌላው የ30 ዓመት ጉዞው ስኬት ማሳያ በማድረግ አንስቷል፡፡

በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ በማገልገል ላይ ከሚገኙት ሠራተኞች መካከል በኮርፖሬሽኑ የይዘት ዕቅድ ማማከር፣ አጀንዳ አወቃቀር እና የኢዲቶሪያል ፖሊሲ ዳይሬክተሩ ጋዜጠኛ  በቀለ አሰጌ ይገኝበታል፡፡ ለዛሬው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን መመሥረት በኵር ጋዜጣን እንደ መሠረት ያነሳል፡፡ “በኩር ጋዜጣ ታኅሳስ 7 ቀን 1987 ዓ.ም ባትመሠረት ኖሮ ዛሬ ላይ ያሉት ሁለት የቴሌዥን እና ሰባት ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ በኵርን ጨምሮ አራት ጋዜጦች ዕውን ሊሆኑ አይችሉም ነበር” ብሏል፡፡

በበኵር ጋዜጣ የተጀመረው ልምድ ግዙፉ የአማራ ክልል ሕዝብ የሚፈልገውን መረጃ በተለያዩ የብዙኃን መገናኛ አውታሮች እንዲያገኝ የሚያስችሉ ተቋማት እንዲገነቡ  ማስቻሉን ጠቁሟል፡፡ “የአሚኮ ዕድገት ዛሬ ላይ ከደረሰበት ደረጃ ተወስኖ መቅረት የለበትም” ያለው ጋዜጠኛ በቀለ፣ ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን አማራጮቹ ዓለም ዓቀፍ ተደራሽነት እንዲኖራቸው ታሳቢ አድርጎ ከመሥራት በተጨማሪ የሕዝብን ችግር ፈልፍለው የሚያጋልጡ እንዲሆኑ መትጋት እንደሚገባም አስገንዝቧል፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ በበኩላቸው የበኵር ጋዜጣ መመስረት ለዛሬው ግዙፍ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እውን መሆን  መሠረት መሆኗን አንስተዋል፡፡ በፈተና ውስጥ ሆኖ ሥራ መጀመር፣ ማስቀጠል፣ ማሳደግ እና ትልቅ ተቋም የማድረግ ልምድ ከመሥራቾቹ መውሰድ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ በኵር መረጃን በህትመት ተደራሽ ለማድረግ የጀመረችው በውስን የሰው ኅይል፣ የተመቸ ቦታ እና እምብዛም የመረጃ ምንጭ ባልነበረበት ዘመን መሆኑን ለዚህ ማሳያ አድርገው ገልጸዋታል፡፡

የያኔዎቹ መሥራቾች ችግርን ተቋቁመው በማለፋቸው አሚኮ ግዙፍ ተቋም ሆኖ በብዙ የመገናኛ ብዙኃን አማራጮች ለሚሊዮኖች ተደራሽ እንዲሆን፣ ብዝኃ ቋንቋ መገለጫው እንዲሆን፣ ብዙ የሰው ኅይል እንዲያስተዳድር ሆኗል፡፡ አሁን በኮርፖሬሽኑ ሥር ያለው ሙያተኛ አሚኮ 30 ዓመታትን እንዲደርስ ካደረጉ መሥራቾች በቀጣይ ዘመናትን እንዲሻገር ኃላፊነትን መውሰድ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ አሚኮን የማሻገር ሂደቱ እንዳይሳካ ሊያደርጉ የሚችሉ እንደ ሀብት ውስንነት፣ የቴክኖሎጂ፣ የተሽከርካሪ እጥረት  እና ሌሎች መሰል ችግሮች… በሚያጋጥሙበት ወቅት ችግርን ተቋቁሞ በመሥራት ኮርፖሬሽኑን የበለጠ ማሳደግ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የታኅሳስ 7  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here