በወባ በሽታ የሚሞቱ ሕጻናትን እንታደግ

0
58

በተባበረከት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) መረጃ እንደሚያመላክተው በወባ ምክንያት በየደቂቃው የአንድ ሕጻን ሞት ያልፋል። በተመሳሳይ የዓለም ጤና ድርጅ ባወጣው መረጃ ደግሞ እ.አ.አ በ2022 በዓለም አቀፍ ደረጃ 249 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ ተጠቅተዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 608 ሺህ ያህሉ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከሟቾች መካከል 76 በመቶ ያህሉ ከአምስት ዓመት በታች ሕጻናት ስለመሆናቸውም መረጃው አክሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያትተው የወባ በሽታ ስርጭት ዓለምአቀፋዊ ገጽታ ያለው ቢሆንም በድሃ ሀገራት ችግሩ የከፋ ነው። ለአብነትም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በሽታው በገዳይነቱ ከቀዳሚዎቹ መካከል ተጠቅሷል።

በሽታው የተለያዩ የወረርሽኝ ወቅቶች እንዳሉት የሚጠቁመው መረጃው ይህም እንደየ ሀገራቱ የአየር ንብረት መለዋወጥ (ከወቅቶች ጋር) ይወሰናል። እ.አ.አ ከ2010 እስከ 2020 በወባ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር በ36 በመቶ መቀነስ ተችሎ ነበር። ለዚህም የተደራጀ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እና የመከላከል ተግባራት መጠናከራቸው እንደሆነ ነው ያመላከተው።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስርጭቱ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ይገኛል። በ2023 እ.አ.አ 263 ሚሊዮን ሰዎች በወባ እንደተጠቁ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። ከዚህ ውስጥ 597 ሺህ ሰዎች እንደሞቱም መረጃው ያመላክታል።

የወባ በሽታ ምንነት እና መንስኤ

ወባ ፕላዝሞዲየም በተባለ ተሕዋስ የሚመጣ ለሕይወት አስጊ እና በሴቷ የወባ ትንኝ (የወባ በሽታ ተሸካሚ) ንክሻ አማካኝነት የሚመጣ በሽታ ነው።

የፕላዝሞዲየም ጥገኛ ተውሳኮች ወባን ያስከትላሉ። የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ እንዳደረገው ሰዎችን ሊበክሉ የሚችሉ አምስት ዓይነቶች የፕላዝሞዲየም ጥገኛ ተውሳኮች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ፕላዝሞዲየም ፋልሲፓረም (Falciparum) እና ፕላዝሞዲየም ቫይቫክስ (Vivax) በጣም የተለመዱ ሲሆኑ ፋልሲፓረም የተባለው ደግሞ ከባድ ሕመምን በማስከተል በገዳይነቱ ይታወቃል።

በወባ እንዴት ልንያዝ እንችላለን?

ሴቷ የወባ ትንኝ የተበከለውን ሰው ስትነክስ ጥገኛ ተውሳኩን (ፕላዝሞዲየም) ትሸከማለች (ትይዛለች)። በዚህ ወቅት ጤነኛን ሰው ስትነክስ ተህዋሱን ወደጤነኛው ይተላለፋል። ጥገኛ ተውሳኩም በጉበት ውስጥ ተባዝቶ ወደ ደም ውስጥ ይሰራጫል። በዚህ መንገድ የበሽታው ስርጭት ይስፋፋል።

ከዚህ በተጨማሪም በእርግዝና ወይም በወሊድ እንዲሁም በደም ልገሳ ወቅት በሽታው ሊሰራጭ እንደሚችል የድርጅቱ መረጃ ያመላክታል።

ምልክቶች

የወባ በሽታ ምልክቶች ከቀላል እስከ ከባድ ምልክቶችን ያሳያል። ከሰባት እስከ 14 ባሉት ቀናት ውስጥ እና ከእነዚህ ቀናት በኋላ ምልክቶች ይከሰታሉ። ለበርካታ ቀናት ያህልም ምልክት ላይከሰት ይችላል።

ብዙውን ጊዜ እንደ የጉንፋን ሕመም ምልክቶች የሚከሰቱ ሲሆን ከዚያም እየተባባሰ ይሄዳል። ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት (ማንቀጥቀጥ)፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ ሕመም፣ ድካም፣ የመተንፈስ ችግር፣ ተቅማጥ፣ ማቅለሽለሽ ወይም ማስታወክ፣ የቆዳ ቢጫ ወይም የዓይን ቀለም ነጭ መሆን ዋና ዋና ምልክቶች ናቸው። ከዚያም አለፍ ሲልም ራስን እስከ መሳት የደረሰ ከባድ የሕመም ምልክት ሊከሰት ይችላል።

መከላከያ

የወባ በሽታ መከላከያ ዘዴዎች በዋነኝነት በሁለት ክፍል ይከፈላሉ፤ በሽታውን አስተላላፊ የወባ ትንኝ መራቢያ አካባቢ በማጽዳት በበሽታው ከመያዝ በፊት መከላከል (Vector control) እና ከተያዝን ደግሞ በሕክምና (Chemoprevention) የመከላከል አማራጮች ናቸው።

በበሽታው ከመያዝ በፊት የመከላከያ አማራጮችን መተግበር ቀዳሚው ተግባር ነው። በኬሚካል የተቀባ የአልጋ አጎበር መጠቀም፣ የወባ ትንኝ መራቢያ አካባቢን (ረግረጋማ ቦታ፣ ቆሻሻ …) ማጽዳት ውጤታማ የመከላከል ስልቶች ናቸው።

ከዚህ ባለፈ በሕመሙ ከተያዝን ደግሞ በቶሎ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ይገባል። አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ የታዘዙ መድኃኒቶችንም በአግባቡ መውሰድ እንደሚገባ የዓለም ጤና ድርጅት በድረ ገጹ ያሰፈረው መረጃ ይመክራል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩትም መስከረም 16 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጠዉ ጋዜጣዊ መገለጫ ደግሞ የወባ ስርጭት ከባለፈዉ ዓመት ጋር ሲነጻጸር መቀነሱን አስታውቋል፤ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክር በላይ በዛብህ እንዳሉት ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት በአንድ ሳምንት ብቻ እስከ 80 ሺህ የወባ በሽታ እንዳለባቸው የሚጠረጠሩ ሪፖርት ይደረግ እንደነበር አስታውሰዋል:: ከሐምሌ ወር 2017 ዓ..ም እስከ መስከረም ወር አጋማሽ 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ 881 ሺህ ተጠርጣሪዎች ተለይተው ከዚህ ውስጥ ከ279 ሺህ በላይ ለሆኑ ወባ ለተገኘባቸው ሕክምና ተሰቷል ብለዋል:: ይም ካምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ማሳየቱን አመላክተዋል::

የወባ ትንኝ መራቢያ አካባቢዎችን ማስወገድ፣ ማጽዳት፣ አሰሳ ማድረግ፣ ግንዛን ማሳደግ ውጤታማ የመከላል ተግባራት እንደነበሩ ተናግረዋል፤ የአርብ እጆች የወባን ወረርሽኝ ይገታሉ የበሚል መሪ ሃሳብ የተደረገው ቅንጅታዊ የመከላከል ሥራም ውጤታማ እደነበር ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት::

ጤና አዳም

ወባ

እንዴት ይተላፋል?

ሴቷ የወባ ትንኝ የተበከለውን ሰው ስትነክስ ጥገኛ ተውሳኩን በመሸከም ጤነኛን ሰው ስትነክስ።

በእርግዝና ወይም በወሊድ፣

በደም ልገሳ፣

ምልክቶች

ትኩሳት፣

ብርድ ብርድ ማለት (ማንቀጥቀጥ)፣

ራስ ምታት፣

የጡንቻ ሕመም፣

ድካም፣

የመተንፈስ ችግር፣

ተቅማጥ፣

ማቅለሽለሽ ወይም ማስታወክ፣

የቆዳ ቢጫ ወይም የዓይን ቀለም ነጭ መሆን ዋና ዋና ምልክቶች ናቸው።

ከዚያም አለፍ ሲልም ራስን እስከ መሳት የደረሰ ሕመም።

መከላከያ

የወባ ትንኝ መራቢያ አካባቢን በማጽዳት መከላከል፣

ሕክምና ማግኜት፣

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here