በውዝግብ የተቋጨዉ የአፍሪካ ዋንጫ

0
146

የ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ በራባት ፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ሲከወናወን ታሪክ ራሱን በልዩ ድራማዊ ክስተት ጽፎ አለፏል። የፍሜው ጨዋታ በአስተናጋጇ ሀገር ሞሮኮ እና በሴኔጋል መካከል የተደረገ ሲሆን መደበኛው 90 ደቂቃ ያለ ምንም ግብ ነበር የተጠናቀቀው። በባክነው የደቂቃ ጭማሪ የመሀል ዳኛው በቫር (VAR) ታግዘው ለሞሮኮ የሰጡት አወዛጋቢ የፍጹም ቅጣት ምት ውሳኔ ነገሮች ወደ ትርምስ እንዲቀየሩ አድርጓል።

በፍጻሜ ጨዋታ አንድ ቡድን ሜዳውን ለቆ ሲወጣ በዓለም እግር ኳስ ታሪክ እንግዳ  ክስተት ነው። የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን በአሰልጣኙ ትዕዛዝ ይህን አደርገዋል፤ ለተመልካቹ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ስታዲየሙ ውስጥ የነበረው ደስታ ወደ ግራ መጋባት እና ስጋት ተለወጠ።  ጨዋታውም ለ15 ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር።

ጨዋታው በዚህ ከተቋረጠ ዋንጫው በፎርፌ ለሞሮኮ ይሰጣል? ወይስ ጨዋታው ይደገማል? የሚለው ጥያቄ በሁሉም ሰው አእምሮ ውስጥ ይመላለስ የነበር ጥያቄ ነው። በመጨረሻም ከረጅም ድርድር በኋላ የሴኔጋል ተጫዋቾች ፊታቸው ላይ የቁጭት እና የልበ ሙሉነት ስሜት እየተነበበ ወደ ሜዳ ተመለሱ። ድራማው ግን በዚህ አላበቃም፤ ይልቁንም ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋገረ። የተገኘውን ወሳኝ የፍጹም ቅጣት ምት ብራሂም ዲያዝ ሳተ። ያቺ ቅጽበት የጨዋታውን ስነ ልቦናዊ የበላይነት ሙሉ በሙሉ የቀየረች ነበረች።

እናም ጨዋታው ወደ 30 ደቂቃ ተጨማሪ ሰዓት ተሸጋገረ። ቀሪው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለሞሮኮዎች ገሃነም ይመስል ነበረ፤ ለሴኔጋሎች ደግሞ እንደ ጥሩ ህልም ጣፋጭ ነበር ማለት ይቻላል። በመጨረሻም ሴኔጋል ድራማዊ ክስተት በተሞላበት አስተናጋጇን ሀገር አሸንፋ ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካን ክብር ተቀዳጀች።

ሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳችው እ.ኤ.አ በ1976 አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ እንደ ዘንድሮው ለዋንጫው የቀረበችበት ጊዜ አልነበረም። የዘንድሮውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም አለመቻላቸው ወርቃማው ትውልድ የእግር እሳት ይሆንበታል ተብሎ ይገመታል።

በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ከዚህ በፊት አስተናጋጅ ሀገራት ዋንጫውን ለማንሳት ሲቸገሩ ይስተዋላል። ሞሮኮ ይህንን ታሪክ ቀይራ በራባት ዋንጫውን ታነሳለች ተብሎ ቢጠበቅም አልተሳካም። የሞሮኮ ደጋፊዎች በፌሽታ ስቴዲየም ገብተው በለቅሶ ወጥተዋል።

በዚህ የፍጻሜ ጨዋታ የቡድኑ አምበል ሳዲዮ ማኒ ያሳየው ብስለት እና መሪነት ለሴኔጋል ድል  የጀርባ አጥንት እንደሆነ የማይካድ ሀቅ ነው። የ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ለሳዲዮ ማኒ የሽኝት ዋንጫ ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ ምርጥ ተጫዋችነት ወደ የአፍሪካ ምርጥ መሪነት የተሸጋገረበት መድረክ  ጭምር ሆኖ ተመዝግቧል። ሳዲዮ ማኒ በ2025 የአፍሪካ ዋንጫ እንደ ጀግና ወደ ሞሮኮ አቀንቶ እንደ ንጉሥ ተሰናብቷል።

በድምቀት የተጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ በውዝግብ እና በትርምስ ተጠናቋል። በተለይ የመጨረሻ 30 ደቂቃ ከሜዳ መውጣት፣ ከስጋት፣ ካልተሳካው ፍጹም ቅጣት ምት ሙከራ እና ከአስደናቂ ግብ ጋር ተዳምሮ የ2025ቱን ፍጻሜ የእብዶች ምሽት አሰኝቶታል ይላል ሱፐር ስፖርት።

ይህ ውድድር የተጠናቀቀው በታሰበው መንገድ ሳይሆን እጅግ ድራማዊ እና ልብ አንጠልጣይ በሆነ ክስተት ነው። የድግሱ ደረጃ እና ጥራት ግን ጥንቅቅ ያለ እንደነበር በግልጽ ታይቷል፤ እንግዶችም መስክረዋል። ካዛብላንካ፣ ራባት፣ ታንጂር፣ ማራካሽ፣ ፌዝ እና አጋዲር ከተሞች ያቀረቡት የስታዲየም ጥራት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ከሚደረግባቸው ስቴዲየሞች  የማይተናነስ መሆኑን እኛም  በቴሌቭዥን መስኮት ተመልክተናል።

አል ቡራቅ (Al Boraq) የተሰኘው ፈጣን ባቡርም የመጓጓዣ ፍሰቱን ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል። ስታዲየሞቹ በተሟላ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት በተለይም በድብልቅ የሣር አይነቶችን የለበሱ መሆናቸው ኳሱ በሜዳ ላይ የሚኖረውን እንቅስቃሴ አሳምሮታል። የደጋፊዎች አቀባበል፣ የሆቴሎች ብዛት እና የዲጂታል ቲኬቲንግ ስርዓት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ የቤት ሥራ የሰጠ ሆኖ አልፏል- 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ። ከዚህ ቀደም በአህጉሩ ካየናቸው ውድድሮች በተለየ መልኩ እጅግ ሞቅ ያለ እና ዘመናዊ የድጋፍ ስልት የተላበሰ ልዩ ድባብ ታይቶበታል።

የዘንድሮው አፍሪካ ዋንጫ የቀድሞውን ባህላዊ የአፍሪካ እግር ኳስ የለወጠ ነው። በውድድሩ ጎልቶ የታየው ኳስን ከኋላ መስርቶ መጫወት የሚያስችለው የታክቲክ ለውጥ ነው። ግብ ጠባቂዎች ኳስን በእጃቸው ከማዳን ባለፈ ልክ እንደ 11ኛው የሜዳ ተጫዋች በእግራቸው በመጫወት የቡድናቸውን የማጥቃት እንቅስቀሴ ሲያግዙ ታይተዋል። የደቡብ አፍሪካው ሮንዌን ዊሊያምስ፣ የሞሮኮው ያሲን ቦኖ እና የናይጄሪያው ስታንሊ ኒዋባሊ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆናቸውን የሱፐር ስፖርት መረጃ አመልክቷል።

ውድድሩ ከዳኝነት ውዝግብ የፀዳ እንዳልነበር ብዙዎች ቅሬታቸውን ያነሳሉ። በተለይ አልጄሪያ ከናይጄሪያ ጋር ባደረጉት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ የቪዲዮ ረዳት ዳኛ (VAR) አተገባበር ላይ የተነሳው ቅሬታ የውድድሩን ድባብ አጨልሞት ነበር። አልጄሪያውያን ሁለት ግልጽ የፍጹም ቅጣት ምት ውሳኔዎችን ተከልክለናል በሚል ለካፍ (CAF) ክስ ማቅረባቸው አይዘነጋም።

እንደ ሞሮኮ እና ግብፅ ያሉ ቡድኖች ኳስ ሲቆጣጠሩ ወደ 3-2-5 ቅርጽ በመቀየር የመስመር ተከላካዮቻቸው (Full-backs) እንደ ተጨማሪ አማካይ ወይም አጥቂ ሆነው ሲያገለግሉ ተስተውለዋል። የሞሮኮው አሽራፍ ሀኪሚ በዚህ ሚና የዓለም ምርጡ መሆኑን በድጋሚ አስመስክሯል። ሀኪሚ ከመስመር እየተነሳ ወደ መሀል ሜዳ በመግባት (Inverted Fullback role) የተጋጣሚን የመከላከል ቅርጽ ሲያዛባም ተመልክተነዋል። ይህም አሰልጣኞች የአውሮፓን ዘመናዊ ታክቲክ ከአፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዋሃድ ረገድ የሄዱበትን ርቀት ያሳያል ተብሏል።

በዚህ ውድድር የጨዋታው ውጤት በአብዛኛው የተወሰነው በሽግግር ወቅት ነው። ኳስ ከተቃራኒ ቡድን ሲቀማ ለማጥቃት የሚደረገው ሽግግር ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈጣን ሆኖ ታይቷል። የነሐስ ሜዳሊ ተሸላሚዋ ናይጄሪያ እና ሻምፒዮኗ ሴኔጋል በዚህ ረገድ ምርጥ ቡድኖች ነበሩ። የናይጄሪያው ቪክቶር ኦሲሜሄን እና አዴሞላ ሉክማን ኳስ እንደያዙ በሽርፍራፊ ሴከንዶች ውስጥ በተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርሱ ታይቷል።

እንደ ማሊ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያሉ ቡድኖች ወደ ኋላ አፈግፍገው በመከላከል ለታላላቅ ቡድኖች ራስ ምታት ሆኖ ተስተውለዋል። እነዚህ ቡድኖች የመሀል ሜዳውን በማጥበብ ታላላቅ ብሄራዊ ቡድኖችን ወደ መስመር እንዲወጡ ሲያስገድዱ እና በረጅም ኳስ የመልሶ ማጥቃት ሲሰነዝሩ እንደነበር አይዘነጋም። ይህ ታክቲካዊ ፉክክር ውድድሩን የአካላዊ ጉልበት ብቻ ሳይሆን የዕእምሮ ጨዋታ (Tactical Battle) እንዲሆን አድርጎታል።

አስተናጋጅዋ ሀገር እስከ ፍጻሜው ድረስ እንከን የለሽ ጉዞ ነው ያደረገችው ማለት ይቻላል። ብራሂም ዲያዝ በፈጠራ ችሎታው፣ ኤዘዲን ኦናሂ በመሀል ሜዳ ብልሃቱ ቡድኑን እየመሩ ፍጻሜ ቢደረሱም ህልማቸው ቅዠት ሆኖ ቀርቷል። እነዚህ ክስተቶች በሰሜን አፍሪካ እግር ኳስ የሃይል ሚዛን ላይ ጥያቄዎች እንዲነሱ አድርገዋል።

ናይጄሪያ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ የጨረሰችው በተከላካዮች ጥንካሬ ሳይሆን በአጥቂዎቿ ብዛት እና ጥራት ነው። “ማንኛውም ቡድን ግብ ቢያስቆጥርብን እኛ ደግሞ የበለጠ ግብ ማስቆጠር እንችላለን” የሚል መፈክር በመያዝ እስከ ግማሽ ፍጻሜ ተጉዘዋል። በሩብ ፍጻሜው አልጄሪያን የጣሉበት መንገድ ይህን ያሳያል።

የ2021 ሻምፒዮኖቹ ሴኔጋሎች ያለ ብዙ ጫጫታ በከፍተኛ ዲስፕሊን በድጋሚ ዋንጫውን አሳክተዋል። በአሊዮ ሲሴ ምትክ ዙፍኑን የተረከቡት ፓፔ ቲያው የገነቡት ቡድን በሁሉም ቦታ የተመጣጠነ፣ ልምድ እና ወጣትነትን ያዋሃደ ስብስብ ይዘው ቀርበዋል። የግብፅ ብሄራዊ ቡድን እንደተለመደው እና እንደምናውቀው በሞሮኮ ማራኪ እግር ኳስ አልተጫወቱም። በኋላ ክፍሉ ጥንካሬ ግማሽ ፍጻሜ መድረስ ችለዋል።

በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ታላላቅ ቡድኖች በጊዜ ከውድድሩ ሲሰናበቱ ተመልክተናል። የ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ኮትዲቯር ጥሎ ማለፉን መሻገር አለመቻሏ የውድድሩ ትልቁ እንግዳ ክስተት ነበር። ዝሆኖቹ በምድብ ጨዋታዎች ያሳዩት የመከላከል ክፍተት እና የተጫዋቾች መዘናጋት ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ይህ ሽንፈት በሀገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ ከፍተኛ ቀውስ አስከትሏል።

በተመሳሳይ የጋና ብሄራዊ ቡድንም አንድም የምድብ ጨዋታ ሳያሸንፍ በጊዜ መሰናበቱ ለአራት ጊዜ የዋንጫ ባለቤቷ ሀገር ትልቅ ውርደት ሆኖ ተመዝግቧል። እንደ ቡርኪና ፋሶ እና አንጎላ ያሉ ሀገራት ግን ያሳዩት ብቃት የሚደነቅ እንደነበር ቢቢሲ ሰፖርት አስነብቧል። የ2026 የአፍሪካ ዋንጫ በአደረጃጀት ጥራት፣ በታክቲክ ብስለት እና በሜዳ ላይ ፉክክር አዲስ ታሪክ አስመዝግቦ አልፏል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥር 11  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here