በዓሉ ባሕላዊ ዕሴቱን ጠብቆ እንዲከበርና እንዲለማ ቢሮዉ ኃላፊነቱን ይወጣል

0
137

የአገው ፈረሰኞች በዓል ባሕላዊ ዕሴቱን ጠብቆ እንዲከበርና እንዲለማ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ መልካሙ ፀጋዬ 85ኛውን የአገው ፈረሰኞች ክብረ በዓል በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ክልሉ ካሉት የማይዳሰሱ ባሕላዊ ሃብቶች መካከል የአገው ፈረሰኞች ማኅበር እና በየዓመቱ የሚከበረው የማኅበሩ ክብረ-በዓል አንዱ መሆኑን አንስተዋል፤ የአገው የፈረሰኞች ማኅበርም ረዥም ታሪክ ያለው፤ የአገው ሕዝብ መገለጫ እየሆነ የመጣ ባሕላዊ ሃብት ነው ብለዋል፡፡

የማኅበሩ አመሠራረትና የበዓሉ አከባበር ከ1928-1933 ዓ.ም ከተካሄደዉ የጣሊያን ወረራ ጋር የተያያዘ ታሪክ እንዳለው የታሪክ ድርሳናትን ዋቢ አድርገው ያነሱት ኃላፊው የአገው ፈረሰኞች ማኅበርም ከዚያ ዘመን ጀምሮ በተለያየ መልኩ አደረጃጀቱን እያጠናከረ፣ አባላቱን እያሰፋ እና በየዓመቱ ክብረ በዓሉን እያከበረ የዘለቀ የዘላቂ ተቋም ግንባታ ተምሳሌት የሆነ ትልቅ ተቋም ነው ብለዋል።

የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ታሪክን ከአሁናዊ ክዋኔ ጋር አዋህዶ፣ ባሕላዊ ዕሴትንና ማኅበራዊ ወግን ጠብቆ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ቅርሳችን ነው ያሉት አቶ መልካሙ የአብክመ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮም ልክ እንደሌሎች ባሕላዊ ክብረ በዓላትና ቅርሶች ሁሉ የአገው ፈረሰኞች በዓልም ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበርና እንዲለማ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ በመልዕክታቸው አክለዋል።።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here