ስታቲስታ ድረ ገጽ እንዳስነበበው ቱሪዝም እ.አ.አ በ2023 (በ2016 ዓ.ም) ከ266 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ዘርፍ ነው፡፡ ይህም በዓለም የተፈጠረውን የሥራ ዕድል ስምንት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ይሸፍናል፤ አምስት በመቶ የዓለምን አጠቃላይ የምርት ውጤት (ጂዲፒ) ድርሻ አለው፡፡ ከዘጠኝ ነጥብ ዘጠኝ ትሪሊዮን ዶላር (አንድ ነጥብ ሁለት ኳድሪሊዮን ብር ገደማ) በላይ ገቢም አስገኝቷል።
በተጠናቀቀው 2024 ዓመትም ዘርፉ ያስገኘው ገቢ ከ11 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመረጃው ተመላክቷል፡፡
ቢዝነስ ኢንሳይደር በበኩሉ በየዓመቱ የበርካታ ጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብ ሀገራዊ ምጣኔ ሀብታቸውን የሚደጉሙ ሀገራትን ዘርዝሯል፤ በዚህም ፈረንሳይን “የጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብ በየዓመቱ በርካታ ሚሊዮን የሚጎበኟት የዓለማችን መዳረሻ” ናት ሲል ነው የገለጻት።
ቱሪዝም ፋክትስ የተባለው ድረ ገጽ ደግሞ ቱሪዝም ከሌሎች ዘርፎች በተለዬ ፍጹም ሰላምን ይሻል፤ ምክንያቱ ደግሞ ዘርፉ በጎብኝዎች እንቅስቃሴ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው፡፡ እንቅስቃሴው የሚኖረው ደግሞ ጎብኝዎች አስተማማኝ ሰላም እና ለደኅንነታቸው ዋስትና እንዳላቸው ሲሰማቸው እንደሆነ ጠቅሷል።
ከዚህ ጋር በተገናኘ ባለፉት ዓመታት የሀገራችን ቱሪዝም እንቅስቃሴ ተዳክሟል፤ ለዚህም የኮሮናን ቫይረስ ወረርሽኝ እና የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ በሀገራችን እየተከሰቱ ያሉት ግጭቶች ምክንያቶች ናቸው፡፡ በዚህም ክፉኛ ጉዳት ከደረሰባቸው የሀገራችን አካባቢዎች መካከል የአማራ ክልል በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ በዓለም የቅርሶች መዝገብ የተመዘገቡ እና ያልተመዘገቡ ትውፊቶች ባለጸጋው የአማራ ክልል ኮሮና ካደረሰበት ተጽዕኖ በተጨማሪ ከግጭትና ከጦርነት አዙሪት ሊወጣ አልቻለም፡፡ በዚህ የተነሳም የቱሪዝም ዘርፉ ተቀዛቅዟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዘርፉ ዘንድሮ የተሻለ መነቃቃት ላይ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡ ከታኅሳስ ወር መጨረሻ ጀምሮ ያሉት ወራት በርካታ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎች የሚደምቁበት ነው፡፡ ገና በላሊበላ እና ጥምቀት በሁሉም አካባቢዎች በተለይ በጎንደር እና በምንጃር ሸንኮራ እንዲሁም የቃና ዘገሊላ በዓላት ሃይማኖቱ በሚፈቅደው ሥርዓት በተለዬ ድምቀት ከተከበሩ በዓላት መካከል ይጠቀሳሉ። በዓላቱ የቱሪዝሙ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ አድርገዋል።
ሀገራችን የተለያዩ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት አስመዝግባለች፣ የሚበዙት ደግሞ በአማራ ክልል ይገኛሉ። የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታት ሕንፃዎች፣ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ እና የጣና ገዳማት በአማራ ክልል የሚገኙ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡት መካከል ናቸው።
እነዚህ ቅርሶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ደማቅ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት ይከበራሉ። በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ምክንያት የሆኑትም እነዚህ በዓላት ናቸው፡፡ እነዚህ በዓላት በደማቅ ሥነ ሥርዓት መከበራቸው ታዲያ በአንድ ጠጠር ሁለት ወፍ እንዲሉ ጎብኝዎች ቅርሶቹን ከመጎብኘት ባለፈ በበዓላቱ በመታደም ሐሴት እንዲያደርጉ አስችለዋቸዋል። የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘምም አካባቢዎቹ በምጣኔ ሀብት ይደጎሙበታል።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላሊበላ፣ ጥምቀት በተለይ በጎንደር፣ በምንጃር ሸንኮራ፣ የቃና ዘገሊላ በሁሉም አካባቢዎች፣ የመርቆሬዎስ ክብረ በዓል በደብረ ታቦር፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል በአዊ ብሔረሰብ፣ የአስተሪዮ ማርያም የንግሥ በዓል በመርጦ ለማርያም፣ በደረስጌ ማርያም እና በሌሎችም አካባቢዎች የሚከበሩ በዓላት አማራ ክልልን የሚያደምቁ ክዋኔዎች ናቸው።
የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ እንዳስታወቀው በዓላቱ የገቢ ማስገኛ ብቻ ሳይሆኑ ጌጦችም ናቸው፣ የማሕበረሰባዊ ትስስር ገመድ እና ወግ ባሕሉ በአደባባይ የሚገለጥባቸው ናቸው።
በቢሮው የባሕል እሴቶች ልማት ባለሙያ ነህምያ አቤ “ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ በርካታ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት ያላት ሀገር እንደሆነች በማንሳት ከእነዚህ መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገበው ጥምቀት አንደኛው እንደሆነ አስታውሰዋል። በዓሉም “ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚታይበት፣ መከባበር እና መተሳሰብ የሚንጸባረቅበት ነው” ብለዋል።
በልደት፣ በጥምቀት እና በቃና ዘገሊላ፣ የግዮን በዓል በሰከላ መድመቅ የጀመረው የክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በቀጣይ ወራትም እንደ ደመቀ ይቀጥላል። የአስተሪዮ ማርያም፣ የመርቆሬዎስ፣ የአገው ፈረሰኞች እና ጥርን በባሕር ዳር የክልሉ ድምቀት ሆነው የሚቀጥሉ በዓላት ናቸው።
ጥርን በባሕር ዳር ከሚያደምቁት መካከል ጥር 18 ቀን በድምቀት የሚከበረው የሰባሩ ጊዮርጊስ የንግሥ በዓል ዋናው ነው፤ ክዋኔዉ የሚካሄደው የጣና ላይ የጀልባ ቀዘፋ ትዕይንት ደግሞ የድምቀት ማዕከል እና ቀልብን የሚስብ ነው፡፡
የአሥራ ሦስት ወር ባለጸጋ ሀገራችን ለማንኛውም ጎብኚ ምቹ የአየር ንብረት ባለቤትም ናት፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታዲያ በግጭቱ ምክንያት የተቀዛቀዘው ቱሪዝም እንዲነቃቃ እንዳደረገው ነው የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ያመላከተው።
በበዓላቱ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቀው ከመከናወናቸው ባሻገር ሀገራዊ መልዕክቶች በአባቶች በኩል ተላልፈዋል።
የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም አስተዳዳሪ አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ “ጥምቀት ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወርዶ የተጠመቀበት እና ትህትናን ያስተማረበት ነው” ብለዋል። የገዳሙ አስተዳዳሪ እንዳሉት ዮርዳኖስ ትህትና ታይቶባታል፣ በዮርዳኖስ የሰው ልጆች የዕዳ ደብዳቤ ተቀዷል፣ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጎ ትህትናን አሳይቶናል። በመሆኑም “በፍቅር እና በትህትና መኖር ይገባል” ሲሉ ነው መልዕክት ያስተላለፉት።
በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሁመራ ከተማ የጥምቀት በዓልን በተከዜ ወንዝ ዳርቻ በድምቀት አክብራለች። በበዓሉ ዕለት ተገኝተው አባታዊ መልዕክት ያስተላለፉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቢ ሀዲስ መምህር ዜናዊ አሸተ “ትሕትና የልዕልና መሠረት ነው፤ ትዕቢት ውድቀትን ትቀድማለች፤ ክርስቶስም ሲጠመቅ ይህንን አስተምሮናል” ብለዋል።
“ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ባሕር ሄዶ የተጠመቀው የሰውን ልጅ የዕዳ ደብዳቤ ለመቅደድ፤ ራስን ዝቅ በማድረግ ከፍ ማለትን ለሰው ልጅ ሁሉ ለማስተማር ነው። በመሆኑም ሁላችንም በትህትና ዝቅ ስንል ራሳችን ከፍ ብሎ እናገኘዋለን” በማለት ነው ትሕትና የልዕልና መሠረት ስለመሆኑ ያስገነዘቡት።
“የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር መፈቃቀርን፣ መዋደድን እና መተባበርን ገንዘቡ ማድረግ አለበት” በማለት አባታዊ ጥሪ ያደረጉት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ጸሐፊ፣ የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ “ሁሉም ቆም ብሎ ስለ ሰላም ማሰብ ይኖርበታል፤ ሁሉም በፍቅር እና በአብሮነት በመቆም ለሀገር ሰላም እና ዕድገት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት አለበት” ብለዋል። ሁሉም ሰው ስለ ሰላም ዋጋ ቆም ብሎ ሊያስብ እንደሚገባም አሳስበዋል።
“የሰው ልጅ ዘላቂ ሕይወትን መቀዳጀት የሚችለው መልካም ሰብዕና ሲላበስ እና ፈጣሪውን ሲፈራ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው ሁሉም ዜጋ ለሀገር ሰላም እና ዕድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመተሳሰብ እና በአብሮነት ለመቅረፍ መሥራት አለበት” ብለዋል።
በጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ የታደሙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ “የሰላም ዋጋው ውድ በመሆኑ ሰላምን ለማጽናት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል” ብለዋል።
የከተራ፣ የጥምቀት እና የቃና ዘገሊላ በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም