በዓላት የኢትዮጵያ ውብ መልኮች መገለጫዎች ናቸው

0
221

የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመው ስታዩ ከየሠፈራችሁ እየወጣችሁ ተከተሉት፤ አጅቡት። (መጽሐፈ እያሱ 3፥3)

ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ ተብሎ እንደ ተጻፈ ለኀጢአት ሥርየት የንስሐን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው ሀገር ሁሉ መጣ። (የሉቃስ ወንጌል 7፥29)

መነሻ ያደረግናቸው ጥቅሶች በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ የጥምቀትን አምላካዊ የመድኅን ቃል የሚያስተምሩ ናቸው። ክርስቶስ ወደ ምድር መጥቶ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ የሰውን ልጅ የዕዳ ደብዳቤ እንቀደደ የሚያሳዩ አስተምሮዎች ናቸው።

በተመሳሳይ ጥምቀት ከሃይማኖታዊ ትውፊቱ ባለፈ ሰው የሚሰባሰብበት፣ ወግ ባሕሉን በአደባባይ የሚገልጥበት፣ በዘላቂ ማሕበራዊ መስተጋብር የሚተሳሰርበትም ነው።

መምህረ መምህራን የኔታ በጽሐ ዓለሙ በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት የደብረ ታቦር ከተማ ደብረ ልዑላን መድኃኒ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባዔያተ መጻሕፍት መምህር ናቸው፤ ሃይማኖታዊ በዓላትን በተመለከተ ከጠሊቅ ዕውቀታቸው ሊያካፍሉን ከበኲር ጋር ቆይታ አድርገዋል። የኔታ እንዳሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሠራቸውን ሥራዎች ሁሉ በተግባር የመግለጽ ልምዷ ሰፊ እና የቆዬ ነው። “ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ መጠመቁን በተግባር የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነውን ታቦተ ሕጉን ይዛ ወደ ባሕሩ በመውረድ ታስታውሳለች። እዚያ ተጠምቆም ከባሕሩ ወጥቶ መመለሱንም እንደዚሁ በጉዞው ታስታውሳለች” ይላሉ።

የኔታ በጽሐ ከላይ ያነሱትን ሐሳብ ተጨማሪ አብነት በማንሳትም ነው የሚያብራሩት፤ ለምሳሌ መስቀሉ ሲታሰብ ደመራውን በመደመር፣ መስቀሉ መውጣቱን ደግሞ መስቀል ይዛ በመሄድ ቦታው ላይ በመገኘት ታከብራለች፤ ቤተ ክርስቲያናችን:: በዚህም የመስቀሉን ተግባር ወይም ድርጊት ቤተ ክርስቲያኗም በዚያው በተግባር ትገልጣለች ማለት ነው። እነዚህ ሁሉ የሚያሳዩት ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል የሠራቸውን በተግባር ይዞ የመቀጠል የቆዬ ልምዷ ስለመሆኑ ነው።

የአራቱ ጉባዔያተ መጻሕፍት መምህሩ እንዳስገነዘቡት ጥምቀት ክርስቶስ የሰውን ልጅ የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ ሲል የተጠመቀበት፣ የሥላሴ አንድነት እና ሦስትነት በዮርዳኖስ ወንዝ የተገለጠበት ነው፤  ክርስቶስ እንደተጠመቀ የቤተ ክርስቲያን ምዕመኖቿም ያንን ቀን በማሰብ ጥምቀተ ሥርዓቱን በየዓመቱ በማከናወን፣ ጸበሉንም በመጠመቅ ሕዝቡን ሃይማኖተኛ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው እንዲሆን አድርጎታል።

ሃይማኖታዊ በዓላት ከሃይማኖታዊ ክዋኔያቸው ባለፈ ለጠንካራ ማሕበራዊ መስተጋብርም መሠረት ናቸው፤ ወንድሙ አምባቸው ደግሞ የዚህ አብነት የሆነ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ነው:: ወንድሙ እንደሚለው የጥምቀት በዓልን በየዓመቱ በጎንደር ከተማ ያከብራል:: በጋብቻ ተሳስረው ትዳር እንዲመሠርቱ መሠረት ከሆነችው ባለቤቱ ጋር የተዋወቀውም በጥምቀት በዓል እንደሆነም ነው የነገረን::

በርካቶችም የእሱ አይነት ተሞክሮ እንዳላቸው የሚናገረው ወንድሙ ሃይማኖታዊ እና ማሕበራዊ ዕሴቱ በሚፈቅደው መሠረት በዓሉን በድምቀት እንደሚያከብር ነግሮናል:: ታቦታት ከመንበራቸው ወደ ማደሪያቸው ሲሄዱ እና በማግስቱ ደግሞ ወደ መንበራቸው ሲመለሱ ከፊት በመሆን ታቦታቱ የሚሄዱበትን መንገድ እንደሚያጸዳም አክሏል፤ በየዓመቱ ይህን በማድረጉም “የእናት አባቴን ወግ እና ባሕል ከመጠበቄ ባለፈ ወደር የሌለው የአዕምሮ እርካታ ይሰማኛል” ነው ያለው:: ይህንኑ ተግባርም በበዓሉ መጨረሻ “ሁላችንንም ሳይለየን በሰላም እና በጤና ያድርሰን ብዬ ለአምላኬ እሳላለሁ፤ በየዓመቱም እንዲህ አጸዳለሁ” ብሏል::

በበዓላት ወቅት ሁሉም እንደ አቅሙ ተውቦ ይወጣል፤ በጥምቀት ደግሞ ይህ ይበልጥ ጎልቶ ይታያል:: ልክ እንደ ጎንደር ከተማ ነዋሪው ወንድሙ ሁሉ ዕድሜያቸው የደረሱ የሚተዋወቁበት እና የትዳር አጋራቸውን የሚያማትሩበትም ነው::  ሃይማታዊ ክዋኔዎች የጥምቀት በዓል ዐበይት ጉዳዮች መሆናቸውን የኔታ በጽሐ ያነሳሉ፤ በሌላ በኩልም በዓሉ በርካታ ማሕበራዊ ክዋኔዎችም ይከናወኑበታል:: ሰዎች ይተዋወቃሉ፤ ትውውቃቸው አድጎም ትዳር እስከመመሥረት የሚደርሱት በርካታ ናቸው:: “የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት፣ የማሕበረሰቡን ወግ እና ባሕሉን ጠብቆ ጋብቻ መፈጸም ቅዱስ ነው” የሚሉት የኔታ በጽሐ እንደ ጥምቀት ዓይነት የአደባባይ በዓላት ደግሞ ይህ ማሕበራዊ መስተጋብር ከሚገለጥባቸው መካከል ስለመሆናቸው ነው የተናገሩት:: “ሁሉም ነገር ሃይማኖቱ የሚፈቅደውን ሥርዓት ጠብቆ፣ በወጉ እና በባሕሉ ሲከወን መልካም ነው” ብለዋል::

የበዓላትን አከባበር የተለያዩ መገለጫዎች ከእናት አባቱ እና ከሌሎች ታላቆች በልጅነቱ እንደወረሰ የነገረን ደግሞ ጥምቀትን በባሕር ዳር ከተማ ሲያከብር ያገኘነው ወጣት አበባው አልማው ነው። አበባው እንደነገረን ከበዓሉ ቀናት ቀደም ብሎ ባሕላዊ አልባሳትን በጋራ  በማሠራት በዓሉን በጋራ ያከብራሉ። በዋዜማው ደግሞ ታቦታቱ የሚሄዱበትን መንገድ ያጸዳሉ፣ በባሕላዊ ጭፈራም በዓሉን ያደምቃሉ።

ይህ ሁሉ ታዲያ ከሃይማኖታዊ ትውፊቱ በተጨማሪ “የአንድነታችን ማጠናከሪያ ክር፣ እርስ በርስም የምንተሳሰብበት ነው” ብሏል። ለዚህ ማሳያም ተመሳሳይ የባሕል አልባሳት በሚያሠሩበት ወቅት ከመካከላቸው ገንዘብ የተቸገረ ካለ እንደሚያዋጡለት አብነት አንስቷል። ጓደኛቸውም በዓሉን በደስታ እንዲያከብር ያደርጋሉ።

በተመሳሳይ ወጣቱ በበዓል ወቅት ከአለባበስ ጀምሮ የሚያከናውናቸው ተግባራት ባሕል አስጠባቂ መሆናቸውን ያነሳው አበባው፣ “አልፎ አልፎ ግን ከባሕል የመውጣት ነገር ታዝቤያለሁ። ለዚህ ደግሞ በተለይ አባቶች በማስተማር መመለስ ይገባቸዋል” ነው ያለው።

አበባው እንደነገረን የጥምቀት በዓልን ከባሕር ዳር በተጨማሪ (አዲስ አበባ፣ ጎንደር) የማክበር ዕድል ገጥሞት ያውቃል። በሁሉም አካባቢዎች ደግሞ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በተጨማሪ የአካባቢውን ወግ እና ባሕል የሚገልጹ የተለያዩ ክዋኔዎች ይከናወናሉ። “ጥምቀትን በአብዛኛው ባሕር ዳር ከተማ ባሳልፍም የሌሎችን አካባቢዎችን አከባበርም ተመልክቻለሁ። በዓላት የኢትዮጵያ ውብ መልኮች የሚገለጡባቸው መሆናቸውን ተመልክቻለሁ” ነው ያለው።

በተለይ ወጣቶች  ከዋዜማው ጀምሮ መንገዶችን በማጽዳት፣ አባቶች የሚያዝዙትን በመሥራት፣ ሰላም በማስከበር፣ በመንፈሳዊ ዜማ እና ባሕላዊ ጭፈራ በዓሉን ሲያደምቁ ታዝበናል።

የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ታላቅ በዓል ነው:: ይህ መሆኑ ደግሞ የአደባባይ በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታይ ያደርገዋል፤ የሀገራችንን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይገነባል:: የጎብኚዎች ቁጥርም በከፍተኛ ደረጃ ያድጋል:: ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታዲያ ምጣኔ ሀብታዊ አበርክቶውም ከፍተኛ ይሆናል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ የባሕል መበረዝ አሁናዊ ስጋት እየሆነ በመምጣቱ ትውልዱ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አባታዊ ምክር ለግሰዋል፤ የአራቱ ጉባዔያተ መጻሕፍት መምህር የኔታ በጽሐ ዓለሙ:: ትውልዱ የራሱን ነገር እስከ ቀለሙ እና የኩራት ምልክት የሆነ መገለጫውን ሀብቱን በአግባቡ አውቆ መጠበቅ እንዳለበት ጠቁመው “ትናንትናውን በደንብ ማወቅ ደግሞ የዛሬ ማንነታችንን ለመጠበቅ ያስችላል፤ ከዚያም አልፎ በትውልዴ፣ በዘመኔ እንዲህ አደረኩ በማለት እንድንኮራ ያደርጋል” ብለዋል።

የኔታ አክለውም ሃይማታዊ በዓላትን ጨምሮ በሀገራችን የሚከወኑ ትውፊቶችን በአግባቡ መጠበቅ ካልተቻለ የባሕል ወረራን ሊያስከትል ይችላል፤ ይህ ደግሞ በተለይ የአሁኑን ትውልድ ከባሕር እንደወጣ ዓሣ ሊያደርገው ይችላል:: በመሆኑም የጥምቀት በዓል መከበር ያለበት እንዴት ነው? ሃይማኖታዊ ይዘቱ ምንድነው? ሥርዓቱስ? የሚለውን ነገር በደንብ ለትውልዱ ማስተማር እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

መምህረ መምህራን የኔታ በጽሐ ዓለሙ የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ዓለም አቀፋዊ የጉብኝት እና የዕውቅና ማዕከል ቢያደርገውም “የባሕል መበረዝ እንዳይመጣ ግን በጣም መጠንቀቅ ይገባል” ይላሉ። በባሕል መበረዝ ምክንያት የራሳቸውን ነገር ያጡ እንዳሉ በማንሳትም “ከዚህ ትምህርት በመውሰድ ለማንነታችን መገለጫዎች ሁላችንም ዘብ መሆን ይገባናል። የሃይማኖት አባቶች የሚጠበቅብንን በማስተማር የአባትነት አደራችንን መወጣት ይገባናል” ብለዋል።

“እነዚህ በዓላት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝባቸው፣ ዓለም እኛን የሚያይባቸው፣ ጎብኚዎችም ወደ እኛ የሚመጡበት ነው፣ በዚያውም ገቢው በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን ብዙ ነገሮቻችንን የምናሟላበት፣ የዓመት ስንቃችንም የምንይዝበት ነው፤ ከጥምቀት ማግስት ደግሞ ሌሎች በዓላት (አስተርዮ ማርያም፣ የቅዱስ መርቆርዮስ ንግሥ በዓላት እና ሌሎችም) በድምቀት ይከበራሉ። እነዚህ ሁሉ የሀገር ሀብቶች ናቸው። የማንነታችን መገለጫ፣ የሥነ ልቦናችን ውቅር ከመሆናቸው ባለፈ ምጣኔ ሀብታዊ አበርክቷቸው ከፍተኛ ነው:: በመሆኑም በአግባቡ ተጠብቀው በሥርዓቱ ሊከበሩ ይገባል፣ ይህ ሲሆን ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር እንገናኛን” ነው ያሉት::

በመጨረሻም ከመላው ዓለም የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊነት ባሕል ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚገባ መምህረ መምህራን መልዕክት አስተላልፈዋል፤ እንግዶችም በዓሉን በልኩ ማየት (ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው ያሉ ክዋኔዎችን በአግባቡ ማየት) እንደሚገባቸው አሳስበዋል:: ይህ ሲሆን የበዓሉን ሙሉ ሥዕል በአዕምሮ ውስጥ ሕያው አድርጎ ለማኖር እንደሚያስችል ተናግረዋል። “በዓሉን ለሀገራችን ሰላምን፣ ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነትን፣ ለሕዝባችን ፍቅር እያሰብን ማክበር ይገባል” ብለዋል።

የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አሕጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሃም የጥምቀት በዓል ቤተ ክርስቲያን የሰላም አምላክ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ ሰላም እና ፍቅር የምትለምንበት ልዩ በዓሏ መሆኑን ገልጸዋል።

“ጥምቀት ፍቅርን፣ መተባበርን፣ መደማመጥን እና መከባበርን ያስተምራል” ብለዋል። ጭፈራውን እና ሃይማኖታዊ ክዋኔውን ሳይቀላቅሉ በሥርዓት ማክበር እንደሚገባም አሳስበዋል። በጥምቀት በዓል ሀገርን የሚያወድሱ መዝሙሮች የሚዘመሩበት፣ እግዚአብሔር የሚመሰገንበት እና ታዛዥ ሆኖ በፍቅር የሚመላለሱበት መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉን እግዚአብሔር ለችግራችን መፍትሔ እንዲሰጠን በመለመን ማክበር እንደሚገባ በማሳሰብ “ጊዜው የሚጨፈርበት ሳይሆን እግዚአብሔር ምሕረቱን እንዲልክልን የምንጸልይበት ነው” በማለት አሳስበዋል።

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የጥር 11  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here