ትንንሽ የዓእዋፍ ዝርያዎች የሚያሰሙት ዝማሬ ምንነታቸውን በማስተዋወቅ አጣማጅ ለማግኘት እና መኖሪያ ቀጣናቸውን ከጥቃት ለመከላከል ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል::
በአውስትራሊያ የፍሊንደር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪው ዶክተር ኮሎምቤሊ ኔግሬል ባደረጉት ጥናት በአእዋፍ ዝማሬ ውስጥ የፆታ ማሳወቂያ፣ የአካል ብቃት ሁኔታ እና መኖሪያ ወይም መገኛ ቀጣናን ከጥቃት ለመከላከል መልእክት እንደሚተላለፍበት ነው ያረጋገጡት::
የዓእዋፍ ምንነት ሲባል ያሉበት ሁኔታ፣ አካላዊ ደረጃቸውን፣ ውስጣዊ ባህሪ – ንዴት፣ ቁጡነት ወ.ዘ.ተ.ን ፊት ለፊታቸው መስታዉት በማኖር መገምገም መቻላቸውን ነው ያስረዱት – ተመራማሪው:: በዚህም ከፆታ ልዩነት እና የአኗኗር ደረጃ (ታዳጊ፣ ጥንድ ወ.ዘ.ተ) ከግምት ውስጥ ሳይገባ አጣማጅ የሚሹ ወይም የሚፈልጉቱ በዝማሬያቸው ውስጥ ከማይፈልጉት የበለጠ የተለያዩ መገለጫዎች ያሏቸው መሆኑን ደርሰውበታል::
ተመራማሪው አክለውም በአብዛኛው ጠበኛ ትንንሽ ወፎች የሚያሰሙት ዝማሬ ድምፀት አጫጭር መሆኑን ክትትል ከተደረገባቸው መገንዘባቸውን ነው ያረጋገጡት:: በጥናታቸው የዓእዋፍ ፆታዊ ምልክቶች ወይም መለያዎች ከሚያሳዩት ስሜት (ባህሪ) ጋር የሚገናኝ እና የአካል ብቃት ደረጃን ሊገልፅ እንደሚችል ነው የተገነዘቡት::
ሁለቱንም ፆታ አካቶ አጣማጅ በሚሹበት ወቅት የሚያሳዩትን ቁጡነት ወ.ዘ.ተ ወፎቹ ለጥናቱ ከተያዙበት በአጭር እና ረዢም ጊዜ መስታውት ፊት ለፊት ክትትል ተካሂዶባቸዋል- በአጥኚዎቹ:: ከዚህ ባሻገር በጥናቱ ናሙና የተካተቱ ከውስን ቦታ ውጪ ተለቀው ለወራት የሚያሰሙትን ዝማሬ በመቅረፀ ድምፅ በመቅዳት የየአንዳንዱን ዝማሬ ልዩነት እና ውስብስብነት ለመለየት ጥረት አድርገዋል- ተመራማሪዎች::
በደቡብ አውስትራሊያ የአእዋፍ የምርምር ቡድን ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት በውስን ቤተሙከራ ከፊሎቹን ለአጭር እና ለረጅም ቀናት በማገት እንዲሁም ለወራት በመስክ የመቅረጫ መሳሪያዎችን በመጠቀም ዝማሬያቸው ተሰብስቦ ተሰንዷል::
የተሰበሰበውን የድምፅ መረጃ እና የምስል ቀረፃ በማገናኘት ከተካሄደው ጥልቅ ትንተና የወፎች ዝማሬያቻው ምንነታቸውን በማስተዋወቅ አጣማጅ ለማግኘት እና መኖሪያ ግዛታቸውን ከጥቃት ለመከላከል ወሳኝ መሆኑ ነው በማጠቃለያነት ለንባብ የበቃው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም