በኢትዮጵያ ውስጥ የተገኙት አዲስ ጥንታዊ የሰው ዘር ቅሬት አካላት በዝግመተ ለውጥ በአንድ ነጠላ መስመር ሳይሆን ውስብስብ የተከፋፈለ ቅርንጫፍ ዝርያዎች እንደነበሩት የሚያረጋገጥ መሆኑን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል::
በአሜሪካ የኒቫዳ ላስቬጋስ ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር ጥናት ተመራማሪዎች ቡድን የተገኙት ጥርሶች የሰው ዘር ከቀደምት ዝንጀሮ መሰል ወደ ዘመናዊው ሰው በአንድ ቀጥ ያለ መስመር የመጣ ሳይሆን ውስብስብ ቅርንጫፍ እንደነበሩት “ኔቸር” በተሰኘው መፅሄቱ ለህትመት በቅቷል::አጥኚው ቡድን በኢትዮጵያ ያገኘው አዲስ የአውስትራሎፒቲክስ ቅሪት አካል ከሁለት ነጥብ ስድስት እስከ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዓመታት በፊት ይኖሩ የነበሩ ጥንታዊ የሆሞ ሳፒያን ናሙናዎች ናቸው፡፡ የተገኙት 13 አዲስ አውስትራሎፒቲከስ ጥርሶች ከአቅራቢያው “ሀዳር” ከተገኘው የሉሲ ቅሪት አካል ሁለት ነጥብ 95 ሚሊዬን ዓመታት በፊት መሆኑንም ነው ያረጋገጡት::የተመራማሪዎች ቡድኑ በአውስትራሎፒቲከስ እና ሆሞሳፒያን ዝርያዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት በአፋር ክልል ከተከሰቱ ተደጋጋሚ የእሳተገሞራ ፍንዳታዎች የተበታተነ ስብርባሪ እና አመድን በመመርመር እድሜውን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ መወሰን እንደተቻለ ጠቁሟል::
በተመራማሪዎቹ ቡድን ውስጥ የተካተቱት የአርካንሳስ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ኘሮፌሰር ሉካስ ዴሌዜኔ አዲስ የተገኘውን የጥንታዊ ሰው የፊት ጥርስ በሀዳር ከተገኘው ጋር አወዳድረዋል፡፡ አዲስ የተገኘው ከሁለት ነጥብ ስድስት እስከ ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዬን ዓመታት በፊት ከተከመረ ደለል ስር መሆኑ የዘር ሀረጉን ጥንታዊነት ማሳያ አብነት መሆኑን አስምረውበታል::በመጨረሻም ዝርያዎቹ ለምግብነት ከተለያየ ማለትም ለአብነት ቅጠላቅጠል፣ ሥራ ስር አና የዱር እንስሳትን ወዘተ በግብአትነት እንደሚያውሉ ነው የተጠቆመው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተፈጥሯዊ አደጋዎች እንደ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ፣ ጐርፍ፣ ሰደድ እሳት በመሳሰሉት ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው ሊፈልሱ እንደቻሉ እና የዝርያዎቹ ቅርንጫፍ ሊበዛ እንደቻለ ነው ያደማደሙት::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም