በደል የተፈፀመበት ስፖርት

0
191

እግር ኳስ በዓለም ላይ ቀዳሚው ተወዳጅ ስፖርት መሆኑን የዘጋርዲያን መረጃ አመልክቷል፡፡ ይህ ተወዳጅ ስፖርት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ሲሆን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቶችን ለማርገብ ዋነኛ መሳሪያ ሆኖም ያገለግላል፡፡ የተጣሉትን ያስታርቃል፤ ጦር የተማዘዙትንም አፈ ሙዙ ወደ ሰገባው እንዲያስገቡት ያደርጋል፤ አድርጓል፡፡

ታዲያ ይህንን የተረዱት የሀገር መሪዎች እና ግለሰቦች ለበጎ ዓላማ ሲያውሉት ጥቂት የማይባሉት ደግሞ በእኩይ ተግባራቸው እግር ኳሱን በድለዋል፡፡ በእግር ኳስ ስፖርት ማሸነፍ፣ መሸነፍ ያለ ቢሆንም ክለቦች እና ብሄራዊ ቡደኖች በመሸነፋቸው ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና ዳኞች ተገድለዋል፤ ተደብድበዋል፤ ታስረዋል፡፡ እነዚህ አምባገነን መሪዎች እና ግለሰቦች በማን አለብኝነት ውጤትም አስቀይረዋል፡፡

ጊዜው እ.አ.አ በ2015 ነው፤ በሀገረ ሞሪታኒያ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በኤፍሲ ቴቭራግ እና በኤስኤስ ክሳር መካከል እየተደረገ ይገኛል። ጨዋታውም 63ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ውጤቱም አንድ አቻ ነው። ጨዋታው በእጅጉ አስደሳች እና ማራኪ አልነበረም። ይህን ጨዋታ የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሙሀመድ ኦዶ አብደላዚዝ ለመመልከት በስቴዲየሙ ተሰይሟል።

የጨዋታውን አሰልቺነት የተመለከቱት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጨዋታው በ63ኛው ደቂቃ ተቋርጦ በመለያ ምት እንዲጠናቀቅ ይወስናሉ። የቀድሞው ፕሬዝደንት ሙሀመድ አብደላዚዝ በጨዋታው ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን ዳኞች እና ተጫዋቾችም ተሰላችተዋል በማለት ነበር ጨዋታውን ያቋረጡት። ሁነቱም እጅግ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። ጉዳዩ ከስፖርት ቤተሰቡ ብዙ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበረ የዘጋርዲያን መረጃ አስነብቧል።

የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን ጉዳዩን ለማስተባበል ሞክሯል። ውሳኔው የአሰልጣኞች እና የዳኞች እንደሆነ ቢናገርም ሰሚ ግን አላገኘም። ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አብደላዚዝ በታሪክ ስልጣናቸውን ተጠቅመው እግር ኳስ ከበደሉ ግለሰቦች መካከል አንዱ ተደርጎ ተመዝግቧል።

የቀድሞው የሊቢያ ፕሬዝዳንት ሙሀመድ ጋዳፊ ልጅ የአባቱን ስልጣን እና ገንዘብ ተጠቅሞ እግር ኳስን ከበደሉ ሰዎች መካከል ይጠቀሳል። የጋዳፊ ሦስተኛ ልጅ የሆነው አል ሳዲ ጋዳፊ እግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ጽኑ ፍላጎት እንደነበረው መረጃዎች አመልክተዋል፥

ታዲያ ህልሙን እውን ለማድረግ እግር ኳስ መጫወት የጀመረው ከረፈደ ከ27 ዓመቱ ጀምሮ ነው። የዋና ከተማዋ ክለብ ትሪፖሊም የመጀመሪያው ክለቡ ነበር። አል ሳዲ ለእግር ኳስ የሚሆን ምንም ዓይነት ክህሎት እና ተሰጥኦ ግን አልነበረውም። ነገር ግን ራሱን የብሄራዊ ቡድኑ አባል እና  አምበል አድርጎ እንደነበር አይዘነጋም። አምባገነኑ አል ሳዲ ይህን በማድረጉ የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ብዙ ምቾት እንዳልሰጣቸው ሲረዳ ግን ከቡድኑ ራሱን አግልሏል።

አባቱ ጋዳፊ ከጁቬንቱስ ክለብ ባለድርሻ እንደነበረም የዘጋርዲያን መረጃ ያመለክታል። በተለይ ልጁ አል ሳዲ ወደ ሴሪ ኤ ከተዘዋወረ በኋላ ሊጉ በሙስና ወንጀል የተዘፈቀው በሊቢያ የነዳጅ ረብጣ ገንዘብ እንደሆነ ይነገራል። አል ሳዲ  የአባቱን ሀብት መከታ በማድረግ ክፉኛ እግር ኳስን በድሏል። በ2006 እ.አ.አ የትሪፖሊ ክለብ አሰልጣኝ የነበረው ባሻር አልራያህ ግድያም ተወንጅሏል። በጣሊያን እግር ኳስ ታሪክ ክህሎት ከሌላቸው ተጫዋቾች መካከል በቀዳሚነት ስሙ ሰፍሯል።

የቀድሞዋ ዛየር የአሁኗ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ማሳካቷን የካፍ ኦላየን መረጃ አመልክቷል። እ.አ.አ በ1968 እና 1974 ዲሞክራቲክ ኮንጎ የመድረኩን ዋንጫ ያነሳችበት ወቅት ነው። በ1974 የአፍሪካ ዋንጫን ካነሳች ከሦስት ወር በኋላ ደግሞ ለመጀመሪያ እና ለመጨረሻ ጊዜ በዓለም ዋንጫ የተካፈለችበት ወቅት ነበር።

ከ1960ዎች እስከ 1970ዎች የቀድሞዋ የዛየር ፕሬዝዳንት የነበረው ሞብቱ ሴሴ ሴኮ ብሄራዊ ቡድኑ ስኬታማ እንዲሆን ብዙ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ አድርጓል። ያወጣው ከፍተኛ ግንዘብም ሁለት የፍሪካ ዋንጫ እንዲያነሱ እና በዓለም ዋንጫው እንዲካፈሉ አስችሏቸዋል።

ብሄራዊ ቡድኑ እ.አ.አ በ1974 ፈረንሳይ ባስተናገደችው የዓለም ዋንጫ መሳተፉን ሲያረጋግጡ ከፕሬዝዳንቱ በርካታ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል። ለእያንዳንዳቸው ቅንጡ ቤት እና መኪና እንዲሁም ግማሽ ሚሊዬን ዶላር ተሰጥቷቸዋል። ተጨዋቾችም በዚህ ደስታ ውስጥ ሆነው በዓለም ዋንጫው ለመካፈል ወደ ፈረንሳይ በረዋል። ብሄራዊ ቡድኑ ወደ ፈረንሳይ ሲጓዝ በርካታ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የሀገሪቱ መከላክያ ሠራዊት፣ የህክምና ዶክተሮች እና ወጪያቸው የተሸፈነላቸው በርካታ ደጋፊዎች ቡድኑን እንዲያበረታቱ አብረው ተጉዘዋል።

የቀድሞዋ ዛየር በምድብ ሁለት ከስኮትላንድ፣ ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ እና ብራዚል ጋር  ተደልድላለች። የፕሬዝዳንት ሞብቱ ሀገር የመክፈቻውን ጨዋታ በስኮትላንድ ሁለት ለባዶ ተሸነፈች። በወቅቱ ከአውሮፓውያን ጋር በተሰጥኦ እና በክህሎት  ልዩነት ያላቸውን  የተመለከቱት አዞዎች ቀሪ ጨዋታዎችን ለማድረግ አሻፈረኝ አሉ። ነገር ግን የአምባገነኑን መሪ ድምጽ በስልክ ሲሰሙ ሁሉንም ጨዋታዎች ለማድረግ ተገደዋል።

ሁለተኛውን ጨዋታ ከዩጎዝላቪያ ጋር አድርገው ዘጠኝ ለባዶ ተሸነፉ። ይህ ውጤት እስካሁን በመድረኩ ታሪክ አስከፊው ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል። ጨዋታውን በሀገራቸው ሆነው የተመለከቱት ፕሬዝዳንቱ ተዋርደናል በሚል የግል ጠባቂዎቻቸውን ወደ ፈረንሳይ በመላክ ተጫዋቾችን እንዲያስፈራሩ አድርገዋል። ሀገራችሁ መመለስ አትችሉም፤ ትታሰራላችሁ እና የመሳሰሉት ዛቻ እና ማስፈራሪያው ግን ለውጥ አላመጣም። ከብራዚል ጋር ያደረጉትን የመጨረሻውን ጨዋታ አራት ለባዶ ተሸንፈዋልና ነው።

ከዚህ ክስተት በኋላ ግማሾቹ ፕሬዝዳንቱን በመፍራት ወደ ሀገራቸው ሳይገቡ ቀርተዋል። ከልዑኩ ጋር ወደ ሀገራቸው የገቡት ተጫዋቾች ከአውሮፕላን ማረፊያ በቀጥታ ወደ ቤተ መንግሥት ገብተዋል። የቀድሞው ተጫዋች ጉዳዩን ሲያስረዳ” ለሁላችሁም ቤት እና መኪና ሰጥቻችሁ ነበር፤ ግን እናንተ ሀገሬን አዋረዳችሁ” እንዳሉ ያስታውሳል። በመጨረሻም ሞብቱ እስር ቤት እወረውራችኋለሁ እንዳላቸው ተናግሯል።

የትኛውም የቡድኑ አባል ከሀገር እንዳይወጣ ተከለከለ። አንድ አንድ ተጫዋቾች ከአውሮፓ ክለቦች የእናስፈርማችሁ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ከሀገር መውጣት ባለመቻላቸው ሳይሳካ ቀርቷል። እ.አ.አ በ2018 የቡድኑ አምበል የነበረው ራአል ኪዲሙ ለቢቢሲ ስፖርት እንደተናገረው ሞብቱ በስልክ ሲያናግረኝ እያስፈራራኝ ነበር። የሀገራችንን ስም እና ገጽታ አበላሽታችኋል፤ የመጨረሻውን ጨዋታ በብራዚል ከተሸነፍን ዋጋችንን እንደምናገኝ በስልክ አስፈራርቶኝ ነበር ሲልም ተደምጧል።

ተጫዋቾችም የተበረከተላችውን ቤት፣ መኪና እና ገንዘብ እንዲመልሱ ተደረጉ። በዚህ ምክንያት አንዳንዶች ጎዳና ተዳዳሪ ለመሆን ተገደዱ። እ.አ.አ በ2012 የበጎ አድራጎት ገንዘብ ሲሰበሰብ ከእነዚህ የቡድኑ አባላት ውስጥ በየወሩ መቶ ዶላር የጡረታ ገንዘብ እየወሰዱ ህይወታቸውን እንዲመሩ የተወሰነላቸው ጥቂቶች አይደሉም።

ከዓለም ዋንጫው በኋላ አምባገኑኑ መሪ ሞብቱ ሴኮ ለእግር ኳስ ያላቸው ፍላጎት ቀነሰ። ለፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያነት ይጠቀሙበት የነበረውን የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድኑን እርግፍ አድርገው ተዉት። ፕሬዝዳንት ሞብቱም የእግር ኳሱ አልሳካ ሲለው ፊቱን ወደ ቡጢ ስፖርት አዙሯል። ረምብል ኢን ዘ ጀንግ (Rumble in the jungle) የተባለውን የ20ኛውን ክፍለ ዘመን ታላቅ የቡጢ ፍልሚያ አዘጋጅቷል።

እስከ አሁን ድረስ የአረቡ ዓለም የእግር ኳስ ታሪክ ምርጡ ብሄራዊ ቡድን ነው። እ.አ.አ በ1960ዎች የነበረው የኢራቅ ብሄራዊ ቡድን። ብሄራዊ ቡድኑ ብዙ ተሰጥኦ እና ክህሎት በነበራቸው የተዋጣላቸው የእግር ኳስ ኮከቦች ስብስብ የተሞላ ነበር። የአረብ ዋንጫን አራት ጊዜ፣ የገልፍ ዋንጫን ሦስት ጊዜ አንስቷል- ብሄራዊ ቡድኑ።

እ.አ.አበ1986 የዓለም ዋንጫም መሳተፉን መረጃዎች አስነብበዋል። ይህ የሆነው በዘመነ ሳዳም ሁሴን ዘመን ነው። ይሁን እንጂ የሳዳም ሁሴን ልጅ ኡዴ ሁሴን ወደ ስፖርቱ ከመጣ በኋላ ደብዝዟል። ኡዴ ሁሴን ራሱን የኢራቅ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አድርጎ የሾመ ሰው ነው። ልክ እንደ አባቱ አምባገነን እና ጨካኝ እንደነበር የኢራቅ ፉትቦል መረጃ ያሳያል።

በርካታ ስፖርተኞችን ቶርቸር አስደርጓል፤ አስገድሏልም። ዳኞችን በማስፈራራት ውጤትም ያስቀይራል። እ.አ.አ በ1999 የፓን አረብ ዋንጫ ኢራቅ እና ጆርዳን ለፍጻሜ ቢደርሱም የጆርዳን ብሄራዊ ቡድን መሪ ከሆኑ በኋላ ኳሷን መንካት ፈርተው ከሜዳ መውጣታቸውን የኢራቅ ፉትቦል መረጃ አመልክቷል። የአባቱን ስልጣን ተገን አድርጎ ውድድሩን ሲያውክ የነበረው ኡዴ ሁሴን በመጨረሻም ሀገሩ በመለያ ምት ዋንጫውን እንድታነሳ አድርጓል።

የብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ሆኖ በእግር ኳስ ልምምድ ላይ መቅረት በኡዴ ያልተጻፈ ሕግ  ከፍተኛ ቅጣት ያስከትላል። በሀገሪቱ አስከፊ ወደ ሆነው አል ራድዋኒያ እስርቤትም ያስወረውራል። ይህ እስር ቤት ሲኦል ማለት እንደሆነ በወቅቱ የቡድኑ ተጫዋች የነበረው አባስ ራሒም ዛየር በአንድ ወቅት ተናግሯል።

ኡዴ ለ1994ቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ራሱን የቡድኑ አባል እና አምበል በማድረግ ልምምድ ለማድረግ ይገኛል። በልምምድ ቦታም የእርሱን ተግባር የተመለከቱት ተጫዋቾች ይደነግጣሉ። በኋላ ግን እርሱ ለቡድኑ እንደማይመጥን በመረዳት ከአራት ቀናት በኋላ ራሱን ከቡድኑ አግልሏል።

አምባገነኑ ልጅ የዐይን ቀለሙ ያለማረው ስፖርተኛ፣ ዳኛ እና አሰልጣኝን ከስፖርቱ ያግዳል። ከፈለገ ባያጠፋም ዘብጥያ ያወርደዋል፤ ካላዘነለት ደግሞ ከምድረገጽ ያጠፈዋል። ይህ ተግባር እና ምግባሩም በታሪክ እግር ኳስን ከበደሉ ግለሰቦች መካከል ከቀዳሚዎች ተረታ አሰልፎታል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here