“በደም የተጣመረ ወዳጅነት”

0
164

በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ሁለት የሶስተኛው ዓለም ሀገራት  የገዛ ሕዝቦቻቸውን ወደ አንድነት ለማምጣት ወደ ኮሚንስታዊ ሀገርነት ተሸጋግረው ነበር። ኢትዮጵያ እና ኩባ ኮሚንስታዊ መንግሥታትን  መስርተዋል።

በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሁለት ለየቅል የሆነ ርእዮት የሚከተሉ ኃያላን ሀገራትን፤አሜሪካን እና ሶቭየት ዩኒየንን ፈጥሯል። እነርሱም የዓለምን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አሰላለፍ በሁለት ጎራዎች የከፈለ እሽቅድድም ውስጥ አስገብተው ይዘውሩ የነበሩበት ወቅት ነበር። ሁለቱም ሀያላን ለየቅል የሆኑ ርእዮቶችን በማራመድ ተከታዮቻቸውን ለማፍራት የሚያደርጉት እሽቅድድም የተለያዩ ሀገራት እንዲፈጠሩ አድርጓል። በተለይ ሁለቱ የሶስተኛው ዓለም ሀገራት መካከከል ኢትዮጵያና ኩባ ኮሚኒስታዊ መንግሥታት መመስረታቸው የቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ውጤት ተደርጎ ይታሰባል።

የቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ በኩባ እና በኢትዮጵያ ተመሳሳይ የፖለቲካ ለውጦች የተካሄዱበት ነበር። በሁለቱም ሀገሮች ውስጥ አብዮቶች ነበሩ። በ1951 ዓ.ም  ፊደል ካስትሮ የሚመራው የትጥቅ ትግል በአሜሪካ ይደገፍ የነበረውን የወቅቱን የኩባው መሪ ፉልጀኒሲዮ ባቲስታን በማስወገድ ኮሚንስታዊ መንግሥት መስርቷል። ይህ ደግሞ በአሜሪካ አፍንጫ ስር የሶሺያሊስት አብዮት መራመዱ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮባታል። እናም ካስትሮን ለማስወገድ ያልቆፈረችው ድንጋይ አልነበረም። ይሁን እንጅ አልተሳካላትም።

በተመሳሳይ በ1960ዎቹ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት በውስጥ ትግል የተዳከመበት ወቅት ነበር። በኮሎኔል መንግሥቱ የህዝብ መተማመንን እና ብሄራዊ አንድነትን ለመፍጠር በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የመንግሥት ስልጣን በመያዝ እና ሀገሪቱን ወደ ኮሚኒስታዊ መንግሥት መቀየር ተችሏል።

የ1967 ዓ.ም  አብዮትን ተከትሎ ነበር በኢትዮጵያ እና በኩባ መካከል ጠንካራው ግንኙነት በይፋ የተመሰረተው። ከ1967 ዓ.ም በፊት ኢትዮጵያ በምእራባውያኑ ጎራ ነበረች፤ ነገር ግን ኩባ በምስራቁ ጎራ የተሰለፈች ሲሆን የውጭ ፖሊሲዋ ዓለማቀፍ ሶሺያሊስት አንድነትን ማጠናከር እና የአፍሪካ የነፃነት ትግሎችን የመደገፍ አላማ ነበረው።

ደርግ ኢትዮጵያ ሶሺያሊስት ሀገር መሆኗን ሲያውጅ የሶቭየት ህብረትን፣ የኩባን እና የሌሎች ሶሺያሊስት ሀገራትን ፍልጎት በመከተል ነበር።  በዚህ ሁኔታ ፕሬዚደንት መንግሥቱ ሶቭየት ህብረትን በመጎብኘት ወታደራዊ የትብብር ስምምነት ከሶቭየት ጋር መፈራረሟ ሲሰማ ለአሜሪካውያን የሚጎረብጥ ሆነ። አሜሪካ ፊቷን ወደ ሶማሊያ በማዞር ድጋፍ መስጠቷ ደግሞ የመንግስቱ ኃይለማሪያም አስተዳደር የአሜሪካውያን ዲፕሎማቶችን አባረረ። ኤምባሲዋን እና የአሜሪካ ተቋማትን በመዝጋት እርምጃ መውሰዱ መቃቃሩ እንዲለይለት አድርጓል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሱማሊያው ዚያድባሬ  የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ ጦርነት በምስራቃዊው የኢትዮጵያ ግዛት ላይ ማወጁ ሌላ ትኩሳት ነበር። እንዲሁም ኢትዮጵያ በምእራብ በኩል  ከኤርትራ አማፂያን እና ከኦነግ ጋር በመተባበር በሱዳን ትንኮሳ ይደረግባት ነበር። ለኢትዮጵያ ወቅቱ እጅግ አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባት ሁኔታ ነበር። ምክንያቱም የሰለጠነው የኢትዮጵያ ሰራዊት የሀገሪቱን አንድነት እና ሉአላዊ ይዞታዋን ለማጠናከር ከኤርትራ አማፂያን ጋር በመፋለም ላይ አተኩሮ ነበር። የዚያድ ባሬ ጠብ አጫሪ ሰራዊት ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እና የወሰን አንድነት በሚጥስ መልኩ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ወረራ ፈፀመ።

ፊደል ካስትሮ ከዚያ በፊት ጦርነት አይቀሬ መሆኑን ሲረዱት፤ ሁለቱን ሀገራት በመጎብኘት ውጥረቱ እንዲረግብ  ጥረት አድርገዋል። ከዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ፣ የሶማሊያን እና የደቡብ የመንን መሪዎች ሰብስበው በቀጠናው  ሶሺያሊስታዊ መንግሥታት እንዲመሰርቱ ወይም እንዲገነቡ ለማግባባት ሞክረዋል። ነገር ግን ይህ የትም አልደረሰም፤ ዚያድባሬ  በ1969 ዓ.ም ኦጋዴንን ሲወር ነገሩ ሁሉ ተበላሸ። በዚህ ወቅት ነበር የኩባው መሪ ፊደል ካስትሮ ኢትዮጵያን በወታደራዊ መስክ ለማገዝ የወሰኑት።

በዚህ ወሳኝ ወቅት ነበር ከወደ ኩባ ታማኝ የኢትዮጵያ ወዳጅ የተገኘው። የኩባው መንግሥት የኢትዮጵያ ጓዶቹን ለማገዝ ኩባውያን አማካሪዎችን እና ተዋጊ ወታደሮችን በመላክ  አጋርነቱን አሳይቷል። ከ15,000 በላይ የኩባ ወታደሮች ከኢትዮጵያውያን ጀግኖች ጎን ተሰልፈው ልክ እንደ ሀገራቸው ተዋድቀውላታል፣ ደማቸውን አፍስሰዋል።

ኩባ ከወታደራዊው ድጋፍ በተጨማሪ በሽዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በማሰልጠን እና ባላት አቅም ሁሉ የኢትዮጵያን ልማት አግዛለች። በጦርነት ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ   ሕፃናትን ወደ ኩባ ወስዳ እንደወላጅ አሳድጋ ለወግ ማእረግ አብቅታቸዋለች።

ኢትዮጵያውያን ኩባውያንን በትህትናቸው እና በግብረገብነታቸው ይወዷቸው ነበር። አንዲሁም በኩባውያን ቆራጥነት እና የውጊያ ክህሎትም ያደንቋቸዋል። በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ባህር አቋርጠው የህይወት መስዋእትነት ለከፈሉላት ለእነዚህ የቁርጥ ቀን ወዳጅ፤ የኩባውያን ወታደሮች ምስል ያለበት መታሰቢያ ሀውልት ቆሞላቸው ዝንት አለም ሲታወሱ ይኖራሉ።

በአዲስ አበባ የቆመው መታሰቢያ የኢትዮ-ኩባን ወዳጅነት ያስታውሰናል። ይህም በ1970 ዓ.ም የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ኩባን በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር “በደም የተጣመረ ወዳጅነት” ሲሉ ገልፀውታል።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ጥቅምት 4  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here