በደቡብ አፍሪካ ደቡባዊ የባህር ዳርቻ ከ20 ሺህ ዓመት በፊት በጥንታዊ ሰዎች ከጠንካራ አለት የተሰሩ መሳሪያዎች መገኘታቸውን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል፡፡
በደቡብ አፍሪካ የመስክ ጥንታዊ ቅሪት የምርምር ማእከል ተመራማሪዎች በመሬት ውስጥ ተቀብረው 20 ሺህ ዓመታት ያህል ያስቆጠሩ በጥንታዊ ሰዎች ከድንጋይ የተሰሩ መሳሪያዎች መገኘታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
የምርምር ማእከሉ ተመራማሪ እና የቡድን መሪ የሆኑት ሳራ ዋትሰን ግኝቱ በቀጣናው ይኖሩ የነበሩ ጥንታዊ ሰዎች በአደን ላይ የተመሰረተ አኗኗራቸውን እና ከተፈጥሯዊው አካባቢ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት ግንዛቤ እንደሚሰጥ ነው ያሰመሩበት፡፡
ከጠንካራ አለት ተሰነጣጥቀው ከ12 ሺህ እስከ 24 ሺህ ዓመታት መካከል በበረዶ ዘመን መጨረሻ በነበሩ ጥንታዊ ሰዎች የተሰሩ መሳሪያዎች ስለመሆናቸው ተመራማሪዎቹ አብነቶችን አንስተዋል፡፡
በዚያን ዘመን የደቡብ አፍሪካ የባህር ዳርቻ ወይም ድንበሩ ጥቂት ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ የገባ እንደነበር ነው የጠቆሙት – ተመራማሪው፡፡ አሁን ያሉት ዋሻዎችም በውኃ የተሸፈኑ ሳይሆኑ ደረቅ መሬት ሆነው የሜዳ ፍየል፣ ሚዳቋን የመሳሰሉ እንስሳት መገኛ ነበሩ፡፡ ይህ በመሆኑም በቀጣናው የነበሩት ጥንታዊ ሰዎች ህይወታቸውን ለማቆየት በአካባቢው የነበረን ዓለት በመሰነጣጠቅ ስለታም ጠርዝ ያላቸው መሳሪያዎችን በራሳቸው እጅ ይሰሩ፣ ለሌሎችም ጥንታዊ እውቀቱን ያሸጋግሩ እንደነበር ነው ተመራማሪዎቹ የገለጹት፡፡
ተመራማሪዎቹ በደቡብ አፍሪካ በባህር ዳርቻ የተገኘው ጥንታዊ መሳሪያ ወይም መገልገያ በመቶዎች በሚለካ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በናሚቢያ እና ሌሴቶ ከተገኙት፣ ከጠንካራ አለት በጥንታዊ ዘመን ከተሰሩት ጋር መመሳሰሉን አረጋግጠዋል፡፡ ይህም የእውቀት ሽግግር ወይም ሆን ተብሎ የልምድ ማጋራት እንደነበረ አብነት መሆኑ ነው የተሰመረበት፡፡
የጥናቱ መሪ ሳራ ዋትሰን በባህሩ ዳርቻ በሚገኝ ኮረብታ መካከል በገመድ ተንጠላጥለው ወጥተው መቆፈሪያ እና ሌሎች አስፈላጊ መሳሪዎችን አጓጉዘው ጥንቃቄ የተሞላበት ፍለጋ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ ቁፋሮው አቧራ የለበሱ የተቀበሩ ጥንታዊ መገልገያዎችን ከነበሩበት ዳራ ጋር ተዛምዶ አቀማመጣቸው ሳይቀር ሙሉ መረጃ እና ማስረጃ ማሰባሰብን ያካተተ እንደነበር ነው በማጠቃለያነት ያመላከቱት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም