በድርቅ እና በሰላም እጦት የተፈተኑት

0
174

ተማሪ ልእልት ብርሃኑ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ በሚገኘው ማዓርነት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ናት። በዝናብ እጥረት ምክንያት ያጋጠመው ድርቅ ዘንድሮ ከትምህርት እንድትርቅ አድርጓት ቆይቷል:: ይህም የልጅነት ህልሟ እንዳይሳካ  ያደርጋል የሚል  ስጋት ደቅኖባት ነበር::

የልእልት እና መሰሎቿ ችግር ያሳሰበው ትምህርት ቢሮ በቅርቡ በትምህርት ቤቱ የተማሪ ምገባ ጀምሯል:: ይህን መልካም ዜና የሰማችው ልእልትም ያቋረጠችውን ትምህርት ለመቀጠል  ወደ ትምህርት ቤቷ  ተመልሳለች:: ያጋጠሙ ችግሮች ሰፊ መሆናቸው በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ለመሆን ቢያዳግትም የምገባ ፕሮግራሙ መጀመሩ ግን ትምህርቷ ላይ ብቻ እንድታተኩር እንደሚያደርጋት ተናግራለች::

በትምህርት ቤቱ የአምስተኛ ክፍል ተማሪው ናትናኤል ሹመትም እንደ ልእልና ከትምህርት ገበታው አልተለየም:: በርካታ ተማሪዎች የዕለት ምግብ በማጣታቸው ምግብ ለመፈለግ ከትምህርት ገበታ ርቀው እንደ ነበር ግን ያስታውሳል። በአንድ ክፍል ውስጥ ከ20 ያልበለጡ ተማሪዎች ይገኙ እንደነበርም ነው ያስረዳው። አሁን ግን በአንድ ክፍል ከ50 በላይ ተማሪዎች ይማራሉ። መንግሥት የጀመረውን ድጋፍ እስከ ሰኔ እንዲቀጥልም ከፍተኛ ፍላጎት አለው::

የአበርገሌ ወረዳ ኒየረ አቁ ከተማ ነዋሪ እና የትምህርት ቤቱ  ወመህ (ወላጅ መምህር ህብረት) አባል አቶ ወርቁ አየነው “ከችግሮች ሁሉ ክፉው ልጅህን የምታበላው ማጣት ነው! አሁን ግን ተመስጌን ነው፤ ልጆቻችን ወደ ትምህርት ገበታቸው በመመለሳቸው ደስተኞች ሆነናል!” ሲሉ ልጆቻቸው ከትምህርት ርቀው የቆዩባቸውን ጊዜያት እና አሁን የተገኘውን መፍትሄ በተደበላለቀ ስሜት ተናግረዋል::

በአበርገሌ ወረዳ በ12 ትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራም መጀመሩን እና በዚህም ከስድስት ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባው ተጠቃሚ መሆናቸውን ያስታወቁት የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገብረሃና ኪሮስ ናቸው:: የምገባ መርሀ ግብር በተጀመሩባቸው ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ከአንድ ሺህ 150 በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ መመለሳቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል::

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በተደጋጋሚ እንዳስታወቀው በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል:: ለአብነት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም እንዳስታወቁት ግጭቱ  ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት እንዲርቁ አድርጓል::

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ቡድን መሪ አጥናፍ መከተ በበኩላቸው ግጭቱ በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ በማስመልከት መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ለአሚኮ ገልጸዋል:: ክስተቱ የሕጻናትን የነገ ተስፋ የሚያጨልም እና በሀገር ላይ ተሻጋሪ ችግሮችን የሚያስከትል በመሆኑ የትምህርት ተቋማት የቀውሱ ሰለባ መሆን እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል። አሁናዊ ቀውሱም  157 ሺህ 785 ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዳይመለሱ ማድረጉን አረጋግጠዋል::

የጸጥታ ችግሩ በሰሜን ወሎ ዞንም የፈጠረው ጫና ቀላል አልሆነም፤ ዋና አሥተዳዳሪው አራጌ ይመር መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁት 100 ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ምክንያት 29 ሺህ 700 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል። 15 ሺህ 600 ተማሪዎች ደግሞ ትምህርታቸውን አቋርጠዋል:: 49 ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ተጀምሮ እንዲቋረጥም ሆኗል::

በመማር ላይ ያሉትም ቢሆን በጸጥታ ስጋት እና በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠመ የዝናብ እጥረት በተፈጠረ ድርቅ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት ባለመቻላቸው ትምህርታቸውን እያቋረጡ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ:: ለዚህም የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አንዱ ማሳያ ነው:: በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን የአስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ለአሚኮ በኲር አስታውቀዋል::

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ፍታለሽ ምህረቴ ድርቅን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎችን በመመለስ በዘላቂነት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል:: ለዚህም የትምህርት ቤት ምገባ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከነወነ ነው::

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ባደረገው ድጋፍ በዞኑ 64 ትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራም መጀመሩን ምክትል ኃላፊዋ አስታውቀዋል:: ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችም የምገባው ተጠቃሚ ሆነዋል:: የምገባ ፕሮግራሙ መጀመሩ ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የሚያግዝ መሆኑንም ኃላፊዋ አስታውቀዋል::

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ኃይሉ ግርማይ በበኩላቸው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተከናወኑ ሥራዎችን አስመልክተው  መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም መግለጫ ሰጥተዋል:: አስተዳዳሪው በዚህ ወቅት እንዳስታወቁት በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው የሰላም ችግር የመማር ማስተማር ሥራው ክፉኛ ተፈትኖ ነበር:: በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ታጥቆ ይንቀሳቀስ ከነበረው ታጣቂ ቡድን ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለረጅም ዓመታት ከትምህርት ውጪ ሆነው የቆዩ ተማሪዎች ወደ መማር ማስተማሩ እንዲመለሱ ማስቻሉን ተናግረዋል:: በዚህም ትምህርት ተቋርጦባቸው በነበሩ 16 ቀበሌዎች ትምህርት ቤቶች በመከፈታቸው ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ተመልሰዋል:: አሁንም ችግር ውስጥ ያሉ ቀበሌዎችን  ከችግሩ እንዲወጡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ ነው::

በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ከመመለስ ጎን ለጎን በሰሜኑ ጦርነትም ሆነ ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ትኩረት መሰጠቱንም የክልሉ ትምህርት ቢሮ በተደጋጋሚ አስታውቋል:: በሰሜኑ ጦርነት የከፋ ጉዳት የደረሰበት በሰሜን ወሎ ዞን በጋዞ ወረዳ የ013 ቦያ ቀበሌ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ መመለሱ ለዚህ ማሳያ ነው:: የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ግንባታ የተከናወነው ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከዓለም ባንክ በተገኘ የ21 ሚሊየን ብር ድጋፍ ነው:: ትምህርት ቤቱ በሦስት ሕንፃ 10 የመማሪያ ክፍሎች፣ የሴቶች እና የወንዶች መጸዳጃ ቤት  ማካተቱን ገልጸዋል::

የጸጥታ ችግሩ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ባለመፈታቱ  በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት አልተመለሱም፤ በትምህርት ላይ ያሉትም ቢሆን ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መማራቸው ብቁ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል:: የሥነ ልቦና ባለሙያው የሺዓምባው ወርቄ በዚህ ወቅት የሚስተዋሉ ችግሮች በትምህርት አቀባበል ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድሩ በተማሪዎች፣ በወላጆች እና በመምህራን  ተግባራዊ መደረግ ይገባቸዋል ያሏቸውን የመፍትሄ ሐሳቦች ጠቁመዋል::

እንደ ባለሙያው በትምህርት ላይ ያሉትም ሆኑ በጸጥታ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎች እኩል የሥነ ልቦና ጉዳት ያጋጥማቸዋል። ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ በሚሆኑበት ወቅት አዕምሯዊ መረበሽ እና የሀሳብ መበተን ሊያጋጥማቸው ይችላል፤ ይህም አዕምሮ አሉታዊ ነገሮችን እንዲያስተጋባ በማድረግ ለድብርት፣ ለጭንቀት እና ለተለያዩ ሱሶች ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል::

ተማሪዎች ከጦርነት በኋላ ወደ ትምህርት በሚመለሱበት ወቅት ያሳለፉት የችግር ወቅት ከአዕምሯቸው ስለማይጠፋ ወጣ ያሉ ባህሪያት መገለጫቸው ይሆናሉ። እናት ወይም  አባቱ ሲገደል ያየ ታዳጊ አዕምሮው የሚያስበው የተጠቂነት እና የአቅመ ቢስነት ሥነ ልቦና በመሆኑ ከመጠቃት ይልቅ ማጥቃትን (በቀል) ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ሊነሳ ይችላል:: እናም ይህ ሁኔታ በሰዎች ላይ በሚስተዋልበት ወቅት ያለፉ ታሪኮችን በመጠየቅ ስሜታቸውን መጋራት፣ ችግራቸውን መካፈል፣ አለሁልህ /ሽ/ በማለት ወደ ነበሩበት ሕይወት እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል::

ከግጭት ወይም ጦርነት መልስ ተማሪዎች ለትምህርት ቤት ሕግና ደንብ ተገዥ ላይሆኑም ይችላሉ:: ታዲያ በዚህ ወቅት መምህራን እና የትምህርት አመራሩ ተማሪዎችን በጥፋተኝነት ከመፈረጅ ይልቅ አቅርቦ ህመማቸውን መረዳት እንደሚገባ አሳስበዋል:: በዚህ ወቅት እያንዳንዱ መምህራን የሥነ ልቦና ባለሙያ ሆኖ ተማሪዎች ከገቡበት ያልተገባ ባህሪ እንዲወጡ ማድረግ እንደሚኖርበት ጠቁመዋል::

ተማሪዎችም አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ሲደረግ ከእነሱ የሚጠበቀውን ለተነሱለት ዓላማ ስኬት የሚያበቃቸውን  ብቻ ከመከወን ውጪ ስለ ሌላ ነገር ሊያስቡ እንደማይገባቸው ባለሙያው ጠቁመዋል:: በተለይ “ዛሬ የተከፈተው ትምህርት ነገ ይዘጋ ይሆን? ለፈተናስ እንደርሳለን? ይዘቱስ በወቅቱ ይሸፈን ይሆን?” በሚሉ ጉዳዮች ተማሪዎች ሊጨነቁ እንደማይገባ ጠቁመዋል:: ከተማሪዎች የሚጠበቀው የሚሰጠውን ትምህርት በንቃት መከታተል፣ ከትምህርት ውጪ የሆኑ ጊዜያትን በአግባቡ መጠቀም፣ ለነገ ግብ አወንታዊ ምልከታ ማድረግ ብቻ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል::

ወላጆች ችግር እና መከራን አብዝቶ ከማውራት በጎ ነገሮችን ማስተጋባት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል:: ሰዎች አንድ ቦታ ላይ የሚደርሱት ሲጀምሩት ነው ያሉት የሥነ ልቦና ባለሙያው፣ ለዚህም ያልጨረስነውን ከማየት ይልቅ በጀመርነው ላይ ትኩረት ማድረግ ለውጤት እንደሚያበቃ አስገንዝበዋል::

ትምህርት ያልጀመሩ ተማሪዎችም “ለራሴ ያለሁት እኔ ነኝ” የሚል አመለካከትን በማዳበር ካልተፈለገ አካሄድ ራሳቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ አሳስበዋል:: ነገን በአዎንታ መመልከት፣ ቤተሰብን በሥራ ማገዝ፣ ዕውቀትን ሊያስጨብጡ እና አስተሳሰብን በመልካም ሊቀይሩ የሚችሉ መጻሕፍትን ማንበብ፣ ነገ ትምህርት እንደሚጀመር አስቦ ለትምህርት ራስን ዝግጁ ማድረግ፣ ትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅት ጊዜ አጥተው ወደ ጎን ትተዋቸው የነበሩ የተለያዩ ክህሎቶቻቸውን ማየት ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን ተከትሎ ወደ አልተፈለገ ቦታ የማምራት ፍላጎታቸውን ለመግታት የሚያስችሉ የመፍትሄ ሐሳቦች አድርገው አቅርበዋል::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here