የጀርመኑ ክለብ ባየርሙኒክ 33ኛውን የቡንደስ ሊጋ ዋንጫ አሸንፏል። እንግሊዛዊው አጥቂ ሀሪኬን በተጫዋችነት ዘመኑ የመጀመሪያውን ዋንጫ ሲያሸንፍ ቤልጄማዊው አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒም በቡንደስ ሊጋ የመጀመሪያውን ዋንጫ አሸንፏል። የባቫሪያኑ ክለብ በጀርመን ዋንጫ እና በሻምፒዮንስ ሊጉ ቀድሞ ቢሰናበትም የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ ግን ቀሪ ሁለት ጨዋታ እያለው ነው ማንሳቱን ያረጋገጠው።
ባየርሙኒክ በዚህ ዓመት ምርጥ አቋም በማሳየት ጭምር ነው ዋንጫውን ያነሳው። የጀርመኑ ኃያል ክለብ በአሰልጣኝ ኮምፓኒ እየተመራ በሁሉም የሜዳ ክፍል ድንቅ መሆኑን አስመስክሯል፤ በተለይ የኋላ ክፍሉ እና የፊት መስመሩ በቡንደስ ሊጋው የተዋጣለት እንደነበር በእያንዳንዱ ጨዋታ አስመስክሯል። ምስጋና ለቤልጂየማዊው አሰልጣኝና ከሜዳው ውጪም በመልበሻ ክፍሉ አስደሳች የቡድን መንፈስ መኖሩ በዋንጫ ታጅበው እንዲያጠናቅቁ አግዟቸዋል።
ቤልጄየማዊው አሰልጣኝ በ2022/23 የውድድር ዘመን በበርንሌይ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማሳደጉ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ከአንድ ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ቆይታ በኋላ ክለቡ ሊጉን መቋቋም እና መላመድ ተስኖት ወደ መጣበት መመለሱ አይዘነጋም። በ2023/24 የውድድር ዘመን ስፔናዊው አሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶ ባየርሊቨርኩሰንን እየመራ የመጀመሪያውን የቡንደስ ሊጋ ዋንጫ ካሳካ በኋላ የአሰልጣኝ ቶማስ ቱሄል ሥራ በአሊያንዝ አሬና አደጋ ላይ ወድቋል።
በመጨረሻም ጀርመናዊው አሰልጣኝ ከሥራው ሲሰናበት በምትኩ ቤልጄየማዊው ቪኒሰንት ኮምፓኒ ነበር ዙፋኑን የተረከበው። ታዲያ በወቅቱ በርንሌይን ከፕሪሚየር ሊጉ ይዞት የወረደው አሰልጣኝ ለጀርመኑ ኃያል ክለብ ኃላፊነት እንዴት ሊመጥን ይችላል? የብዙዎች ጥያቄ ነበር።
በሌላ በኩል የኮምፓኒን ቅጥር የርገን ክሎፕ ወደ ቦርሲያ ዶርትመንድ ከመጣበት ጊዜ ጋር ያነፃፀሩትም አልጠፉም። የርገን ክሎፕ በ2008 እ.አ.አ ሜንዝን ወደ ታችኛው የሊግ እርከን በወረደ ማግስት ነበር የቦርሲያ ዶርትመንድ አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመው።
ታዲያ ይህንን የተገነዘቡ ደጋፊዎች ግን በኮምፓኒ እምነት አሳድረው ነበር፤ አሁን በአሊያነዝ አሬና ስቴዲየም እምነታቸው ተግልብጦ ተመልክተውታል፡፡ ኮምፓኒ በባየረሙኒክ ቤት ከወጣት ተጫዋቾች ጋር ተግባብቶ መሥራቱ ውጤታማ እንዲሆን አስችሎታል።
በአሊያንዝ አሬናም አዲስ የእግር ኳስ አብዮት ፈጥሯል። አዝናኝ እግር ኳስ የሚጫወት እና የሚያጠቃ ቡድን ገንብቷል። በተለይ በ2-4-4 የአሰላለፍ ስልት የመስመር አጥቂዎች ማይክል ኦሊሴ እና ሌሮይ ሳኒ አስፍተው በመጫወት የተጋጣሚ ቡድንን ፋታ በመንሳት ቡድኑ አስፈሪ መሆኑን አሳይቷል።
አማካዮች እና የኋላ ተመላላሾችም በተጋጣሚ የግብ ክልል እና በኮሪደሩ በመመላለስ እረፍት አልባ እንቅስቃሴ በማድረግ የኮምፓኒ ቡድን የልብ ምት ሆነዋል። በዚህ ዓመት የባየርሙኒክን ያህል የኳስ ቁጥጥር የነበረው፣ ብዙ ግብ ያስቆጠረ እና አነስተኛ ግብ የተቆጠረበት ክለብ አልነበረም። ይህም ሜዳ ላይ ፍሬ አፍርቶ ታይቷል።
በውድድር ዓመቱ ባየርሙኒክ በአማካይ 64 በመቶ የኳስ ቁጥጥር እንደነበረው የቡንደስ ሊጋ ድረግጽ ያስነብባል። በማጥቃቱ ብቻ ሳይሆን በመከላከሉም የተዋጣለት እንደነበረ ቁጥሮች ይናገራሉ።
ኮምፓኒ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ የደች እና የጀርመን ቋንቋዎችንም አቀላጥፎ መናገሩ ከተጫዋቾች ጋር በቀላሉ ሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም ተግባብቶ እንዲሰራ አግዞታል። ቡድኑ ውስጥ የተለየ ባህል ፈጥሯል፤ የተጫዋቾች ተነሳሽነት እንዲጨመር አድርጓል። ለዚህ ደግሞ ጀማል ሙሲያላ፣ ጆሽዋ ኪሚች እና ሰርጂ ናብሪ ምስክርነት ሰጥተዋል።
ኮምፓኒ በመጀመሪያው ዓመት የባየርሙኒክ ዘመን ምርጥ የሚባል ጊዜ አሳልፏል። ይህም በፕሪሚየር ሊግ እና በላሊጋ ሌላ ኃላፊነት መሸከም እንደሚችል አስመስክሯል ይላል- የቡንደንስሊ ጋው ድረግጽ መረጃ።
የ39 ዓመቱ አሰልጣኝ በመጀመሪያው ዓመት የቡንደስሊጋ አሰልጣኝነት ዘመኑ ዋንጫ ማሳካት ችሏል። በአሰልጣኝ ቶማስ ቱሄል ዘመን ተሰልቦ የነበረው የማሽነፍ ስነልቦናውን ኮምፓኒ በአንድ የውድድር ዘመን በማስተካክለ ለዋንጫ አብቅቶታል። በአሰልጣኝ ቶማስ ቱሄል የመጨረሻው ዘመን በክለቡ ታሪክ እጅግ መጥፎ የተባለውን የውድድር ጊዜ ማሳለፉ አይዘነጋም። አምና ከሻምፒዮናው ባየርሊቨርኩሰን በ18 ነጥብ ርቆ ዓመቱን መጨረሱ የሚታወስ ነው።
ቪኒሰንት ኮምፓኒ በመጀመሪያው የውድድር ዘመኑ ዋንጫ ያነሳ አሰልጣኝ ሆኖ በባቫሪያኖቹ ቤት ስሙ ተመዝግቧል። ብራንኮ ዜቢች፣ ሊዊስ ቫንሀል፣ ፔፕ ጓርዲዮላ፣ ካርሎ አንቸሎቲ፣ ሀንሲ ፍሊክ እና ቪኒሴንት ኮምፓኒ በአሊያንዝ አሬና የመጀመሪያ ዓመት ውድድራቸው በሊጉ በዋንጫ ታጅበው ያጠናቀቁ አሰልጣኞች ናቸው።
ኮምፓኒ በቡንደስ ሊጋ ታሪክ የመጀመሪያው ጥቁር አሰልጣኝ ሲሆን በጀርመን እግር ኳስ ታሪክ ደግሞ ሁለተኛው ጥቁር አሰልጣኝ ነው። አሁን ደግሞ ኮምፓኒ አዲስ ታሪክ ጽፏል፤ የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ በማንሳት የመጀመሪያው ጥቁር አሰልጣኝ ሆኖ በታሪክ መዝገብ ሰፍሯል።
በሀገሩ ቤልጂየም በሚገኘው ክለብ አንደርሌክት እግር ኳስን ጀምሮ በጀርመኑ ሀምቡርግ ጎልብቶ በማንቸስተር ሲቲ ቤት ያንፀባረቀው ኮምፓኒ በኢትሀድ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይቷል። የቀድሞው የተከላካይ አማካይ ከ2010 እስከ 2018 እ.አ.አ ወኃ ሰማያዊ ለበሾችን በአምበልነት አገልግሏል። ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በቆየባቸው 11 ዓመታት አራት የፕሪሚየር ሊግ ሁለት የኤፍ ኤ ዋንጫ፣ እና አራት የካራባዋ ዋንጫን አሳክቷል።
የቀድሞው የመሀል ተከላካይ እ.አ.አ በ2017 ነበር የሁለተኛ ዲግሪውን በንግድ ሥራ አስተዳደር በአሊያንስ ማንቸስተር ቢዝነስ ትምህርት ቤት ያጠናቀቀው። የመመረቂያ ፕሮጀክቱም ድንቅ እንደነበር የዘ ኢንድፔንደንት መረጃ ያትታል።
በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ከምርጥ የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋች እንደነበረም አይዘነጋም። ኮምፓኒ በልጅነት ክለቡ አንደርሌክት ለሁለት ዓመታት ያህል አሰልጣኝ ሆኖ ከሠራ በኋላ ወደ እንግሊዝ መጥቶ በርንሌይን ለሁለት ዓመታት አሰልጥኗል።
የኳስ ቁጥጥርን እና ማጥቃትን መሰረት ያደረገ የአጨዋወት ስልት ተግባራዊ በማድረግ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። በርንሌይንም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማሳደግ ችሎ ነበር። በፕሪሚየር ሊጉም ከአሁኑ የኖቲንግሀም ፎረስቱ አሰልጣኝ ኑኖ ስፕሪቶ ሳንቶ ቀጥሎ ሁለተኛው ጥቁር አሰልጣኝ ሆኖ ተመዝግቧል።
በርንሌይ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ባደገበት ዓመት ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ከወረደ በኋላ የኮምፓኒ ፍልስፍና ውጤት ላይ ያተኮረ (pragmatism) አይደለም ተብሎ ሲተች እንደነበር አይዘነጋም።
ኮምፓኒ የፔፕ ጓርዲዮላ ተጽእኖ እንዳለበት ይናገራል። የሥራዎቹ እና የስብዕናው ትልቅ አድናቂ ነኝ ይላል የ39 ዓመቱ አሰልጣኝ። ኮምፓኒ በ2019 እ.አ.አ በአንድርሌክት ከስፔናዊው ታክቲሽያን ብዙ ልምድ እንዲቀስም እና ተመሳሳይ የእግር ኳስ አቀራረብ እንዲከተል በር ከፍቶለታል።
አሁን ላይ ባየርሙኒክ የራሱን የእግር ኳስ ባህል የሚያስቀጥል አሰልጣኝ ከረጅም ዓመታት በኋላ ማግኘቱ እፎይታ ተሰምቶታል፤ በአሊያንዛሬና የተፈጠረው ምቹ የሥራ ከባቢ አየር የሚቀጥል ከሆነ ከዚህ የበለጠ ክለቡን ወደ ተሻለ ክብር እንደሚመራው የባየርን ስትሪክስ መረጃ አስነብቧል።
(ስለሺ ተሸመ)
በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም