በገንዘብ የማይለካው

0
140

“ሁሉም የየራሱ ትውስታ ይኖረዋል። በተለይ በበዓላት ወቅት፡፡ የገና በዓል ደግሞ ለእኔ ልዩ ቦታ አለው፡፡ በዓሉ ሊደርስ አካባቢ ተሰባስበን፣ የቅርጫ ሥጋ ተከፋፍለን፣ በዚያውም የሆድ የሆዳችንን ተነጋግረን ወደ የቤታችን እንሄዳለን፡፡ የማይተዋወቁ ሁሉ እንዲህ ስንሰባሰብ ቤተሰብነት የመሠረቱም አሉ” ሲሉ የበዓል ትዝታቸውን ያካፈሉን አቶ ሀብቴ ባይህ ናቸው፡፡

ሐሳባቸውን ያካፈሉን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አሁንም ድረስ የገና በዓል ሲመጣ ሰዎችን በማሰባሰብ እና ሁሉም እንደየአቅሙ የቅርጫ ሥጋ እንዲወስድ ያደርጋሉ፡፡

በኢትዮጵያዊያን ዘንድ በበዓላት ወቅት ማኅበረሰቡ ደስታውን ከሚገልጽባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ እርድ መፈጸም ነው፡፡ እርድን አከናውኖ ከጎረቤት እና ከዘመድ አዝማድ ጋር ተጠራርቶ መብላትም የተለመደ ነው፡፡  የሥጋ ቅርጫ  በስፋት ከሚከናወንባቸው በዓላት መካከልም የመስቀል እና የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓላት ይጠቀሳሉ፡፡ ታዲያ በእነዚህ በዓላት ሰዎች በየአካባቢያቸው ተሰባስበው እንደየ አቅማቸው  በሬ በመግዛት አርደው ሥጋውን ይከፋፈላሉ፡፡ በዓሉንም ያከብራሉ፡፡

ይህ ማሕበራዊ ተግባር ታዲያ በዓልን ከማድመቅ ባለፈ ሁሉም እንደየአቅሙ እንዲያከብር ያድርጋል፡፡ የርስበርስ ማሕበራዊ መስተጋብርንም ያጠናክራል፡፡ መግቢያችን ላይ ሐሳባቸውን ያነሳነው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አቶ ሀብቴ ባይህ ደግሞ የዚህ አብነት ናቸው፡፡ ለበርካታ ዓመታት ሰዎችን በማሰባሰብ (በማቧደን) እንደየአቅማቸው የቅርጫ ሥጋ እንዲወስዱ ያደርጋሉ፡፡

ይህን ልምድ ከቤተሰቦቻቸው እንዳገኙት ያጫዎቱን ሲሆን በዚህም ከበርካታ ሰዎች ጋር ማሕበራዊ ሕይዎታቸውን እና መስተጋብራቸውን እንዳሻሻሉ ነግረውናል፡፡ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ሀብቴ ከበዓላት በተጨማሪ በአዘቦት ቀናትም ሥጋ መብላት የፈለገ ነገር ግን በግ ወይም ፍየል መግዛት ያልቻለ ሰው ተጠራርቶ አቅሙ የቻለውን በማዋጣት በቅርጫ ሥጋ አምሮቱን እንደሚቆርጥ አጫውተውናል፡፡

ሥጋ በማቃረጥ ልምዳቸውም ቅርጫ ሲነሳ የሚያውቋቸው ሁሉ አቶ ሀብቴን ያነሳሉ፡፡ “የትኛው የተሻለ ሥጋ እንደጨበጠ ሀብቴ ይይልን” ይሉኛል ይላሉ፡፡ እርሳቸውም የትኛው በሬ በሰው ሠራሽ (በአርቲፊሻል) መንገድ እንደደለበ ማለትም የሚያደልብ መርፌ እንደተወጋ ወይም ተፈጥሯዊ  (እንዳልተወጋ) መሆኑን ባካበቱት የዘመናት ልምድ እንደሚለዩ ገልጸውልናል፡፡

አቶ ሀብቴ እንደሚሉት የሚያደልብ መርፌ የተወጋ በሬ ቆዳው ላይ ያለው ጸጉር በእጅ ሲነካ (ሲዳበስ) ይረግፋል፡፡ በተቃራኒው በተፈጥሮ ሳር፣ ፉርሽካ እና የጠላ አተላ የተመገቡ በሬዎች ደግሞ ቆዳቸው እንኳን ተነክቶ በእጅ ቢነጩትም እንደማይረግፍ ጠቁመውናል፡፡

አቶ ሀብቴ እንዳጫዎቱን በሥጋ ክፍፍል በኩል እንደበሬው መጠን ቢለያይም አንድን በሬ  ለስድስት ወይም ለስምንት በጋራ ተገዝቶ ይቃረጣል፡፡ አሁን ላይ ባለው የኑሮ ውድነት ምክንያት መደቡ ለስምንት ከሆነ አንድ መደብ መቃረጥ ያልቻለ ግለሰብ ለሁለትም ለአራትም (ግማሽ ወይም ሩብ) ሆኖ አንዱን መደብ ይቃረጣሉ፡፡

“ቅርጫ ከዚህም በላይ በገንዘብ የማይተመን ትሩፋት አለው” የሚሉት አቶ ሀብቴ የሚፈጥረው ማሕበራዊ መስተጋብር ልዩ መገለጫው መሆኑን ያነሳሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት የቅርጫ ሥጋ ኢኮኖሚን ከማገዙ ባለፈ ከግዥው ጀምሮ ያለው ሂደት ማሕበራዊ ትስስርን የሚያጠናክር ነው፡፡ ተጠራርቶ ልምድ ባላቸው ሰዎች በሬው ከተገዛ በኋላ እርድ በሚፈጸምበት መኖሪያ ቤት ምግቡ እና መጠጡ (ባሕላዊ) ይዘጋጃል፡፡

እርድ የሚፈጸመውም በፊት ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት እንደነበረ ነገር ግን ጨለማ ስለሆነ በንጽህና ለማረድ አስቸጋሪ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ረፋዱ 3 ሰዓት ድረስ እንደሚያከናውኑ ነው የነገሩን፡፡

አቶ ሀብቴ እንደሚሉት ቅርጫን በጣም የሚወዱት ከምግብነቱ ይልቅ ባለው ማሕበራዊ ትስስር ነው፡፡ ለቅርጫ ሲሉ ከተለያዩ ሰፈሮች (ቦታዎች) ዘመዶች እና ጎረቤቶች ከዚህበፊት በእሳቸው ሰፈር ይኖሩ የነበሩ አሁን ግን የመኖሪያ ሰፈራቸውን የቀየሩ ሰዎች ሁሉ የሚሰባሰቡበት በመሆኑ ነው፡፡

በዓላቱም፣ የቅርጫው ሥርዓትም እስኪደርስም ይናፍቃሉ፡፡ ከታረደ በኋላም ምላስ እና ሰንበር ተጠብሶ ይበላል፡፡ ቀደም  ሲል ባሕላዊ መጠጡ በሚታረድበት መኖሪያ ቤት ነበር የሚሸፈነው፡፡ አሁን ግን ኑሮ ስለተወደደ ሁሉም የሥጋ ተቃራጮች እኩል ገንዘብ ያዋጣሉ፡፡ “ከዚያ በኋላማ ጨዋታው ይደራል፤ የማይነሳ ሀሳብ የለም” ነው ያሉን፡፡ “ልጅህ የት ደረሰ/ች? ትምህርቷን ጨረሰ/ች? አገባ/ች? ወለደ/ች”? የተሰብሳቢዎቹ ቤተሰባዊ የሐሳብ ልውውጥ ከሚደረግባቸው መካከል ናቸው፡፡

ከዚህ ባሻገር በዕድሜ የገፉ ሰዎች ስላሳለፉት የሕይዎት ውጣ ውረድ ለወጣቶቹ ተሞክሯቸውን እንደሚያካፍሉ፣ ወጣቶቹ  ስለፍቅር ጓደኞቻቸው፣ ካገቡ ደግሞ ስለ ትዳር አጋራቸው፣ ስለልጆቻቸው እና ስለአባትነት ሀሳብ እንደሚያነሱ እንደሚጥሉ አጫውተውናል፡፡   “አሁን አሁን ደግሞ ወጣቶቹ የኳስን ነገር እያበዙብን ነው፤” ያሉን አቶ ሀብቴ በዚህ ወቅት ታዲያ ትልቆችም አስፈላጊውን ምክር (የተሳሳተ መንገድ ላይ ላሉት) ይለግሳሉ፤ እንዲሁም ስለ ሀገራቸው፣ ስለፖለቲካው፣ ስለ ኑሮው፣ ስለ ዓለም አጠቃላይ እየተጠያየቁ እርዱ ይከናወናል፡፡ ሥጋው እኩል ተመድቦ በዕጣ የማን እንደሆነ ተለይቶ ሁሉም ወደየቤቱ እስኪመለስ ጨዋታው እንደሚቀጥል ገልጸውልናል፡፡

አቶ ሀብቴ ቀደም ሲል በየሜዳው እና በየሠፈሩ ይጣል የነበረው የእንስሳቱ ተረፈ ምርት እና ደምም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መስተካከሉን ነግረውናል፡፡ እርዱ ሲከናወን ደሙን በእቃ ያስቀምጣሉ፣ የፈርሱን እና ሌሎች የሚወገዱ የበሬውን ክፍሎችም በሌላ ቆሻሻ ማስቀመጫ በማስቀመጥ የከተማውን የጽዳት ሥራ የሚያከናውኑ አካላትን ደውሎ በመጥራት እንደሚያስነሱ ነግረውናል፡፡ ቀደም ሲል ግን እንዲሁ በየመንገዱ ይጣል ስለነበር ተረፈ ምርቱ መጥፎ ሽታ በመፍጠር  አካባቢን ይበክል እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ሌላዋ ሐሳባቸውን ያካፈሉን የሁለት ልጆች እናት የሆኑት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ ሃና ባንቲደር ናቸው፡፡ ቅርጫ ሥጋ መቃረጥ ከሚያስገኘው ማሕበራዊ ፋይዳ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊው ፋይዳው ላቅ ያለ እንደሆነ ነው ያጫዎቱን፡፡ እርሳቸው እርድ በሚከናወንበት ሥፍራ ባይገኙም ልጆቻቸውን ይልካሉ፡፡ ልጆቻቸውም ከሰው ጋር የመግባባት ልምድን እያዳበሩ ጠያቂ ዘመድ እንዳፈሩበት ነግረውናል፡፡

ወ/ሮ ሃና ከጎረቤቶቻቸው ወይም ከዘመዶቻቸው ጋር በመቧደን በተለይ የመስቀል እና የልደት በዓላት ከመድረሳቸው በፊት ለቅርጫ ሥጋ ገንዘብ ያስቀምጣሉ፤ እንደየአቅማቸውም ይከፋፈላሉ፡፡

ወ/ሮ ሃና እንዳጫዎቱን ከሁለት እና ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን የኑሮ ውድነቱ በጣም ስላሻቀበ ቀደም ሲል በግ እና ፍየል አርደው በዓሉን ያሳልፉባቸው የነበሩት የዘመን መለወጫ እና የፋሲካ በዓላትም በቅርጫ ሥጋ   እያሳለፉ እንደሚገኙ አጫውተውናል፡፡ የቅርጫ ሥጋን እንደ አቅም ተካፍሎ  በዓሉን ከወዳጅ ዘመድ ጋር ማሳለፍ ደስ የሚያሰኝ ዕሴት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ከኑሮ ውድነቱ የተነሳ በበዓላት ጊዜ የሚከናወነው የሥጋ ቅርጫ ሥርዓት እና ትውፊት የቀደመው የመተሳሰብ፣ የመሰባሰብ እና የመደጋገፍ ዕሴቱ እየተሸረሸረ እንደመጣ የነገረን ደግሞ ወጣት ክፍሌ ቢሆን ነው፡፡ የገንዘብ አቅም ካላነሰ በስተቀር ሰዎች በግላቸው በግ ወይም ፍየል ቢያርዱም ለቁርጥ እና ለጥብስ እንዲሁም ሥጋው ብዙ ይሆናል በሚል  የቅርጫ ሥጋ በአብዘኛው ሰዎች ዘንድ የተለመደ እንደሆነ ነው ያጫወተን፡፡

ወጣት ክፍሌ እንደሚለው እሱ ተወልዶ ባደገበት ሰፈር ትላልቅ አባቶች ቅርጫ ይገባሉ፡፡ ልጆችም ወላጆቻቸው የተቃረጡትን ሥጋ ለመውስድ እርድ የተፈጸመበት መኖሪያ ቤት  አብረው ይሄዳሉ፡፡ ይህም ከሌሎች ልጆች ጋር መተዋወቅን ይፈጥርላቸዋል፡፡ እንዲሁም ማሕበራዊ ሕይዎትን እንዴት መኖር እንዳለባቸው ልምድ ይቀስሙበታል፡፡ በቤተሰቦቹ ቤት ለበዓል በግ ከታረደ  ለጎረቤት እና ለዘመድ አዝማዱ ምሳ ወይም የእራት ግባዣ ስለሚኖር ሥጋው እንዲበቃ በሚል የቅርጫ ሥጋ ሁልጊዜ አይቀርም ብሎናል፡፡

እላይ የጠቀስንላችሁ የማሕበረሰብ ክፍሎች እንደገለጹት ቅርጫ ፋይዳው ሰፊ ነው፡፡  የማይተዋወቅን ሰው ሁላ ቅርጫ ያስተዋውቀዋል፡፡ ቅርጫ ከፈለጉ ወደ ከብት ገበያ በመሄድ “መቃረጥ የሚፈልግ ወደ እኔ ይምጡ” እያሉ ሰዎችን መጣራት ብቻ ይበቀዎታል፡፡ ታዲያ በፍጥነት በርካታ ሰዎች በዙሪያዎት ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም እነሱም የሚቃረጥ ሰው እየፈለጉ ነበርና፡፡ ከዚያም እስከ ስንት ብር አንዱን መደብ መቃረጥ እንደምትችሉ ያላችሁን አቅም አውቃችሁ የበሬውን መጠን ትወስናላችሁ ከመሀከላችሁ ከብት በመግዛት ልምድ ያላቸውን  ሰዎች መርጣችሁ ግዥውን መፈጸም እና እርዱን ማከናወን እና መቃረጥ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ከቡድኑ አባላት ጋር ስልክ ተቀያይሮ ለሌላ ጊዜ ቅርጫ የምትፈልጉ ከሆነ እንድትደዋወሉ ተነጋግራችሁ መለያየት ነው፡፡ በዚህም አንድ ሰው ቢያንስ ስድስት ሰው ጋር ማሕበራዊ ግንኙነት እንደ አዲስ ጀመረ ማለት ነው፡፡ በቅርጫ አስተዋውቋቸው  በአሁኑ ጊዜ በሃዘን እና በደስታ የሚጠያየቁ ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡

ቅርጫ አስተዋውቋቸው ወደ ቤተሰብነት የተሸጋገሩም በርካታ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ ከማሕበራዊ መስተጋብር መራቅ ከቶውንም አይቻለውም፡፡ ሰው ማሕበራዊ እንስሳ ነውና፡፡ ቅርጫ ደግሞ የዚህ አንዱ መገለጫ ዕሴታችን ነው፡፡

ልብ ሊባል የሚባለው ነገር የቅርጫ ሥጋ የበሬውን ጤንነት ስለማያረጋግጥ ጤናቸው የተመረመሩ ከብቶችን ከቄራ ቢገዙ እና ሲታረዱም አካባቢን በማይበክል መንገድ ቢከናውን ምልካም ነው የሚል ሐሳብ በኩር ታጋራለች፡፡

መልካም በዓል!

 

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የታህሳስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here