“በጋዜጠኝነት ሙያ የቡድን ሥራ በጣም ወሳኙ ጉዳይ ነው”

0
178

“በጋዜጠኝነት ሙያ የቡድን ሥራ በጣም ወሳኙ ጉዳይ ነው፤ የአንድ ጋዜጠኛ ስህተት የተቋሙ ስህተት ተደርጐ ስለሚወሰድ ሙያው በጋራ መቆምን የግድ ይላል” በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን /አሚኮ/ አንጋፋዉ ጋዜጠኛ ታምራት ሲሳይ ከተናገረው የወሰድነው ነው::

ታምራት ተወልዶ ያደገው በቀድሞው የሀረርጌ ክፍለ ሀገር፣ ወበራ አውራጃ፣ ሜታ /ጨለንቆ/ ወረዳ፣ ቁልቢ ውስጥ ነው:: ቁልቢ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ “ቁልቢ ገብርኤል” በሚለው የንግሥ ቦታነቷ ነው ምትታወቀው ::

ቁልቢ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል አስገንብቶ ያስተምር ስለነበር ታምራትም ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን የተከታተለው በዚሁ በቁልቢ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት ውስጥ ነው:: ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን ደግሞ በደደር እና ሀረር ከተሞች ተከታትሎ ባመጣው ከፍተኛ ውጤት መሠረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቱ ተምሮ የመጀመሪያ ዲግሪውን ይዟል::

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ላይ የጋራ “ኮመን ኮርስ” የሚባሉትን ትምህርቶች የተማረው ታምራት ሁለተኛ ዓመት ላይ የሚማሩበትን የትምህርት ክፍል እንዲያሳውቁ በተጠየቀው መሠረት የመጀመሪያ ምርጫውን ፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አድርጐ መርጧል፤ በሁለተኛነት የመረጠው እና የፀደቀለት የትምህርት ዘርፉ ደግሞ ቲያትሪካል አርት የሚለውን ነው::

በ1984 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘው ጋዜጠኛ ታምራት በዚያው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በማዘጋጃ ቤት ሠራተኝነት የሥራውን ዓለም ለመቀላቀል ጥረት ያደረገ ቢሆንም በወቅቱ በነበረው ግርግር ምክንያት ሀሳቡ ተፈፃሚ አልሆነለትም:: ታምራት በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ያስመዘገበው ጥሩ ውጤቱ በዚያው በአስተማሪነት ሊያስቀረው የሚችል ቢሆንም ከወቅቱ ጋር በተያያዘ የዩኒቨርሲቲ መምህርነት እድልን አላገኘም::

የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አልሳካ ሲለውም በባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቅጥሩን ማመልከቻ ከጓደኞቹ ጋር አስገብቷል:: የወቅቱ የፌዴራል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ በአዲስ አበባ ቦታ ባይኖረውም በባሕር ዳር እና ሌሎች ከተሞች ክፍት የሥራ መደብ መኖሩን ጠቁሟቸዋል:: ድሬደዋ አካባቢ ተወልዶ ላደገው ታምራት ባሕር ዳር እንደ ስሟ ባሕር ዳር የምትገኝ የጠረፍ ከተማ ስለመሰለችው ወደ ባሕር ዳር ለመሄድ ሥጋት ቢያድርበትም የተሻለ አማራጭ ስላልነበረው ወደ ባሕር ዳር አቅንቷል::

በምዕራብ ጐጃም ዞን ባህል፣ ቱሪዝም እና ማስታወቂያ ቢሮ /ባቱማ/ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ሥራውን አንድ ብሎ የጀመረው የዛሬው የኛ ገጽ አምድ እንግዳችን በባሕር ዳር የሥራ ቆይታው በርካታ የቲያትር ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ለፍሬ አብቅቷል:: ለአብነትም በባሕር ዳሩ የሙሉ ዓለም ባህል ማዕከል ውስጥ የቲያትር ባለሙያ ሆነው የሚሠሩት ግዮን አለምሰገድ፣  ጋዜጠኛ ሀይሌ አበራ፣ ጋዜጠኛ ሽመልስ ከበደ እና ሌሎችም በታምራት ሲሳይ እና ሌሎችም ታንጸው ለትልቅ ደረጃ የበቁ ባለ ሙያዎች ናቸው::

ታምራት ያሰለጥናቸው ከነበሩ የቲያትር ባለሙያዎች ውስጥ አንዳንዶቹ በሙያው የዘለቁበት ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ሕይወታቸውን በሌላ የሙያ መስክ መምራት ቀጥለዋል::

ታምራት በ1989 ዓ.ም ሥራ እና ሠራተኛን ማገናኘት በሚለው የመንግሥት አሠራር መሰረት ደቡብ ጐንደር ዞን ደብረ ታቦር ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ተመድቦ ሠርቷል::

በ1988ዓ.ም  በያኔው ባቱማ /ባህል ቱሪዝም እና ማስታወቂያ/ ቢሮ ውስጥ በሙሉዓለም የባህል ማዕከል በቲያትር ኤክስፐርትነት ሲሠራ የቆየ ሲሆን በ1993 ዓ.ም የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በአዋጅ ሲቋቋም  በኲር ጋዜጣ ላይ ተመድቦ  ላለፉት 23 ዓመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ረዥም ጊዜያትን አሳልፏል:: ጋዜጠኛነት እና የቲያትር እና ሥነ ጽሑፍ ባለሙያነት ተቀራራቢ ናቸው ብሎ የሚያምነው ታምራት የጋዜጠኝነት ሥራውን በጀመረበት አካባቢ በሙያው ብዙም ላለመፈተኑ ምክንያቱ የቲያትር እና ሥነ ጽሑፍ ተማሪ መሆኑ ነው ብሎ ያምናል::

በአሁኑ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን  ውስጥ የበኲር ጋዜጣ አዘጋጅ ሆኖ ጋዜጠኝነትን የጀመረው ታምራት በዚያው በበኲር ጋዜጣ ላይ አትሮንስ እና ዐውደ ባህል የሚባሉ አምዶች አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል:: አንኳር፣ ፍትህ እና አስተዳደር፣ አስኳል፣ ዐውደ ባህል፣ አትሮንስ እና ሌሎችም አምዶች የነበሯት በኲር ጋዜጣ በ16 ገፆች ለሕትመት ትበቃ እንደነበረም ታምራት ያስታውሳል::

አትሮንስ የተባለው አምድ ላይ በሀገራችን እና በዓለም ላይ የተከሰቱ ድንቃ ድንቅ ነገሮች የሚቀርቡ ሲሆን የወቅቱ የአምዱ አዘጋጅ ደግሞ ታምራት ሲሳይ ነበር:: አሁን በኲር ጋዜጣ በገጽ ብዛት፣ በአምዶች ብዛት እና በሥርጭት ትልቅ ደረጃ ላይ በደረሰችበት ወቅት “አግራሞት” የተሰኘውን የዓለም ድንቅ ድንቅ መረጃዎች በማዘጋጀት ላይ የሚገኘውም ታምራት ሲሳይ ነው:: ታምራት ከአግራሞት በተጨማሪም በተለያዩ የጋዜጣዋ አምዶች ላይ አንጋፋ የብዕር አሻራውን እያሳረፈም ይገኛል::

ታምራት ሲሳይ  የፕሬስ ዘርፉ አስተባባሪ ሆኖም ሠርቷል:: በአማራ ሬዲዮ የመምሪያ ኃላፊ፣ የአማራ መገናኛ ብዙኃን (በቀድሞ ስሙ) የፕሮሞሽን እና ገበያ ልማት የሥራ ሂደት ኃላፊ ሆኖም ሠርቷል::  ከእነዚህ የኃላፊነት ሥራዎቹ በኋላ ባጋጠመው እክል ምክንያት ከትላልቅ የኃላፊነት ቦታዎች ቢነሳም በአሚኮ ቋንቋዎች የሥራ ሂደት የኦሮሞኛ አስተባባሪ ሆኖም ሠርቷል::

ታምራት ሀረር በማደጉ ምክንያት የኦሮምኛ እና አማርኛ ቋንቋዎችን በተገቢው መልኩ መናገር ይችላል:: “በኦሮምኛ ክፍል እስካሁንም ድረስ የኦሮምኛ ፕሮግራም ማስጀመሪያ የሆነው ድምጽ የኔ ነው” የሚለው ታምራት የቋንቋ ብዝሀነት ሀገርን በብዙ መልኩ እንደሚጠቅምም ገልፆልናል:: አሁን ላይ በበኲር ጋዜጣ የአግራሞት እና ሌሎች አምድ አዘጋጅ ሆኖ እየሠራ የሚገኘው ታምራት የአማርኛ፣ የኦሮምኛ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታዎቹ ለጋዜጠኝነት ሙያው ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸውም ነው የሚናገረው::

“የቋንቋ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነገሮች ብዝሀነት ለሀገራችን ይጠቅማታል” የሚለው ታምራት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በርካታ ቋንቋዎችን እንደ ሀብት በመውሰድ በአግባቡ መጠቀም ሲገባን፣ ቋንቋን ለብሔር እና ለማንነት መከፋፊያ ማድረግ ግን ትልቅ ስህተት ነው ይለናል:: “እኔ ሀረር ውስጥ ተወልጄ በማደጌ የኦሮምኛ ቋንቋን በደንብ አውቄያለሁ፤ የኦሮምኛ ቋንቋን በማወቄ ደግሞ በኦሮምኛ ቋንቋ የሚተላለፉ የተለያዩ ፕሮግራሞችን እንድከታተል እና መረጃዎችን እንዳገኝ አገዘኝ እንጂ ቋንቋውን በማወቄ ያጣሁት ነገር የለም” ብሎናል::

“የኔ ቋንቋ የተሻለው ነው ወይም ያንተ ቋንቋ ከእኔ ያነሰ ነው የሚሉ አስተሳሰቦች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዙ ብሔሮች እና ቋንቋዎች ባሉባት ሀገር ውስጥ ብዙ እርምጃ ወደፊት አያስጉዙንም” ያለን ጋዜጠኛ ታምራት ሁሉንም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቋንቋዎች የሁላችንም ሀብት አድርገን ብንወሰዳቸው እንጠቀማለን እንጂ አንጐዳም የሚል ሀሳቡንም አጋርቶናል::

አሚኮ በተለያዩ ቋንቋዎች ፕሮግራሞቹን በማሠራጨቱ የብዙዎች አገልጋይ እንደሚሆነው ሁሉ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችም አሚኮን የእነሱ ድምጽ መስሚያ አድርገው ስለሚወስዱት አሚኮ በብዙ ያተርፋል የሚለው ታምራት በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘፈኑ ዘፈኖች እና የተፃፉ መጽሐፎችን ማዳመጥ እና ማንበብ የተለመደው ከእኛ ውጪ ከሆኑ ቋንቋዎችም ጥሩ መረጃዎችን ስለምናገኝ ነው፤ በማለት የብዝሀነትን ጥቅም አብራርቷል::

ታምራት እና የታምራት ክፍል ጋዜጠኞች በአንድ ወቅት የሥራ ግምገማ እያካሄዱ ነው:: የመገምገም ተራው የታምራት ሲሆን አንድ የሥራ ኃላፊ ታምራትን እንዲህ በማለት ገመገሙት:: “ታምራት ሲናገር ድምጹ የክፍሉን ሠራተኞች የሚረብሽ ነው” ሲሉ ገመገሙት:: ታምራትም ለኚሁ ገምጋሚ በሰጠው ምላሽ “እኛ የሀረር ልጆች ስንናገር ድምጻችንን ከፍ አድርገን እና በግልጽ ነው:: የድምጼን ከፍ ማለት ደግሞ ባለቤቴም ከእናንተ በፊት ገምግማኛለች” የሚል መልስ ሰጣቸው እና ሁሉም ተሰብሳቢዎች ሳቁ::

እኛም ስለ ባለቤቱ ግምገማ በሰፊው እንዲያጫውተን ጠይቀነው ታምራትም ከፈገግታ ጋር ምላሹን ሰጥቶናል:: “ከላይ እንደገለጽኩት እቤትም ሆነ በቢሮ አካባቢ ሳወራ ድምጼን ከፍ አድርጌ ነው፤ በዚህም ምክንያት ባለቤቴ ብዙ ቀን ለምን ትጮሀለህ ብላ ትጠይቀኝ ነበር፤ እኔም ለባለቤቴ የምሠጣት ምላሽ ድምጼ ያስተዳደጌ ነጸ ብራቅ መሆኑን ብቻ ነው:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ታናሽ ወንድሜ ከሀረር እኔ ጋር ባሕር ዳር መጥቶ ሲጠይቀኝ፣ በእንግድነቱ ሳይጨነቅ ድምጹን ጎላ አድርጎ ሲያወራ የሰማችው ባለቤቴ አነጋገራችን የእውነትም ከአስተዳደጋችን የመጣ እንደሆነ ተገንዝባለች፤ ለዚያም ነው በድምጼ ጉዳይ ባለቤቴም ገምግማኛለች የምለው” በማለት እንደ ሀረር ተወላጅነቱ ነገሮችን በግልጽ ማስረዳቱን አጫውቶናል::

ሙያቸውን የሚወዱ ወጣት ጋዜጠኞች ለሙያቸው መሥራት ያለባቸው በወጣትነታቸው ነው:: እኔ ወጣት ጋዜጠኛ በነበርኩበት ወቅት በአማራ ክልል ባሉ አብዛኞቹ ዞኖች እና ወረዳዎች ተንቀሳቅሼ ሠርቻለሁ:: በዚያ ወቅት ያገኘሁትን እውቀት እና የአማራ ክልልን ሁለንተናዊ ገጽታ የተረዳሁበትን አጋጣሚ አሁን መልሼ ላገኘው አልችልም:: ወጣት ጋዜጠኞች ብዙ ነገር ማወቅ፣ መሥራት እና በሕዝብ ዘንድ በሥራቸው ታዋቂ መሆን ያለባቸው በወጣትነታቸው ጊዜ ነው:: ‘ወጣት የነብር ጣት’ የሚለውን ብሂል እውን ማድረግ ያለባቸውም በወጣትነታቸው ወቅት ነው::

“በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ የቡድን ሥራ በጣም ወሳኙ ጉዳይ ነው፤ የአንድ ጋዜጠኛ ስህተት የተቋሙ ስህተት ተደርጐ ስለሚወሰድ ሙያው በጋራ መቆምን የግድ ይላል” ያለው አንጋፋው ጋዜጠኛ ታምራት ሲሳይ ለአብነት በበኲር ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ በምስራቅ አፍሪካ የምትገኝን አንዲት ሀገር በምስራቅ ኤዢያ እንደምትገኝ አድርጐ በማውጣቱ በአንድ ሌላ ትልቅ የሀገሪቱ ጋዜጣ ላይ “አዲዮስ ጂኦግራፊ” በማለት የጋዜጠኛውን ስህተት በመጠቆም ተሳልቆብናል::

ከላይ እንደገለጽኩት ዓይነት ያሉ የጋዜጠኞች ስህተቶች የጋዜጠኞቹ ናቸው ተብለው ብቻ የሚናቁ አይደሉም፤ ስህተቶቹ አነስተኛም ይሁኑ ትልቅ፣ ስህተቱ የተቋሙ ስህተት እንደሆነ ተደርጐ ነው የሚወሰደው:: የጋዜጠኛነት ሙያ የቡድን ሥራን አጥብቆ ይፈልጋል የሚባለውም የአንዱን ስህተት ሌላኛው ማረም ስላለበት እና ስለሚገባው ነው:: በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ አሽከርካሪው፣ ስምሪት ሰጪው፣ ጋዜጠኛው የካሜራ ባለሙያው እና ሌሎችም በአንድ ልብ ተቀናጅተው ካልሰሩ በቀር ሥራቸው ስህተት ባይኖርበት እንኳን አድማጭ እና ተመልካችን የሚማርኩ ሊሆኑ አይችሉም በማለት ሀሳቡን አጋርቶናል፤ አንጋፋው ጋዜጠኛ ታምራት ሲሳይ::

 

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here