አቦከር የወጣቶች ማህበር በሀረር ከተማ ከሚገኙ የወጣች በጎ ፍቃድ አንዱ ነው:: ማህበሩ ከ200 በላይ ወጣቶችን በአባልነት ያሳትፋል:: የ2017 ዓ.ም የክረምት ወራት ሀገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ እና የዕውቅና መርሐ ግብር “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት ጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደበት ወቅት በሁለገብ ተሳትፎ ተሸላሚ ከነበሩት በጎ ፈቃደኛ ማህበራት አንዱ ነው።
የማህበሩ አባል ገመቹ አበራ እንደሚገልፀው ማህበሩ አረጋዊያንን በቤት እድሳት እና በሌሎች ልዩ ልዩ ጉዳዮች በማገዝ፣ በመንገድ ደህንነት /ትራፊክ/ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም ለሌሎች አቻ ወጣቶች የኪነ ጥበብ ስልጠና እና የሥራ ዕድል በመፍጠር ባደረገው አስተዋፅኦ እውቅና እና የ150 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል:: የበጎ ፍቃድ ሥራ ለምስጋና ሳይሆን የአዕምሮ ርካታ የሚሠራ መሆኑን ያነሳው ገመቹ፤ አሁን ላይ ደግሞ ማህበራዊ ተሳትፎው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁሟል::
ከጋምቤላ ክልል የመጣው እና የሴንተር ፎር ዩዝ ራይት ኢምፓወርመንት ወጣት በጎ ፍቃደኞች ማህበር አባል ዳዊት ኀይሉ በበኩሉ የማህበሩ አባላት በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥር በከተማ ጽዳት፣ በማዕድ ማጋራት እና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ተግባር በክረምት ወቅት ይሳተፋል:: በተለይ ደግሞ ወጣቱ ወደ ቴክኖሎጂ ቅርበት እንዲኖረው ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በተሰጣቸው ሥልጠና ለሽልማት እንደበቃ ተናግሯል:: እንደ ክልል ጠቅለል ባለ ተግባራቸው አሸናፊ የሆኑትን ሲመለከቱ ደግሞ በቀጣይ እንደ ማህበር ሳይሆን እንደ ክልል አካባቢያቸውን ለማስጠራት በትጋት እንዲሠሩ እንደፈጠረለት ተናግሯል::
መስፍን አበጀ (ዶ/ር)የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የብልፅግና ፓርቲ ዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ናቸው:: እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ክልሉ በበጎ ፈቃድ ማህበራዊ አገልግሎት በሁሉም ዘርፍ ተደራሽ በመሆን በተለይ ለአቅመ ደካማ ዜጎች ቤት በመሥራት እና በማደስ እውቅና እና ሽልማት አግኝቷል:: ክልሉ በፀጥታ ችግር ውስጥ ሆኖም የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን በከፍተኛ ሁኔታ መፈፀም መቻሉም ሌላው ለሽልማት ያበቃው ጉዳይ ነው:: ሁሉንም አቅም በማስተባበር የበጎ ፍቃድ ተግባርን ከክረምት ባለፈ በበጋም በመቀጠል ባህል ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ዘርፍ ኃላፊው ተናግረዋል::
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እንዳሉት በጎ ፈቃድ የመንፈስ ርካታ ለማግኘት ሰዎች በፈቃደኝነት የሚሰጡት አገልግሎት ነው። ዜጎች በተለይም ወጣቶች ክህሎት እና ልህቀታቸውን ከማጎልበት ባሻገር ሰብዓዊነት የሚያጎለብቱበት አገልግሎት መሆኑንም ገልጸዋል።
ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ ብዙ ተግዳሮቶች እየገጠማት ቢሆንም የመጀመሪያ ደራሾች በጎ ፍቃደኞች እንደሆኑ ያነሱት ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)፤ በሀገራችንም የልማት ክፍተቶችን በመሙላት እና የማኅበረሰቡን መልካም እሴት በማጠናከር የአቅመ ደካሞችን ችግር እየፈታ ነው::
በአማራ ክልል በ2017 ዓ.ም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ከ656 ሺህ በላይ ወጣቶች መሳተፋቸውን ያነሱት ሙሉነሽ (ዶ/ር) በዚህም ከ13 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግም ተችሏል። በዚህም በተሠጠው አገልግሎት ከ7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ የመንግሥትን ወጭን መታደግ መቻሉን ነው ያብራሩት።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒሥትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው የበጎ ፈቃድ ሥራ የወጣቶች እና ሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ ነው። በተለይም ደግሞ በመንግሥት እና በማኅበረሰቡ ያልተሸፈኑ የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት በጎ ፍቃድ የማይተካ ሚና አለው።
በጎ ፈቃድ የወጣቶች የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲጠናከር እና የማኅበረሰቡን ጠቃሚ እሴቶች እንዲቀስሙ አድርጓል ብለዋል። ወደ ፊትም የበጎ ፈቃድ ሥራው ቀጣይነት እንዲኖረው እና ባሕል ሆኖ እንዲቀጥል የአሠራር ማዕቀፍ በመቅረጽ እየተሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በ14 አይነት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሠራ የቆየው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሀገር ደረጃ ከ35 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን በሥራው ላይ ያሳተፈ እንደ ነበር እንስተዋል:: በዚህም 53 ሚሊዮን የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የገለጹት ሚኒሥትሯ፤ ከ86 ቢሊዮን ብር በላይ የመንግሥት እና የሕዝብ ሃብትን ማዳን መቻሉን ነው የተናገሩት።
የ2017 ዓ.ም የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ ቆይቶ ነው በባሕር ዳር ከተማ ለተሳታፊዎች እውቅና በመሥጠት የተጠቃለለው:: በ2018 በጀት ዓመትም በበጋው ወራት በክረምት የተጀመሩ ተግባራት እንደሚቀጥሉ በማጠቃለያ መርሀግብሩ ተገልጿል::
ለዛ
- “በመጨረሻም፤ የምታደርገው ነገር ሁሉ ባንተ እና በፈጠረህ አምላክ መካከል ነው። በየትኛውም ጊዜ በአንተ እና በሌሎች መካከል አልነበረም።”
ማዘር ቴሬዛ
- “ሥራ ፈትነት እና ሥራ አጥነት እርኩሰት እና ጤና ማጣት ያስከትላል፤ በተቃራኒው ፣የአዕምሮ ምኞት ወደ አንድ ነገር ለመድረስ መመኘት ደስታን
ያመጣል ፣ ሁል ጊዜ ወደ ሕይወት መሻሻል ይመራል።” ሂፖክራተስ
- “መኖር ማለት የሰውነትን ቁሳዊ ፍላጎት ማርካት ብቻ ሳይሆን በዋናነትም የሰውን ክብር ማወቅ ማለት ነው።” ጄ በርን
- “ሰዎች ህይወት አንድ ናት ይላሉ፡፡ አዎ እኔ ያም አንዱ ነገር ማንበብ ነው እላለው፡፡ ” አንቶኒ በርገሳ
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


