ተወዳጁ የእግር ኳስ ስፖርት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጽንፍ በረገጡ ዘረኞች ምክንያት ውበቱ እየደበዘዘ እና የቆዳ ቀለማቸው ጥቁር የሆኑ ተጫዋቾች የሚሳቀቁበት መድረክ እየሆነ መጥቷል። በእግር ኳስ ውስጥ ያለው ዘረኝነት በክለቦች፣ በተጫዋቾች እና በደጋፊዎች ቢወገዝም በተፈለገው ልክ ግን ሊቀንስ አልቻለም።
አሁን ላይ የማህበራዊ ሚዲያ መበራከት እና ተጠቃሚ መብዛት ደግሞ ጥቃቱ መልኩን እንዲቀይር አድርጎታል። በአውሮፓ አምስቱ ታላላቅ ሊጎች ከ140 በላይ አፍሪካውያን ተጫዋቾች እየተጫወቱ መሆኑን በቅርቡ የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
በርካታ አፍሪካውያን እና የዘር ሀረጋቸው ከአህጉራችን የሚመዘዝ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ለክለባቸው እና ለአሳደጋቸው የአውሮፓ ሀገር ብሄራዊ ቡድን ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ዘረኝነትን በደማቸው ያሰረጹ አውሮፓውያን የእግር ኳስ ደጋፊዎች ለአፍሪካውያን ተጫዋቾች በቆዳ ቀለማቸው እና በማንነታቸው ምክንያት ጭፍን ጥላቻ አላቸው።
በቅርቡም የበርንሌው አማካይ ሀኒባል መጅበሪ ክለቡ ከፕሪስተን ኖርዝ ኢንድ ጋር በነበረው ጨዋታ የዘረኝነት ጥቃት እንደደረሰበት የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል። አዲሱ የፈረንጆች ዓመት ከገባ ጀምሮ በኒውካስትሉ ተጫዋች ጆ ዊሎክ ላይም የዘረኝነት ጥቃት ደርሷል። እነዚህን ለአብነት አነሳን እንጂ በሌሎች የአውሮፓ ሊጎች የቆዳ ቀለም እና ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ተፈጽሟል፤ እየተፈጸመ ነው።
ከባለፉት ዓመታት አንጻር ሲታይ ግን በዚህ ዓመት በተጫዋቾች ላይ የሚፈጸመው የዘረኝነት ጥቃት ቀንሷል። የፀረ ዘረኝነት ተቋሙ ኪክ ኢት አውት (Kick it out) ባጠናው መሰረት በእንግሊዝ እግር ኳስ ብቻ ባሳለፍነው ዓመት አንድ ሺህ 332 ጥቃቶች መድረሳቸውን አረጋግጧል። 52 በመቶው ስቴዲየም ውስጥ የተፈጸመ ነው።
በእነዚህ ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥ እንደ ዝንጀሮ እና ጦጣ ተጩሆባቸዋል፤ የሙዝ ልጣጭ ተወርውሮባቸዋል፤ እጃችሁን አንጨብጥም ተብለዋል፤ ተሰድበዋል፤ ተንቋሸዋልም። ቀሪው 48 በመቶ ደግሞ በማህበራዊ የትስስር ገጽ እንደሆነ መረጃው አመልክቷል። በማህበራዊ የትስስር ገጽ የሚደርሰው የዘረኝነት ጥቃት ተጫዋቾችን በማንነታቸው እና በቆዳ ቀለማቸው ከማሳቀቅ ጀምሮ ዛቻ እና ማስፈራሪያንም ይጨምራል።
ምንም እንኳ ተደጋጋሚ መሰል በደሎች በተጫዋቾች ላይ ቢደርስም ችግሩን ለመቅረፍ የተሰሩ ሥራዎች እና ጥናቶች ግን በቂ አለመሆኑን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። ጥቃቱ የሚደርስባቸው ተጫዋቾች ለስነ ልቦና ጭንቀት፣ ለፍርሃት፣ ለብስጭት፣ ለሀዘን እና ድካም ይዳርጋቸዋል። ችግሩ ሲጸናም ለዘርፉ ማበርከት ያለባቸውን አስተዋጽኦ ሳያበረክቱ ከሚወዱት እግር ኳስ ለመገለል ይገደዳሉ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብራዚላዊውን ባለተሰጥኦ ቪኒሺየስ ጁኒየር ያህል የዘረኝነት ጥቃት የደረሰበት ተጫዋች የለም። ብራዚላዊው ኮከብ በ21 የተለያዩ አጋጣሚዎች በቆዳ ቀለሙ እና ማንነቱ ጥቃት ተሰንዝሮበታል። እንደ ጣሊያን ሴሪ ኤ ግን ዘረኝነት በደማቸው ሰርጾ ባሰከራቸው ደጋፊዎች የተሞላ ሊግ የለም።
እንደ ፍራንስ 24 መረጃ የጣሊያን ሴሪ ኤ ከሌሎች ሊጎች የበለጠ ዘረኛ ደጋፊዎች በጥቁር አፍሪካውያን እና ላቲን አሜሪካውያን ተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ ጥቃት አድርሰዋል፤ እያደረሱም ነው።
ከጣሊያን ቀጥሎ ስፔን የዘረኛ እግር ኳስ ደጋፊዎች መኖሪያ መሆኗን መረጃው ይነግረናል። ከጣሊያን እና ስፔን ሊግ ቀጥሎ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾችን በቆዳ ቀለማቸው እና ማንነታቸው ጥቃት የሚያደርሱ ደጋፊዎች ያሉበት ምድር ነው።
ከስፔን፣ ከጣሊያን እና እንግሊዝ በተሻለ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው ተጫዋቾች የሚከበሩበት ነበር- የፈርንሳይ ሊግ አንድ። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየስቴዲየሙ ጥግ ዘረኛ ደጋፊዎች ተበራክተዋል። ከሁለት ዓመታት በፊት የሊዮን ደጋፊዎች በኦሎምፒክ ማርሴ ተጫዋቾች ላይ የናዚ ምልክት ሰላምታ በመስጠት እና በመጮህ ጥቃት ማድረሳቸው የሚታወስ ነው።
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ አሁን ላይ ስቴዲየም ውስጥ የሚፈጸመው ዘረኝነት ጥቃት ቢቀንስም በተለያዩ የማህበራዊ የትስስር ገጾች የሚደርሰው ጥቃት ግን አልቀነሰም። እ.አ.አ በ2023 የባቫሪያኑ ክለብ ባየርሙኒክ እንዳስታወቀው ዳዮት አፕሜካኖ እና ማቲስ ቴል ደካማ አቋም አሳይተዋል በሚል በማህበራዊ የትስስር ገጽ ተሰድበዋል፤ ተንቋሸዋል።
በእግር ኳስ ስፖርት መላው ዓለምን አንገት ያስደፋ የዘረኝነት ጥቃት በተለያዩ አጋጣሚዎች ተከስተዋል። ከእነዚህ መካከል እ.አ.አ በ2005 በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ከሪያል ዛራጎዛ በነበረው ጨዋታ በካሜሮናዊው የቀድሞው ግብ አነፍናፊ ሳሙኤል ኤቶ ላይ የዘረኝነት ጥቃት ደርሶበታል።
ዘረኝነት ያሰከራቸው የሪያል ዛራጎዛ ደጋፊዎች ሳሙኤል ኤቶ ኳስ ሲይዝ እንደ ዝንጀሮ እና ጦጣ በመጮህ ለማሳቀቅ ሞክረዋል። የመሀል ዳኛው ጨዋታውን በማስቆም የተሰባበሩ ጠርሙሶችን እየወረወሩ እንደ ዝንጀሮ የሚጮሁትን የዛራጎዛ ደጋፊዎች ከድርጊታቸው ሊያስቆም ቢሞክርም አልተሳካም። ሳሙኤል ኤቶ እና የቡድን አጋሮቹም ሜዳውን ለቀው ለመውጣት ጫፍ ደርሰው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ድጋሚ ጨዋታው እንደ ተጀመረ አፍሪካዊው የቀድሞው ኮከብ ሳሙኤል ኤቶ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር እና እንደ ዝንጀሮ በመጨፈር ደስታውን በመግለጽ አጻፋውን መልሷል። ጨዋታውም በባርሴሎና አራት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ማሪዮ ባሎተሊ ጣሊያን ውስጥ ነው ከጋናውያን ስደተኛ ቤተሰቦች የተወለደው። ይሁን እንጂ ጣሊያናውያን ዘረኞች ለባለተሰጥኦው አጥቂ አልራሩለትም። እንደ ባሎተሊ በተደጋጋሚ የዘረኝነት ጥቃት የደረሰበት ተጫዋች የለም። በተጫወተባቸው ሊጎች ሁሉ በፈረንሳይ ሊግ አንድ፣ በጣሊያን ሴሪ ኤ እና በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጥላቻ ባደረባቸው ደጋፊዎች ተበድሏል።
ብሄራዊ ቡድናቸውን የወከለላቸው ደጋፊዎች ሳይቀር ጥላቻቸውን ሜዳ ውስጥ አሳይተውታል። በተጨማሪም የስፔን እና ክሮሺያ ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎችም የዘረኝነት ጥቃት እንዳደረሱበት የፍራንስ 24 መረጃ አመልክቷል። ማሪዮ ባሎተሊ ጥቃቱን መቋቋም ተስኖት በተደጋጋሚ ስቴዲየሙን ለቆ ለመውጣት ብዙ መኩራ አድርጓል። ይህ ዐይነቱ ድርጊት የመረረው ባሎተሊ በእንግሊዙ ክለብ ማንቸስተር ሲቲ ቤት ግብ ካስቆጠረ በኋላ እስከ አሁን ድረስ የእርሱ መለያ የሆነውን “ለምን እኔን ብቻ!” (“whay always me!”) የሚል ጽሁፍ ማስነበቡ አይዘነጋም።
እ.አ.አ በ2014 ባርሴሎና ቪያሪያልን ሦስት ለሁለት ባሸነፈበት ጨዋታ ዘረኝነት ያሰከራቸው የቪያሪያል ደጋፊዎች በብራዚላዊው የቀድሞ ተከላካይ ዳኒ አልቬዝ ላይ ጥቃት አድርሰዋል። ተጫዋቹ የማዕዘን ምት ሊመታ ወደ መስመሩ በወጣበት ቅጽበት ሙዝ በመወርወር እንደ ዝንጅሮ ጮኸውበታል። ዳኒ አልቬዝ ግን የተወረወረውን ሙዝ አንስቶ በመብላት ለዘረኞች በቀላሉ የማይሰበር መሆኑን አሳይቷል።
ጥቂት ዘረኛ አውሮፓውያን የእግር ኳስ ደጋፎዎች የዘር ሀረጋቸው ከአፍሪካ የሚመዘዙትን ተጫዋቾች ሜዳ ላይ አንያችሁ ቢሉም ካለ አፍሪካውያን ኮከቦች ደግሞ አይሳካላቸውም። ለአብነት እ.አ.አ በ1998 ፈረንሳይ የዓለም ዋንጫን ስታነሳ በስብስቡ ከነበሩ 25 ተጫዋቾች መካከል 14ቱ የዘር ግንዳቸው የሚመዘዘው ከአህጉራችን ነው። ከ20 ዓመት በኋላ በ2018 እ.አ.አ ድጋሚ የዓለም ዋንጫን ስታሳካ ከ23ቱ የተጫዋቾች ስብስብ 12ቱ ተጫዋቾች ከአፍሪካውያን ስደተኞች የተወለዱ ናቸው።
የዓለም የእግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ (ፊፋ) ዘረኝነትን ለመከላከል በተለያዩ የእግር ኳስ መድረኮች የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ከጀመረ ሰንባብቷል። በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከመጀመራቸው በፊት በአንድ እግራቸው በመንበርከክ ዘረኝነትን ሲያወግዙ መመልከት እንግዳ አይደለም። በሁሉም የአውሮፓ ሊጎች ጥቃቱን በሚያደርሱ ደጋፊዎች፣ ተጫዋቾች እና የክለብ ኃላፊዎች እርምጃ እየተወሰዱ ቢሆንም ቅጣቱ አስተማሪ እና ከባድ ባለመሆኑ ተወዳጁ እግር ኳስ ከዘረኝነት ሊጸዳ አልቻለም።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም