በጦርነት የምትታመሰዉ ሱዳን 

0
108

በየዓመቱ ዓለምአቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ (International Rescue Committee) ለከፋ ሰብአዊ ቀውሶች ተጋላጭ የሆኑትን ሀገራት ይለያል። ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመትም ሱዳን በአሳዛኝ ሁኔታ ከዝርዝሩ አንደኛ ሆናለች። በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰው አረመኔያዊ ጦርነት ምክንያት የሀገሪቱ ውድቀት እየተፋጠነ ነው።

የሱዳን መንግሥት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ለፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (RSF) የጦር መሣሪያ ማቅረቡን እንዲያቆም እና ቡድኑን “አሸባሪ ድርጅት” ተብሎ እንዲሰይም በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል።

ሱዳን ይህን ጥያቄ ያቀረበችው የሱዳን የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ አምባሳደር አል-ዘይን ኢብራሂም ሁሴን በኢትዮጵያ አዲስ አበባ በሚገኘው የሱዳን ኤምባሲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

አምባሳደሩ “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ በሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ ኤል-ፋሸር እንዲሁም በሌሎች ከተሞች እና መንደሮች ጭካኔ እንዲፈጽም ፈቅዷል” ሲሉ መክሰሳቸውን ሱዳን ትሪቡን ላይ ያገኘነው መረጃ ያትታል::

የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እ.አ.አ ሚያዚያ 15 ቀን 2023 ነበር የተጀመረው። ይህ ጦርነት የተጀመረው በሀገሪቱ መንግሥት ወታደራዊ ኃይል (Sudanese Armed Forces–SAF) እና በሀገሪቱ ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይል (Rapid Support Forces – RSF) መካከል በተነሳ የስልጣን ሽኩቻ ነበር። ሁለቱ ኃይሎች ቀደም ሲል እ.አ.አ በ2019  ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል-በሺር ከተወገዱ በኋላ አብረው ይሠሩ ነበር።

የሱዳን ጦር አዛዥ ጀኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ አዛዥ ጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጎሎ (ሄሚቲ) የተጋጩበት ዋናው መንስኤ ሁለቱ ወታደራዊ ኃይሎች እንዲዋሃዱ እና አንድ የጦር አዛዥ እንዲኖር በሚለው ላይ መግባባት ላይ መድረስ ባለመቻላቻው ነበር።  እንዲሁም ሱዳን ውስጥ ብዙ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች መኖራቸው እና   የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ግጭቱ እንዲባባስ ማድረጉን አናዶሉ ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል::

ከዳርፉር ጃንጃዊድ ሚሊሻዎች የተወለደው የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ (RSF) ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ በመሆን ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ የኃይል ማዕከልን በእጁ ጨብጧል። አባላቱ  ሰፊ ሕገ-ወጥ ግድያ፣ ፆታዊ ጥቃት እና የዜጎችን ንብረት ማውደማቸውን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አስታውቀዋል።

የጃንጃዊድ ሚሊሻ በምዕራባዊ የዳርፉር ግዛት በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር በ2000ዎቹ መጀመሪያ በሱዳን መንግሥት ተቋቁሞ አማጺያንን ሲዋጋ የነበረ  የታጣቂ ስብስብ ነው። አብዛኛዎቹ ተዋጊዎቹም በዳርፉር ከሚገኙ ጎሳዎች የተመለመሉ ናቸው። አሁን ካለው ጦርነት በፊት ተንታኞች የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ በዳርፉር እና በሌሎች ክልሎች የተሰማሩ 100 ሺህ የሚጠጉ ተዋጊዎች እንደነበሩት ይገምታሉ።

ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት በሱዳን 15 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር:: በወቅቱ ደግሞ ሀገሪቱ  ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ አጋጥሟት ነበር።

ከሁለት ዓመታት በላይ በዘለቀው በአሁኑ ጦርነትም እነዚህ ሁኔታዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሰዋል:: በአሁኑ ጊዜ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሱዳናዊያን ተፈናቅለዋል፣ ከ30 ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች (ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሱዳን ሕዝብ) ደገሞ የሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።

ሱዳን ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ዕድገቷ ወደታች አሽቆልቁሏል። ንጹሃን ለተደጋጋሚ ጥቃቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጋልጠዋል:: እየተጋለጡም ነው። የሀገሪቱ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ወድቋል:: በሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ሠራተኞች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት የሕይወት አድን እርዳታዎችን በግጭቱ ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች ለማድረስ አስቸጋሪ አድርጎታል።

ሮይተርስ እንደዘገበው የግጭቱን ጫና  የተሸከሙት ንጹሃን ጾታዊ ጥቃት በስፋት እየተፈጸመባቸው ነው:: የሁለቱም ወገኖች ተዋጊዎች ንጹሃንን እና የመሠረተ ልማት አውታሮችን አዘውትረው ዒላማ አድርገዋል:: የሕጻናት ወታደር ምልመላ የተለመደ ሆኗል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በዳርፉር የሚገኙ ተዋጊዎችን ድርጊት የዘር ማፅዳት ሲሉም ኮንነውታል።

ቢቢሲ ከሰሞኑ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በዚህ ጦርነት ከ150ሺህ በላይ  ሰዎች ተገድለዋል:: በሰላማዊ ሰዎች ላይ ኢ-ፍትሃዊ ጥቃት እየተፈፀመ ነው። የውጭ ኃይሎች ዲፕሎማሲውን ከማራመድ ይልቅ የጦር መሣሪያ ለአጋሮቻቸው በማቀበል ግጭቱን እያባባሱ ይገኛሉ። በስልጣን ይገባኛል ምክንያት ወደ ጦርነት ያመሩት የሱዳን ጦር አዛዥ አብዱል ፈታህ አል-ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሹ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ አዛዥ መሀመድ ሀማዳን ዳጎሎ ሱዳንን እና ሱዳናዊያንን ወደ አስከፊ የሰብአዊ ውድቀት አስገብተዋቸዋል::

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው በዳርፉር ውስጥ ፍላጎቶች በጣም አሳሳቢ ሆነዋል:: የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ በፈጸመው ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች የግዛቱን ትልቁ ከተማ ኤል ፋሸርን በመሸሽ ወደ 400 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች በአጎራባች ታዊላ ውስጥ የደኅንነት እና የሰብዓዊ አገልግሎቶችን በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

ግጭትን ሸሽተው የሚሰደዱ የሱዳን ስደተኞችን በሚቀበሉ ሀገራት የሚገኙ የረድኤት ድርጅቶች አስቸኳይ ሰብአዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚያስችል ግብአት የላቸውም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ የእርዳታ ቅነሳ ቀውሱን በማባባስ የእርዳታ ሠራተኞች ለስደተኞች አስፈላጊ አገልግሎቶችን እንዲቀንሱ አስገድዷቸዋል።

ጦርነቱ እና በየቦታው ያለው ብጥብጥ የሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማቅረብ ከባድ እንቅፋት በመሆኑ ረሃብ በመላው ሱዳን እየተስፋፋ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የምግብ ዋጋ መናር እና የምግብ አቅርቦት መውደቅ የዜጎችን ረሃብ አባብሶታል።

እ.አ.አ. በታኅሳስ 2024 እና በግንቦት 2025 መካከል በሱዳን ከ24 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት አጋጥሟቸዋል። በሀገሪቱ ጊዜያዊ መጠላያ ውስጥ የሚኖሩ ከ635 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ የረሃብ አደጋ አንዣቦባቸዋል። የመሞት እድላቸውም ከፍተኛ ነው ተብሏል። አስከፊው የምግብ እጥረት ሰዎች   ለበሽታ ተጋላጭ እንዲሆኑም እያደረገ ነው።

በሱዳን ያለው ጦርነት የጤና ሥርዓቱን ጨምሮ የሀገሪቱን የሕዝብ መሠረተ ልማት አውድሟል። ብሉምበርግ እንዳስነበበው ከ70 በመቶ በላይ የሱዳን ሆስፒታሎች ወድመዋል:: ይህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አስፈላጊ የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኙ አድርጓል። የጤና አገልግሎት ተደራሽነት በጣም ውስን በመሆኑ የኮሌራ ወረርሽኝ በሱዳን ተስፋፍቷል:: በዚህም ከ120 ሺህ በላይ ሰዎች ሲታመሙ  ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል።

ጦርነቱ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይም ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። የወሳኝ ጤና አጠባበቅ አገልግሎቶች አለመኖር ነፍሰጡር እናቶች ሕይወታቸውን ከባድ ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል::

በተመሳሳይ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እየተባባሱ ነው። የቅርብ አጋሮች ጾታዊ ጥቃት፣   የጉልበት ብዝበዛ በደል እና ሕገ -ወጥ የሰዎች ዝውውር ሪፖርቶች ተስፋፍተዋል:: የተረፉት ደግሞ ድጋፍ ለማግኘት ይቸገራሉ። የምጣኔ ሀብት ችግር ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሴቶች ሕይወታቸውን አስቸጋሪ አድርጎታል::

ከሰሞኑ የመንግሥታቱ ድርጅት እንዳስታወቀው በሱዳን እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት የሱዳናዊያንን መከራ እና ስቃይ እያባባሰው ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃክ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ  ግድያ እና ጾታዊ ጥቃት እንደተፈጸሙ የሚሳዩ ታማኝ ሪፖርቶችን ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

በያላ ዩኒቭርሲቲ ይፋ የተደረገ መረጃ እንደሚጠቁመው የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ በኤል-ፋሽር ከሰሞኑ የፈጸመውን የጅምላ ግድያ ለመሸፈን ሟቾችን በጅምላ እየቀበረ ነው::

ሁለት ዓመታትን የተሻገረው ጦርነቱ የሱዳናዊያንን ሕይወት እየቀጠፈ፣ ሱዳንንም እያወደመ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው።

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የህዳር  1  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here