በፈተና ውስጥ የታለፈ ፈተና

0
248

በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም የዕውቀት ጎዳና ዕትም የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከምስራቅ አማራ ቀጣና የዞን እና የወረዳ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተደርጎ እንደነበር ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ በግምገማው  የክልሉ ትምህር ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ  በትምህርት ዘርፉ ላይ ባሳደረው ተጽኖ በተማሪዎች፣ በመምህራን ፣ በወላጆች እና በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ዘንድ የስነልቦና ጫና እንዳሳደረ እና የተከሰተውን የፀጥታ ችግር በመቋቋም የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል አበረታች ሥራዎች መሠራታቸውንም መግለፃቸውን ዘግቦ ነበር:

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሰሜን ጎጃም እና ባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ የትምህርት አመራሮች ጋር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በገመገመበት ወቅት በከተማ አሥተዳደሩ ከመቶ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁለት የሁለተኛ ደረጃ እና 22 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሥራ ማቆማቸው ተመላክቷል::

በክልሉ ካሉት ትምህርት ቤቶች የፀጥታ ችግር የሌለባቸው እና   በትምህርት ገበታ ላይ ያሉ ፣ ዓመቱን ደግሞ   በጥሩ ውጤት  ያሳለፉ የአንደኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች  ጥሩ ውጤት ማምጣት የቻሉበትን መንገድ እና የጥናት ስልታቸውን በተመለከተ ያላቸውን  ተሞክሮ በዚህ ሳምንት የዕውቀት ጎዳና ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

የመጀመሪያዋ የሽንብጥ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችው ናታኒም አለማየሁ የስድስተኛ “E”(ኢ) ክፍል ተማሪ እና የ13 ዓመት ታዳጊ ናት፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤቱ ስትገባ አዲስ ስለነበር 23 ተኛ ደረጃ ስታገኝ በመቆጨት መምህር ያስተማረውን ነገር በአግባቡ ተከታትሎ በመከለስ የከበዳትን ደግሞ ቤተሰብ በተለይም እንግሊዘኛ መምህር አጎቷን በመጠየቅ ሁለተኛ ክፍልን በአንደኛነት ማጠናቀቋን ትገልፃለች፡፡

ከሁለተኛ ክፍል  በኋላ ባለው ጊዜም እስካሁን ድረስ ባለው የትምህርት ደረጃዋ አንደኛ የሆነችው ናታኒም መምህር ሲያስረዳ በመከታተል ፣ መያዝ ፣ በመጠየቅ እና በቤት ደግሞ ማንበብ ለጥሩ ውጤት አንደሚያበቃ የምትገልፀው ናታኒም በክልሉ ባለው ችግር ምክንያት ትምህት ሲቆም አንኳን ተመልሶ ሲከፈት ላለመቸገር ጊዜዋን በማንበብ ስለምታሳልፍ እንደማትቸገር ነው፡፡

መረዳት ከቻሉ የሚከብድ ነገር የለም ብሎ ማሰብ እንደሚያስፈልግ የምትናገረው ጎበዟ ተማሪ ናታኒም “ሒሳብን ትምህርት ሳጠናው አይገባኝም ብዬ ትቼው 77 ከመቶ ሳመጣ እስኪ ጊዜ ሰጥቼ ላጥናው ብዬ በማንበብ እና በመረዳት ሒሳብን 99 ዘንድሮ ከመቶ ማምጣት ችያለሁ፡፡” ስትል ነው የነገረችን፡፡

ሌላዋ የሽንብጥ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የስድስተኛ “C” (ሲ)ክፍል ተማሪ ረድኤት ሉሌ ደግሞ በትምህርት ጅማሬዋ በቸልተኝነት እንደነበር አስታውሳ ተማሪዎች ጎበዝ ሁነው ውጤት ሲያመጡ ስትመለለከት ግን “እኔስ ይህንን ለማግኘት ምን ያንሰኛል” በሚል የእልህ ስሜት በማንበብ ከሁለተኛ ክፍል ጀምሮ አንደኛ በመውጣት አሁንም የአንደኛነት ውጤቷን አስጠብቃ መሄድ እንደቻለች ነው የምትገልፀው፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ሰላም በመሆኑ አዕምሮን ትኩረት የሚበትን ነገር ስለሌለ ዕድሉ ያጋጠመው ተማሪ አዕምሮውን ሰብስቦ ማጥናት ከቻለ ውጤታማ እንደሚሆን የገለፀችልን ረድኤት ሁሉም ሰው  የራሱ የሆነ የመረዳት አቅም አለው ስለዚህ ለራሱ ውጤታማ የሚያደርገውን መንገድ መምረጥ የተማረውን እስኪረዳ ድረስ ማጥናት እንደሚገባው  ነው የምትገልፀው፡፡

ጎበዞቹ ተማሪዎች ረድኤት እና ባለፈው ዓመት ከ6 እስከ 14 ዓመት ያሉ ወጣቶች የሚሳተፉበት “አባከስ” የሒሳብ ውድድር የተሳተፉ ሲሆን 12 አሸናፊዎች ተመርጠው ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ በዝግጅት ላይ እያሉ ግጭቱ ተከስቶ መሔድ አለመቻላቸውን እና ወደፊት ደግሞ የሕክምና ዶክተር ለመሆን በርትተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የቁልቋል ሜዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው የ14 ዓመቱ ሰለሞን ጌትነት በበኩሉ እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ ትምህርት ቤት ብቻ በደንብ ተከታትሎ ከአንደኛ እስከ አስረኛ  ደረጃ በማግኘት ከክፍል ወደ ክፍል ሲዘዋወር ቢቆይም ስድስተኛ ክፍል ላይ ሲደርስ ግን መምህር ሲያስተምር በዛው በመጠየቅ መረዳት እና በቤቱ ውስጥ ደግሞ የተማረውን በደንብ በማጥናት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ እንዳጠናቀቀ ይገልጻል፡፡ በአሁኑ ዓመት ደግሞ ወደ ስምንተኛ ክፍል ሲያልፍ አንደኛ ደረጃ እንደያዘ የገለፀልን ሰለሞን ግዜን ከጨዋታ ባለፈ ለጥናትም  ሆነ ቤተሰብ ለማገዝ በአግባቡ ከፋፍሎ መጠቀም ውጤታማ እንደሚያደርግ ከሱ ልምድ መመልከት እንደሚቻል ነው፡፡

በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ከማምጣቱ ባሻገር እግር ኳስ በመጫወት ወደ ፊት ትልቅ የእግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን እንደሚጥር የሚገልፀው ሰለሞን ለዚህ ደግሞ ጊዜን ከፋፍሎ በአግባቡ በመጠቀም ቤተሰብን ማሳየት እንደሚገባ በማመኑ በአግባቡ ግዜውን እንደሚጠቀም ነው የሚገልፀው፡፡

ከህልውና ጦርነት በኋላ ባለው ጊዜ ብዙ ተማሪዎች በተለያየ ችግር  ምክንያት እየተማሩ አለመሆኑን ከመገናኛ ብዙኃን መሥማቱንም የገለፀው ሰለሞን እድሉን አግኝተው በትምህርት ገበታ ያሉ ተማሪዎች በመምህር መታገዝ የቻሉበትን ጊዜ እና ትርፍ ሰዓታቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ውጤታማ እንዲሆኑ መትጋት እንዳለባቸው ይመክራል፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here