በ“ፍካሬ” ውስጥ ያሉ እውነቶች

0
142

ሥነ – ጽሑፋዊ ዳሰሳ፡- ታደሰ ጸጋ

ደራሲ፡- ዓለማየሁ ዋሴ (ዶ/ር)

የታተመበት ዓመት፡- 2017 ዓ.ም

የገፅ ብዛት፡-202

የምዕራፍ ብዛት፡- 30

“ፍካሬ” በሰውኛ ዘይቤ የቀረበ የሥነ – ጽሁፍ ሥራ ነው:: ሰውኛ (personification) ዘይቤ ጥበባዊ በሆነ መንገድ ግዑዛን እንደሰው እንዲያስቡ እና አንደበት ኖሯቸው እንዲናገሩ ማድረግ ነው:: ይህ ሁኔታ ዛፎችን እንደሰው ማናገርንም ይጨምራል::

ይህ ዘይቤ በጥንት ግሪክ እና ሮም የብሉይ ተረቶች እንዲሁም ዘመን አይሽሬ ተረኮች መንገሪያ ነው:: አልፎም የዘመናችን በርካታ ጥበባዊ መልክ  የተጐናፀፉ (allegorycal) ተምሳሌታዊ መጻሕፍት እና ከተለመደው የሰው ልጅ አቅም እና ችሎታ በላይ የተጐናጸፉ (Superhero) ፊልሞችም ይጠቀሳሉ::

ከብዙ በጥቂቱ ከሰውኛ፣ ተምሳሌታዊ እና ምፀታዊ የሥነ – ጽሑፍ ሥራዎች መካከል ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በ1945 ዓ.ም የታተመውን የጆርጅ ኦርዌል የእንስሳት ኮሜዲን (Animal farm) በአብነት መጥቀስ እንችላለን:: ይህ መጽሐፍ በሚያነሳው ጭብጥ እና ባጻጻፍ ስልቱ ምጸታዊ እና ተምሳሌታዊ በሆነ ስልት የተጻፈ ሥራ ነው::

የጣሊያናዊው የዳንቴ ኢንፌርኖ (the divine comedy) ከጥንታዊ  ሮም ቅኔዎች መካከል አንዱ ተደርጐ ይቆጠራል:: የአንድ ሰው ነፍስ ከሞት በኋላ በገነት እና በሲኦል የሚኖራትን ቆይታ ነው የሚተርክልን:: መተረኪያው ደግሞ (allegory) ተምሳሌታዊ ነው:: ዳንቴ የዘመኑን ፖለቲካ፣ ፍቅርን፣ ሀይማኖታዊ አመለካከትን ነው በምናብ የሚያስቃኜን::

እንስሳትን በሰዎች ዘይቤ የሚያናግረው ጆርጅ ኦርዌል በእውነተኛ ስሙ ኤሪክ አርተር ብሌየር ዋነኛ ጭብጡ የሩሲያ አብዮት ነው፤ የ1917 የስታሊን ዘመን የሶቪየት ህብረት ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ውጥንቅጥ::

የማርክሲስት ሌኒኒስት ሩሲያ፣ የጆሴፍ ስታሊን ርእዮተ ዓለምን በምፀት የተቸ ነው:: ጥበባዊ በሆነ መንገድ የተፃፈ የፖለቲካ ዘውግ ነው:: እንስሳቱ የሚወክሉት ደግሞ ሩሲያን ነው:: ሌሎች እንስሳትም  እንደ ባህርያቸው ገፀ ባህሪ ሆነው ተሰይመዋል፤ ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ እንስሳት የታሪክ መንገሪያ ሆነዋል:: አብዛኞቹ ገፀ ባህርያት ደግሞ አሳሞች ናቸው::

አንድነትም ልዩነትም ሊኖራቸው ቢችልም “ፍካሬን” ለማንፀሪያ የዳንቴን እና የጆርጅ ኦርዌልን ሥራዎች መርጫለሁ::

“ፍካሬ” መጽሐፍ እንደ ቀደምት የዶ/ር አለማየሁ ዋሴ መጽሐፎች ሁሉ መነሻው እኛ ነን:: ሀገር በቀል ጉዳይ ለአንባቢያን የቀረበበት ሥራ ነው:: ታሪኮቹ ቅርብ የሆኑት ከዚህ መነሻነት ይመስላል:: ቃላቱ እና ገለፃው ቀላል፣ በተምሳሌታዊ ዘይቤ የቀረቡ ከመሆናቸውም በላይ አጫጭር ዓረፍተ ነገሮቹ እንዲሁም አጫጭር ምእራፎቹ ለማንበብ ይጋብዛሉ:: በየምዕራፉ መግቢያ የዛፍ ሥእሎች መኖራቸው ደግሞ በታሪኩ ውስጥ እንድንሳተፍ ያደርገናል:: ይህም የደራሲውን ምናባዊ ፈጠራ አግዝቶታል ማለት ይቻላል:: ዛፎቹ ባለ ቀለም ቢሆኑ ደግሞ የበለጠ በጫካው ውስጥ ተቀምጠን እንድናነብ ያግዘናል::

“ፍካሬ” መጽሐፍ ለሥነ – ጽሑፍ እንግዳ ያልሆነ፣ ከሁሉም ይልቅ ደግሞ በሙያው ኢኮሎጅስት (የሥነ እፅዋት አጥኝ)  የሆነ ደራሲ ስለዛፍ እና ጫካ ከሚነገረን ሥነ – ሕይወታዊ ሳይንሳዋ ሀቅ ባሻገር ባነሳው ተምሳሌታዊ ታሪክ እና ገለጻ ዘመንን የዋጀ ጭብጥ  ነው ማለት ይቻላል:: በኢኮሎጅስት እና በሥነ – ጽሑፍ መነፅር መንታ ትርጉም ያላቸው የዛፎቹ ታሪክ አስገራሚ ነው::

ከዛፎቹ ሥነ – ሕይወታዊ እውነት ባሻገር በሰውኛ ዘይቤ የቀረቡ የሥነ – ጽሑፍ ፍች እንደ ሰው አንደበት የተፈጠረላቸው፣ ልሳናቸው የተፈታ ዛፎች እኛን አይመስሉም ማለት አይቻልም:: አልፎ አልፎም ነገር ሥራቸው “ብሔር ብሔረሰቦችን” አላስታወሱኝም ማለት አይቻልም::

“ፍካሬን” ለዚህ ዳሰሳ ሳነብ በጫካ ውስጥ የመሆን ስሜት ብቻ ሳይሆን አስገራሚዋን 82 ገደማ ብሔሮችን ከእነቋንቋቸው የያዘችውን ፓፓዋኒው ጊኒን እንዳስታውስ ገፋፍኞል:: ፖፖዋኒው ጊኒ የቋንቋ ጫካ ማለት ናት:: “በፍካሬ” የቀርቀሀ ፍሬ ለማፍራት 50 ዓመት መውሰዱ፣ ባሕር ዛፍ የሀገር በቀል ዛፎች እንዳይጨፈጨፉ ባለፈው 100 ዓመት ያደረገው አስተዋፆኦ እና አሉታዊ ውኃ የመምጠጥ እና የድርቅ ምክንያት መሆኑ፣ አውራሪስ የጫካ እሳት ሲነሳ በቀንዱ አፈሩን  እየገፋ ለማጥፋት የሚያደርገው “ደመ ነፍሳዊ” ጥረት ይገርማል:: በዚህ ላይ በፍካሬ መጽሐፍ እፅዋት እና እንስሳት ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው ምስጢራዊ ትስስር፣ ሳይንሳዊ እውነት ማንንም የሚያስደንቅ ነው::

ለአብነት ምዕራፍ ሰባት እፅዋት እንዲያውም እንስሳት እኛን አያምኑንም፤ የእኛ ጥገኞች አይደሉምን?… ምፀታዊ … ካካካ… ቀረ ቀር…. ጸጸጸ…. ሽሻሻ… የዛፍ ሳቅ የተገለፀበት መንገድ ገላጭ ነው:: መሪ ለመምረጥ በተከታታይ የተካሄደው ጉባኤ እና ውዝግቡ፣ ከሁሉም ይልቅ በሰባተኛው ጉባኤ ጽጌረዳ ለመሪነት የሰው ልጅን በመምረጧ በጉባኤው የተፈጠረው ትርምስ… የሚነግረን ግልጥ እውነት አለ::

ሁሉም ራሱን በመሪነት ያጨበት አጋጣሚ የግብረ እፅዋት መለያ ይሆን? የሚል ጥያቄ ይፈጥራል:: የሚገርመው ደግሞ እርሱ ካልሆነ ሌላው አይሆንም ብሎ በጭፍን የማመን የዘመናችን ችግር ተንፀባርቋል:: ምናልባት ይህ  ሁኔታ የዘመን መንፈስ መገለጫ አይደለም ማለት አንችልም:: በዚህ እንደ (ደሞክራሲ) “እፅዋቶ ክራሲ” ባህሪ አለመገረም አይቻልም:: “… ያልተፈጠረ አደረጃጀት፣ ያልተሰየመ የቡደን አይነት አልነበረም” በማለት በእፅዋት በኩል የአሁኑ የፖለቲካ ባህላችን የሚተች ሀሳብ እንደተንፀባረቀ ይሰማኛል::

በተለይ ደግሞ ከምእራፍ 11 ጀምሮ እፅዋቱ የሰው ባህሪ የሚመስል እልቂት፣ መናቆር፣ መቧደን፣ መፋጀት እና መጨፋጨፍ ግብረ እንስሳት እንጂ ግብረ እፅዋት አይመስልም:: ደራሲው በመጽሐፉ ገፅ ሦስት ላይ ባሰፈሩት ማስታወሻ ለነፍሴ ቅርብ ለሆኑ እፅዋት እና ለምወደው ጫካ ካለኝ ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ምናብ የታከለበትን የገሀዱን ዓለም ለማሳየት እንጂ “ሌላ ጉዳይ የሚመስለው ካለ እሰየው እንኳንም መሰለው” የሚል አስተያየታቸውን እያከበርን፤ በተለይ ከሥነ – ጽሑፍ አንፃር ዕይታችንን መቃኜት ተገቢ ነው ማለት እንወዳለን::

የእፅዋት ሥነ – ሕይዎታዊ ባህሪ በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ እፅዋት የተወከሉበት ትእምርታዊ እና ተምሳሌታዊ ሰዎች ባህሪ የገሀዱ ዓለም እውነታ ነው:: የእፅዋት ሳይንሳዊ ባህሪ እንዳለ ሆኖ ውክልናቸው ደግሞ ሰው ነው:: ለምሳሌ ርስ በርስ ከሚጨፋጨፉት እፅዋት በተቃራኒ መድኃኒትነት ያላቸው እፅዋት ጠቢብነትን፣ ማስተዋልን እና መረጋጋትን ማንሳት ይቻላል:: ምዕራፍ 13 ላይ  የ “ጉባኤ ደሸት  ስብስብን ልብ ይሏል:: ምዕራፍ 23 ገፅ 164 ላይ የእነ እፀ ሕርመት የመፍትሄ ሀሳብ የፀሐይ ብርሃን ችግርን ለመፍታት የተወሰደውን እርምጃ፣ የመደማመጥ እና የመመካከር፣ የመመራመር እንዲሁም የመሠልጠን ምልክት ህብረ ቀለም ዋና መልእክት ወይም  ጭብጥ አድርጎ ማየት ይቻላል::

ምስለ ክርስቶስን እና ጥልቅ ፍቅር ያለበትን መስዋእትነት እንዲያሳዩ ተደርገው የቀረቡት እንደ “ዋልያ መቀር” አይነት እፅዋት ይደንቃሉ:: የናይሎቲክ ግራር ተአምር እጅግ ይገርማል:: እንዲሁም ካንሰርን የመፈወስ ኃይል ያላቸው “ሆማ”ን የመሰሉ ሀኪም እፅዋት ያስደምማሉ::

መራራው ኮሶ የእውነት ማሳያ ትእምርት ሆኖ መቅረቡን፣ “ብዙ አቅም፣ ብዙ መልክ፣ ብዙ ገፅ… ልዩ ፍጥረት፣ ሥራ፣ ብዙ ቅርንጫፈ ሰፊ ነን “ ከሚለው አገላለጽ በእርግጥም በልዩነት ውስጥ ያለውን የጫካን አንድነት እንመለከትበታለን፤ እንማርበትማለን::

እንደ ገተም አይነት ገራም እፅዋት ሳይንሳዊ ሥነ – ሕይዎታዊ ባህሪያቸው ብቻ ሳይሆን ሰዋዊ ውክልናቸው ያስገርማል::

እፅዋት ሕዝብን፣ ጫካ ሀገርን እንደወከሉም መገመት ይቻላል:: በገፅ 126 ላይ ገተም ለወገኖቹ ቀሪ እፅዋት “መሪ የሚመጣው ጫካ ሲኖር ነው:: ጫካ ደግሞ የእፅዋት መስተጋብር ነው:: መሪነት ካማረን ጫካው ስለመኖሩም እርግጠኛ መሆን አለብን:: መሪ ከፈለግን ጫካነታችን ጠንካራ ሥርዓት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ አለብን:: እውነተኛ መሪን የሚፈጥረው የተረጋጋ ማህበረ እፅዋት ነው “ ይላል::

ምዕራፍ 18 ደግሞ ማህበራዊ መስተጋብር፣ ማህበረሰባዊ አንድነት እንደሚያስፈልግ የምንገነዘብበት ክፍል ነው:: መሪን የተመለከተው የገተም ፍልስፍና ድንቅ እና ግሩም ነው:: “ደሸታዊያን” ኤሊቱን (ልሂቁን) ወካይ ሆነው ነው የቀረበት::

ፍካሬን እያነበብኩ ያስታውስኩት እንስሳት እና እፅዋትን እንደሰው የማናገር ሁኔታ ቀደም ሲል ድንቅ ቁም ነገር በቋጠሩ ተረቶች፣ ከሲኒማ እና ቴሌቪዥን መፈጠር በኋላም ተረት የሚነግሩን የአሻንጉሊት ፊልሞች የተለመዱ ናቸው:: በሰው ልሳን የሚናገሩ እንስሳትን እና እፅዋትን እናያለን፤ እንሰማለን::

ከሁሉም ይልቅ ደግሞ በተለይ በተረት ውስጥ ያለውን ጥልቅ ጥበብ እንድናስብ፣ ስለ እፅዋት ሳይንሳዊ ባህሪ እንድንረዳ የሚያደርግ መጽሐፍ ነው::

“ፍካሬ” ስለ እፅዋት ሳይንሳዊ እና ሥነ – ሕይዎታዊ ሀቅ፤ ምናባዊ በሆነ የሥነ – ጽሑፍ ሥራ ነው:: በአዳም ረታ አገላለጽ የ“ስርግር” (Rhizom) ፍልስፍናዊ መነፅርም ሊታይ ይችላል:: በእዕዋት በኩል የሚነገረን የቀውስ እና የችግር ታሪክ በብሔር የተተረጐመበት ድርሰት ነው:: ችግር እና መከራ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ፍኖት የሚያመላክቱ አማራጮች እና የመፍትሄ ሀሳቦች ተመላክተውበታል::

“ከ“ስርግር (Rhizom) ሕይዎትን በልኩ መኖር፣ ከተለያዩ ጫናዎች ተላቆ ራስን ሆኖ መኖር ነው”፤ ይላሉ; ድሉዘ እና ጉተር የተባሉ ፈላስፋን የጠቀሱ አንድ አብረሃም ገብሬ የተባሉ የማህበራዊ ሚደያ ጦማሪ:: በርግጥም በ “ፍካሬ” ውስጥ እፅዋት ውስብስብ እንቆቅልሾችን ሴራ፣ የሞራል ዝቅታችንን ያሄሳሉ፣፡ ከቀውስ ወደ ቀውስ የምናደርገውን ጉዞ ቆም ብለን እንድንታዘብ ይጋብዙናል:: ከዚህ ቀውስ የምንወጣበትን በር ሁሉ “በደሸት ጉባኤ” በኩል ይጠቁሙናል:: በዛፋዊ ዕይታ፣ በጫካ ሥነ – ልቦና እያየነው ባላስተዋለነው፣ እየሰማን ባላደመጥነው ታሪክ እንድንሳተፍ ሆኖ ነው የቀረበበው፤  በእውነቱ  በዛፍ ውስጥ ህብር የሕይዎት አተያያን እናይበታለን::

(ታደሰ ጸጋ)

በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here