በቻይና 97 ኪሎግራም ክብደት የነበረው የ31 ዓመቱ የቀዶ ጥገና ሀኪም አዘወትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመስራቱ በ42 ቀናት ውስጥ 25 ኪሎግራም ቀንሶ በዓለም አቀፍ የቅርፅ ውድድር አሸናፊ ሊሆን መቻሉን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶቷል::
ዶክተር ዉ ቲያን ጄን በተካነበት የህክምና ሞያ ከመጠን በላይ ለውፍረት የተጋለጡ ህሙማን ሲገጥሙት ክብደታቸውን እንዲቀንሱ ምክር ይሰጥ ነበር:: ምነው ቢሉ? ለተለያዩ ተዛማጅ የጤና እክል ያበቃልና:: “ጠንቋይ ለራሱ…” እንዲሉ እሱም የተወሰነ ክብደት መቀነስ እንዳለበት አምኖ በተደረገለት ምርመራ በጉበቱ አካባቢ ስብ መከማቸቱን እና መቀነስ እንዳለበት ይነገረዋል::
ዶክተር ዉ ቲያንጄን በታህሳስ ወር መጨረሻ 2024 እ.አ.አ በሁቤ ዞንግናን ሆስፒታል ሀኪሞች ክብደቱ 97 ኪሎ ግራም መሆኑ እንደተነገረው እና በአጭር ጊዜ በጠንካራ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ትርፉን ማራገፍ እንደሚገባውም አስጠንቅቀውታል::
የተሰጠውን ሞያዊ ምክር ተቀብሎ ከመደበኛ ስራው ጐን ለጐን በመጀመሪያዎቹ ቀናት በቀን ለሁለት ሰዓት እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ቀናት በቀን ለአራት ሰዓታት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ቻለ:: እንግዲህ በመደበኛ የህክምና ስራው በሳምንት ሦስት ቀዶ ህክምና፣ ለሁለት ቀናት የተኙ ህሙማን ተዘዋውሮ መጐብኘት እንዲሁም ከምርምር እና የማማከር ተግባራት በተጨማሪ መሆኑን ልብ ይሏል::
ከመጠን በላይ ውፍረት የገጠመው ዶክተር ዉ ማለዳ 11፡30 ከእንቅልፉ ተነስቶ ለአንድ ሰዓት የልብ ምት ማስተካከያ እና የአተነፋፈስ እንቅስቃሴን ሰርቶ ወደ መደበኛ ስራው ያመራል፤ ከስራ ተመልሶ ተጨማሪ አንድ ሰዓት ተመሣሣይ እንቅስቃሴ ሰርቶ የተሟሟቀ አካሉን አቀዝቅዞ ከታጠበ በኋላ ወደ መኝታው እንደሚያመራም ነው ያብራራው::
ይህንን እንቅስቃሴ ሲያደርግ አገሩን ቻይናን ወክሎ ሉቲኒያ ላይ በተደረገ ዓለም አቀፍ ውድድር በ2024 እ.አ.አ አሸናፊ በነበረው አትሌት ሺ ፋን አሰልጣኝነት ይታገዝ ነበር::
በመጨረሻም ከ97 ኪሎግራም 25 ኪሎ ግራም ቀንሶ በ72 ኪሎ ግራም ክብደቱ ዶክተር ዉ በጥር ወር መጨረሻ 2025 እ.አ.አ በተደረገው የአካል ብቃት ቅርፅ ውድድር ተሸላሚ ሊሆን መቻሉን ድረ ገጹ አስነብቧል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም