በ80 ሚሊዮን ብር ቅርሶች እየተጠገኑ ነው

0
108

ታሪካዊ ቅርሶች የአንድን ክልል የበለፀገ ባሕላዊ፣ ማሕበራዊ እና የስነ-ህንፃ ታሪክ የሚያንፀባርቁ በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ ሀብቶች ናቸው።
ቅርሶች የማንነት ስሜትን ይፈጥራሉ፤ ያለፈውን ጊዜን ለማስታወስ ያገለግላሉ። ያለፈውን ታሪክ እንድንማር የሚያስችሉንም ናቸው፡፡ ነገር ግን ከከተሞች መስፋፋትና ፈጣን ልማት ጋር በተገናኘ፣ በትኩረት ማነስ፣ በባለሙያ እጥረት እና በተያያዥ ምክንያች ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ ፈተናዎች ገጥመዋል።
ታሪካዊ ቅርሶችን በመጠበቅ ረገድ የስነ-ህንፃ ስልቶች ቀዳሚ ተግባራት አንዱ የህንፃዎችን አካላዊ ታማኝነት ማረጋገጥ ነው። በጊዜ ሂደት ታሪካዊ ሕንፃዎች እና ሀውልቶች በአየር ሁኔታ እና በኢንዱስትሪ ብክለት ገጽታቸው ሊበላሽ ይችላል። የጥበቃ ባለሙያዎች ተለምዷዊ እደ -ጥበብን፣ ቁሳቁሶችን እና የተራቀቁ ቴክኖሎጅዎችን ተጠቅመው ጥንታዊ ህንጻዎችን ለማደስ እና ለማረጋጋት ልዩ የማገገሚያ ቴክኒኮችን ይጠቀማሉ። ይህ አካሄድ የታሪካዊ አወቃቀሮችን ህልውና የሚያረጋግጥ ሲሆን ዋናውን፣ ትክክለኛነት እና ውበትን በመጠበቅ ይከናወናል።
እነዚህን መሠረታዊ ተግባራት ግምት ውስጥ በማስገባት በአማራ ክልል የሚገኙ ጉዳት ያለባቸውን ቅርሶች የጥገና ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፤ ለዚህም 80 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ወደ ሥራ መገባቱን የቢሮው ኃላፊ መልካሙ ፀጋዬ አስታውቀዋል።
ከቢሮው የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው የቢሮው የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል፤ የቅርሶችን የጉዳት ደረጃ በመለየት የጥገና በጀቱ መደልደሉን አቶ መልካሙ ተናግረዋል። በዚህም 41 ቅርሶች ተለይተው በተራ ቅደም ተከተል (እንደ ጉዳት ደረጃቸው) ጥገና እየተደረገላቸው ይገኛል።

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here