ቡሄን በደብረ ታቦር

0
133

ሀገራት የሕዝቦቻቸውን ወግ፣ ባሕል እና ትውፊት የሚያንጸባርቁበት በርካታ መገለጫዎች አሏቸው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ  በቀዳሚነት  ከሚጠቀሱት  መካከል ናት።

ዓመቱን ሙሉ ደምቀው የሚከበሩ ሐይማኖታዊ  እና  ሕዝባዊ  በዓላት  ኢትዮጵያዊ ቀለም  ደምቆ  የሚታይባቸው  በረከቶች  ናቸው፡፡

ለአብነትም በመስከረም መስቀል፣ በታሕሳስ ገና፣ በጥር ጥምቀት፣ ቃና ዘገሊላ፣ አስተርዮ ማርያም፣ የመርቆሪዮስ፣ የኢድአልፈጥር፣ የኢድአልአድሀ እንዲሁም የመውሊድ በዓላት ተጠቃሾች ናቸው።

አስራሦስት ወራትን ሙሉ የጸሐይ ብርሃን የማይለያት ሀገራችን እያንዳንዱ ወራት የየራሱ መገለጫዎች አሉት። ነሐሴ ወር ሲነሳ ደግሞ ቡሄ፣ እንግጫ ነቀላ፣ ሻደይ፣ አሸንድየ እና ሶለል አብረው የሚነሱ የወሩ በረከቶች ናቸው።

እነዚህ በዓላት ዕሴታቸው ተጠብቆ በትውልድ ቅብብሎሽ የቀጠሉ ናቸው። የዚህ ዘመን ትውልድም ኃላፊነቱን ተቀብሏል። በደብረታቦር ከተማ በወጣቶች፣ ታዳጊዎች እና ሕጻናት ዘንድ የተመለከትነውንም ይህን የአደራ ተቀባይነት እና አደራውንም ለቀጣዩ ትውልድ ለማሸጋገር የሚደረግን ፍሬ ያረጋግጣል።

እኛም በዚሁ ጽሑፋችን ወደ ደብረታቦር በሐሳብ አስጉዘናችሁ የቡሄን በዓል እናስቃኛችዋለን – ቡሄን በደብረ ታቦር።

የቡሄ በዓል (ደብረታቦር) ሲነሳ ደብረታቦር ከተማ አብራ ትነሳለች። ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ገጽታዎች ናቸው። ለምን? ቢሉ የቡሄ በዓል እና ጥንታዊቷ ከተማ ከስያሜ ጀምሮ አንዱ በሌላው የሚደምቁ በመሆናቸው ነው። የቡሄ በዓል በደብረታቦር ይደምቃል፣ ደብረታቦርም በቡሄ ትደምቃለች። ደብረታቦር ኢየሱስ ቤተክርድቲያን ደግሞ የድምቀቱ መዕከል ነው።

“ደብረ ታቦር ከዋለ የለም ክረምት፣

ምነው አለ እንጂ ወር ከሁለት ሳምንት!”

ስንኙ የቡሄን ወይም የደብረታቦር በዓልን ተከትሎ የሚዘወተር ነው። ምክንያቱ ደግሞ ከበዓሉ ማግስት የክረምቱን መጠናቀቅ እና የበጋውን የመምጣት ተስፋ ለማሳየት እንደሆነ ይነገራል።

ከዚህ ጋር አገናኝተው የቡሄ ትርጉም መገለጥ፣ ክረምቱ አልፎ የብርሃን ጎህ የሚወጣበት ወቅት ማብሰሪያ መሆኑን ያብራሩልን የደብረታቦር ኢየሱስ እና የመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ አስተዳዳሪና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተክሌ አቋቋም ምስክር ትምህርት ቤት ምክትል መምህር መላከ ታቦር ዘውዴ መንግሥቱ ናቸው።

 

መላከ ታቦር እንዳስገነዘቡት በዓሉ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶ ከነብያት እና ከሐዋርያት ጋር በመሆን በደብረታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበትን ምስጢር የሚያዘክር ነው።

ቡሄ እና ከተማዋ ያላቸውን ቁርኝት በተመለከተ ለመላከ ታቦር ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር። እርሳቸውም ደብረታቦር ከተማ በአጼ ሰይፈ አርዕድ እንደተሰየመች በማስታወስ ስያሜው የተሰጠው ደግሞ በኢየሩሳሌም ያዩት ታቦር የተሰኘው ተራራ የሚመስለው ቦታ ይህ በመሆኑ ከዛ ተነስተው ደብርታቦር እንዳሏት መላከ ታቦር ዘውዴ ነግረውናል።

በበዓሉ ወጣት ወንዶች ሙሉሙል ዳቦ ይዘው፣ በጅራፍ ጩኸት ውብ ድምጸት ታጅበው በየቤቱ እየዞሩ ያዜማሉ፣ ነዋሪውንም ያወድሳሉ።  የቤቱ ባለቤትም ስጦታ (ሙልሙል ዳቦ) ይበረከትላቸዋል።

ይህ በዘመናት ሂደት ዕሴቱን ጠብቆ በድምቀት እየተከበረ የተሸጋገረውን በዓል ታዲያ ትውፊቱን ሳይለቅ ለቀጣይ ትውልድ ማሸጋገር የዚህ ትውልድ አደራ ነው።

በዓሉ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ  ለተተኪ ትውልድ በማስረከብ ማስቀጠል ይገባል የሚለው ደግሞ የመላከ ታቦር ዘውዴ አባታዊ ምክር ነው።

ቡሄ መነሻው ሃይማኖታዊ ሥርዓት  ቢሆንም ባሕላዊ ክዋኔዎች እንደሚንጸባረቁበት የተናገሩት ደግሞ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለበል ደመላሽ ናቸው ። እነዚህ ክዋኔዎችም ከዋዜማው ጀምሮ ነው የሚደምቁት።

የዋዜማው ዕለት የእቴጌ ጣይቱ የልደት ቀን መሆኑ ደግሞ ሌላው የበዓሉ ውብ ገጽ ነው። ይህም በዓሉን ለየት ያደርገዋል። እነዚህ ልዩ ክስተቶች ሁሉ ተጨማምረው ታዲያ በዓሉም በዚያው ልክ በድምቀት እንደሚከበር ነው አቶ አለበል የነገሩን።

የቡሄ /ደብረታቦር/ በዓልን ሀይማኖታዊ እና ባሕላዊ ይዘቱን ጠብቆ ማክበር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ያሉን አቶ አለበል በዓሉ አንድነትን የሚያጎለብት፣  አብሮነትንም የሚያጠናክር ነው ይላሉ።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ በዓሉ የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ለገቢ ምንጭነት እንዲውል ያደርጋል። ባሕልን ለማስተዋወቅም መልካም አጋጣሚ ነው። ይህን ውብ ትውፊት በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ እየተሠራበት ስለመሆኑም ነው የተነገረው። ለዚህም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አቶ አለበል ጥሪ አቅርበዋል።

 

(አለምነሽ ንጉሴ)

በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ

በhttp:// www.ameco.et/Bekur

በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here