በየዕለቱ አንድ ሲኒ ቡና መጠጣት የልብ ምትን አዛብቶ፣ የደም ግፊትን በመጨመር፣ ለደም መፍሰስ “ስትሮክ” ወይም ለልብ ድካም የሚያጋልጠውን “ኦትሪያል ፋይብሪሌሽን”ን መከላከል እንደሚያስችል ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል፡፡
የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ በመረጃ ምንጭነት ለንባብ እንዳበቀው በተመራማሪዎች በተደረገ አዲስ ጥናት ቡና መጠጣት የልብ ምት መዛባት (አትሪያል ፋይብሪሌሽን)ን መከላከል እንደሚያስችል ተረጋግጧል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት የጤና ባለሙያዎች የልብ ምት መዛባት ያለባቸው ሰዎች ቡና ከመጠጣት እንዲርቁ ወይም እንዲተዉ ሲመክሩ ቆይተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ያደረጉት አዲስ ጥናት ግን ቡና መጠጣት የልብ ምት መዛባትን 39 በመቶ መቀነስ እንደሚያስችል ነው ያመላከተው፡፡
ተመራማሪዎቹ በጥናታቸው ለደረሱበት ድምዳሜ ግብአት ይሆን ዘንድ 200 የተዛባ የልብ ምት የነበረባቸው ህሙማንን በሁለት በመክፈል ከፊሎቹ ለስድስት ወራት በየእለቱ ቡና እንዲጠጡ ከፊሎቹ ደግሞ ከማናቸውም የ“ካፊን” ንጥረ ነገር ካለው መጠጥ እንዲታቀቡ አድርገዋል፡፡ በውጤቱም ቡና የጠጡቱ 39 በመቶ የልብ ምት መዛባት “አትሪያል ፋይብሪሌሽን” ቀንሶላቸው ተስተውሏል፡፡
ከተደረገው ጥናት የተገኘውን ውጤት መሰረት አድርገው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ክሪስቶፈር ኤከስ ዋንግ እና የአደላይድ ዩኒቨርሲቲው አቻዎቻቸው ቡና መጠጣት ደህንነቱ የተጠበቀ ብቻ ሳይሆን የልብ ችግርን የመከላከል አቅም እንዳለው አማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ተመራማሪዎቹ በአሁኑ ወቅት 37 ሚሊዬን የልብ ምት መዛባት ህመም ያለባቸው ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በመጨረሻ አዲሱ የሊቃውንቱ ጥናት በየእለቱ ቡና መጠጣት መድህን መሆኑን በማጉላት ነው ያደማደሙት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሕዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


