ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአነቃቂ ንግግር አድራጊዎች በሀገራችን ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ማህበራዊ ትስስር ገጹ ደግሞ የአነቃቂዎች ዋና መገኛ መድረክ ነው።
ማነቃቃት ዋና ዓላማው ቀስቅሶ ወደ ስራ ማስገባት ነው። የሰው ልጆች በተፈጥሮ የተሰጣቸውን እምቅ አቅም አውጥተው እንዲጠቀሙበት ማስቻል ነው። ማንቃት መደገፍ እንጂ ተሸክሞ ማድረስ ወይም መጓዝ አይደለም። የተደበቀውን አቅም በማቀጣጠል አቅምን ወደ ተግባር መቀየር ነው። ባለመረዳት፣ ባለማስተዋል፣ በማጣት፣ በችግር፣ በስንፍና፣ በአመለካከት፣ በፈተና መብዛት የሰው ልጆች ከአምላካቸው የተሰጣቸውን የማደግ፣ የመለወጥ እና የተሻለ ሕይወት ለመኖር የተሰጠ አቅም ሳይጠቀሙበት ያልፋሉ። በአጭሩ ማነቃቃት ማለት የተኛን መቀስቀስ፣ ወደ ድርጊት ማስገባት ነው ብለን ልንጠራው እንችላለን።
ዘመናዊው የትምህርት ስርዓት እንጀራ ለመብላት ከሚሆን የተሻገረ እውቀት አልሰጠንም። ተምሮ ከመቀጠር በኋላ ሌሎች የሕይወት ገጾች አሉ። ሕይወት መስራት እና መብላት ብቻ አይደለም። አነቃቂዎች የሰብዕና ግንባታ፣ የሕይወት ክህሎት እና የአመለካከት ለውጥ አምጪ ስልጠናዎችን እና ንግግሮችን ነው የሚያቀርቡት።
አነቃቂዎች በሁለት ዘርፍ ተከፍለው የሚታዩ ናቸው። የመጀመሪያው ዘርፍ ውስጥ ያሉት ሳይንሱን በመማር በባለሙያነት ሰልጥነው፣ ወይም ያነበቡትን እውቀት ለሌሎች የሚያጋሩ ናቸው። ሁለተኛዎቹ ደግሞ ያለፉበትን የሕይወት መንገድ ከስኬት እና ውድቀት ሰው ይማራል ብለው በማመን ከእኔ ተማሩ የሚሉ ናቸው።
ሻለቃ አትሌት ኀይሌ ገብረ ሥላሴ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ስኬት ተሞክሮ ያለፉበትን የሕይወት መስመር ከሚያስተምሩ አነቃቂ ሰዎች ሊመደብ ይችላል። ኀይሌ በፍሬው ታይቷል። ብዙዎች ለማመን አይቸገሩም። እኔም በሆንሁ የሚል ስሜታዊ ንሸጣ ያድርባቸዋል። ኀይሌ ስለገንዘብ ማግኘት ሲያወራ ሰዎች ልባቸውን ከፍተው ይሰሙታል።
በአንጻሩ አንድ ጎረምሳ በቲክቶክ ወይም ዩቱዩብ 10 የገንዘብ ማግኛ ዘዴዎች ብሎ ቢያወራ ያልተራመደበትን ወይም የሸመደደውን ሳይንስ ብቻ ስለሚናገር ለስሜት አይቀርብም። ሐሳቡ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ቢሆንም እንኳን ሰሚው ደግሞ አንተ ማን ሆነህ ነው የምታስተምረኝ ብሎ ወደ ውስጡ ሳያስገባው ይቀራል። የሰው አዕምሮ ነገሮችን በደመ ነፍስ አይቀበልም። የሚሰማውን መረጃ የሚናገረው ሰው ማን ነው የሚለውን ይመዝናል።
የአነቃቂዎች ማንነት ሰሚዎች ሐሳቡን አድምጠው፣ ነቅተው፣ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጉልህ ሚና አለው። መነቃቃት አልፈልግም የሚሉም ሰዎች አሉ። ቡና ያነቃኛል ብለውም አነቃቂዎችን የሚተርቡ አሉ። አነቃቂ ንግግሮችን አትስሙ ብለውም ማነቃቂያ ቪዲዮ የሚሰሩ አሉ። አነቃቂዎች የሚያስተላልፉት ልምድ ወይም እውቀት ለሁሉም የሚሆን አይደለም። ለአንዱ ይረዝማል፣ ለሌላው ያጥራል። ጭራሽ የማይሆነውም ይኖራል።
አነቃቂ ንግግር አይሰራም? ሁለት መልሶች በዘርፉ ምሁራን በኩል ይቀርባሉ፤ ይሰራልም አይሰራምም የሚሉ። አምኖ የመቀበል ጉዳይ ነው። የአስተሳሰብ ጉዳይ ነው። የጥረት እና ቀጣይነት ጉዳይ ነው።
በጣም ብዙ ጊዜያት አነቃቂ ንግግሮችን ሰምቻለሁ። ማስታወሻ ያዝ ሲሉኝም እየጻፍሁ እንደ ትምህርት ሰምቻለሁ። እንዲሁ እንደ እኔ ሁሉ ለረጂም ሰዓታት የሰዎችን አነቃቂ ንግግሮች በመስማት አነቃቂ ንግግር አድራጊ የሆኑ ሰዎችም አሉ። ንግግሮችን እንደ ዜና በመስማት እያሳለፉ አዳዲስ ንግግር እስኪመጣላቸው የሚጠብቁም አሉ። ከነበሩበት ችግር ወጥተው ጥሩ ስራ፣ ንግድ፣ ትምህርት፣ ትዳር፣ ሰላማዊ ሕይወት የጀመሩም አሉ። የቀናት ንግግሮችን ሰምተው ከአልጋቸው ያልወረዱ፣ ዛሬም አነቃቂ ንግግሮችን የሚሰሙም አሉ። አነቃቂዎች ለምን ወደ ተግባር እንድንገባ አላደረጉንም?
አነቃቂ ንግግር እንደተወጠረ ጎማ ነው የሚያደርገው፤ ነፋስ ላይ መርገብገብ። ማነቃቃት እንድ እርምጃ እንጂ መድረሻ ግብ አይደለም። ብዙዎች የሚረሱት ማነቃቃት ዓይንን መግለጥ፣ መንገድ ማሳየት፣ ከእንቅልፍ መቀስቀስ መሆኑን ነው። የእገሌን ምክር ሰምቼ ትዳሬን አጣሁ፣ የእገሊትን ምክር ሰምቼ ወረቴን ከሰርሁ ሲሉ ይሰማሉ፤ የእገሌ ምክር ሰምቼ ጥሩ ስራ ጀመርሁ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ። ማነቃቃት ጊዜያዊ መነሳሳት ይፈጥራል። ስሜት ላይ ብቻ ይንጠለጠላል። ቀጥሎ ተግባር እና ቀጣይነት ወይም ዲሲፕሊን ናቸው ለፍሬ የሚያበቁት። ብዙዎች በመነቃቃት ሩጫ፣ ንግድ፣ ስራ፣ ትዳር ፍቅር፣ ወዳጅነት ጀምረዋል። የቀጠሉት ግን ጥቂት ናቸው። ማነቃቃት ያስጀምር ይሆናል። የሚያስቀጥለው ግን ዲሲፕሊን ነው።
ደሞዝ ጭማሪ፣ የተጨማሪ ሰዓት ክፍያ፣ ሽልማት፣ ጥሩ ንግግር ሰዎችን ያነቃቃቸው ይሆናል። ጂም ሮን ሞቲቬሽን (መነቃቃት) እንድትጀምር ያደርግሃል፤ የሚያስቀጥልህ ግን ዲሲፕሊን ነው ይላል። በዚህም ሞቲቬሽን ከመጀመር በላይ አንድን ጉዳይ ያለማቋረጥ ማስቀጠል ነው። አንድ ነገር መደረግ እስካለበት ጊዜ ድረስ ቢከብደንም ቢቀለንም ማድረግ ነው፤ ወይም ደግሞ መደረግ የሌለበትን ተግባር ፈለግንም አልፈለግንም አለማድረግ ነው። ይህ ቁርጠኝነት ነው ለምንፈልገው ዓላማ የሚያተጋን።
በአነቃቂ ንግግሮች መነሻነት ወደ ድርጊት መግባት ያስፈራል፤ ለውጥም ቀላል ነገር አይደለም። መጠራጠር እና ምቾት ማጣት ለለውጥ ስንነሳ የሚገጥመን ጉዳይ ነው። እነዚህን አስፈሪ ነገሮችን መጋፈጥ ይጠይቃል፤ ከመነቃቃት በኋላ ወደ ተግባር ለመግባት።
ዜን ሀቢትስ ገጽ መነቃቃት በድርጊት መታገዝ አለበት ይላል። በተጀመረ ግለት ተግባር ውስጥ ለመግባት ደግሞ መከወን አለባቸው ያላቸውን ደረጃዎች ዘርዝሯል።
ዓላማን ማወቅ የመጀመሪያው ሒደት ነው። ብዙዎቻችን በሕይወታችን ዓላማ የለንም። መሆን ያለበት ግን ማንም ሰው የሚኖረው ለምን እንደሆነ በማቀድ ያንን ግብ ለማሳካት ደግሞ መትጋት ነው። ዓላማ ከሌለህ አሁን ጀምር ይላል ዜን ሀቢትስ። በሕይወትህ መጨረሻ፣ ከዓመታት በኋላ ምን መሆን ነው የምትፈልገው? በሕይወትህ ዋጋ የምትሰጠው ትልቁ ነገር ምንድን ነው? የሕይወትህስ ትርጉም ምንድን ነው? ሲል ይጠይቃል። ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከሌለህ እስኪ የእግር ጉዞ እያደረግህ ማሰብ ጀምር ይላል። ጊዜ ሰጥተህ ማሰብ መጀመር ቀዳሚው ሒደት ነው።
ፍላጎትህን ተቀበል። ይህንን ጽሑፍ ስታነብ በሕይወትህ አንዳች አዎንታዊ ነገር ማግኘት የሚያስችል መሻት አለህ ማለት ነው። መልካም ነገር መስራት እፈልጋለሁ የሚል መሻትህን ተቀበለው። አዎ ልክ ነው ይገባኛል፤ ማድረግ አለብኝ ብለህ አስብ። እንደዚህ አይነት መልካም መሻት ቢኖርህ ጥሩ አይመስልህም? ይህንን በሕይወትህ የወሰድኸው የመጀመሪያው አዎንታዊ ርምጃ አድርገህ ተቀበለው። እናም ይህን ጅምር መጠቀም እና ድርጊት ውስጥ መግባት ጀምር።
ነጠል የምትልበት ሁኔታ ፍጠር። ለለውጥ አንዲት ትንሽ ምቹ ቦታ መፍጠር ካልቻልህ ምንም ዓይነት ውጤት ማምጣት አትችልም። ይህንን ለውጥ መቼ ማምጣት እንደምትችል አስብ። ይህንን ለውጥ ጠዋት፣ ምሳ ሰዓት፣ ወይስ ማታ ነው ማምጣት የምፈልገው የሚለውን መለየት ተገቢ ነው። ለውጥ መጥቶ እጅህን እንዲጨብጥህ አትጠብቀው፤ አንተ ራስህ ነህ ሄደህ ማምጣት ያለብህ። ከቀን ውሎህ የተወሰነ ጊዜ ለብቻህ ሆነህ ማሰብ፣ ማቀድ መጀመር አለብህ። አስር ወይም አስራ እምስት ደቂቃዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በእነዚህ ደቂቃዎች ከራስህ ጋር ተነጋገር። በቀን ፌስቡክ፣ ቴሌቪዥን፣ ቲክታክ፣ ጌሞች፣ እና ሌሎች ህይወትህን በማይለውጡ ተግባራት ላይ ምን ያህል ጊዜ እንደምታባክን አስብ እስኪ። እነዚህን ልምዶችህን ተውና ለሚጠቅሙ ጉዳዮች ጊዜህን አውለው። ቅድሚያ ለምትሰጠው ጉዳይ ቅድሚያ ስጥ።
ዙሪያህን ተመልከት። ለውጥ ማምጣት የሚፈልግ ሰው የሚያደርገው ቀዳሚ ጉዳይ ራሱን እሱ ከሚፈልገው ዓላማ ተመሳሳይ ድርጊት እና ውሎ ባላቸው ሰዎች መክበብ ነው። የለውጥ እቅድ፣ ድርጊት እና ሐሳብህን ከሚደግፉ ሰዎች ጋር መዋል ልመድ። ስራህ፣ ጉዞህ እንዴት ነው ብለው በሚጠይቁህ እና በሚደግፉህ፤ ወደ ፊት በሚገፉህ ሰዎች መክበብ አለብህ። አይዞህ፣ በርታ፣ ትችላለህ የሚሉህ ሰዎች በዙሪያህ መኖር ቶሎ ያሳድግሃል።
ተጠያቂነትን ልመድ። በስራህ፣ በጉዞህ የሚከታተልህ አንድ ሰው ይኑርህ። ይህ ሰው ስትደክም፣ ስታንቀላፋ፣ ስትዘናጋ የሚቀሰቅስ እና ጉልበት የሚሆን የለውጥ ሞተር ነው። “ስሳሳት ምከረኝ፣ ሳጠፋ ገስጸኝ፣ ወደ መጠጥ ቤት ስሄድ ተመለስ በለኝ” የምትላቸው ወዳጆች፣ የቡድን መሪዎች ወይም አሰልጣኞች ሊኖሩህ ይገባል። “ከዚህ በኋላ አልኮል ስጠጣ ካገኘኸኝ ግደለኝ” የሚሉ ሰዎች ራሳቸው ላይ አለቆችን በመሾም ለተጠያቂነት ራሳቸውን አሳልፈው እየሰጡ ነው።
በትንሹ መተግበርን ጀምር። ብዙዎች ባላቸው ትንሽ አቅም አይጀምሩም። ሁሉንም ነገር አሟልተው፣ አሳክተው፣ አስደናቂ ተግባርን መፈጸም ይፈልጋሉ። ንግድ ስትጀምር በትንሽ ጀምር። በልምድ ትልቅ የንግድ ስራ ላይ ትደርሳለህ። ድንገት ሰማይ አትንካ፤ ስትመለስ ትሰበራለህ። በሒደት እደግ። ቀስ ብለህ ተራመድ እንጂ ዘልዬ ጫፍ ላይ ልውጣ አትበል፤ ትሰበራለህ። ስትደርስም ለዚህ ነው የዘለልሁት ብለህ ደስታ ታጣለህ። ዛሬ ልትወስደው የምትችለው፤ የሚለውጥህ ምን ጥቂት ተግባር አለህ? አንድ ጊዜ ብዙ እራመዳለሁ ከማለት ትንሽ ትንሽ ርምጃን ወደ ፊት ግፋበት። ለውጥን የምትጀምረው እንዲህ ነው ሲል ዜን ሀቢትስ ጽፏል።
ብዙዎች ለዓመታት አነቃቂ ንግግሮችን ሰምተዋል፣ በሃይማኖት አባቶች ተሰብከዋል፣ በፖለቲከኞች ሰልጥነዋል። ለጊዜው በሰሙት ነገር ተገርመው መነቃቃት ተፈጥሮላቸዋል። አሳካዋለህ፤ እለወጣለሁ፤ ራሴን እቀይራለሁ ብለዋል። እንዳሉትም ሁለት ሦስት ቀናት ተግባር ውስጥ ገብተዋል። በኋላ ግን ሁሉንም ትተውታል። የተለኮሰባቸው የመነቃቃት እሳት ሙቀት ሲጠፋ አቋርጠውታል። ዜን ሀቢትስ ያስቀመጣቸው ደረጃዎች መነቃቃትን ወደ ፍሬ ለመቀየር ማሳያዎች ናቸው።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም