“ቢሆን ኖሮ”ን ለማስቀረት

0
138

እንደ መንደርደሪያ

የሥነ ልቦና አባት በመባል የሚታወቁት ሲግመንድ ፍሩድ “ወጣትነት የሁሉም ነገር መሠረት ነው” ይላሉ፤ ሳይኮ አናሊሲስ (Psycho analysis) በሚለው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት:: ወጣቶች ወርቃማው ዘመናቸውን ሰብዕናን፣ ክህሎትን እና መልካም ግንኙነቶችን በመገንባት ማሳለፍ ይገባቸዋል:: ትኩረታቸውንም ለወደፊት ደህንነታቸው የሚሆኑ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንዲያተኩሩ የሥነ ልቦና ምሁሩ ይመክራሉ:: ለዚህም ወጣቶች በጊዜያዊ ደስታ ላይ ከማትኮር ይልቅ በመማር፣ ለፍላጎቶቻቸው ዕውን መሆን በመትጋት፣ ሌሎችን በመርዳት፣ ንቁ በመሆን እና አዳዲስ  ልምዶችን በመቅሰም ሊሆን ይገባል:: በተመሳሳይ የወጣትነት ዕድሜን በአግባቡ መጠቀም ከጸጸት ያድናል፤ የእርጅና ዘመንን በደስታ ለማሳለፍ መሠረት መሆኑንም የስኬትማ ሰዎች ተሞክሮ ያሳያል::

የጎልማሳው ተሞክሮ

አድዝሃር ኢብራሂም የ59 ዓመት ማሌዢያዊ ጎልማሳ ናቸው፤ ዛሬያቸውን ትናንት እና በአግባቡ በመሥራታቸው ስኬታማ ናቸው፤ ዛሬ ያሉበትን የተሻለ ሕይወት ትናንት በአግባቡ የሠሩ በሚልም ማሌዢያ ቱዴይ ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ ጋብዟቸው ነበር:: ከግማሽ ክፍለ ዘመን (ከ50 ዓመት) በፊት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አብረዋቸው ከነበሩ የድሮ ጓደኞቻቸው ጋር በቅርቡ መገናኘታቸውን ያስታውሳሉ፤ ከሁሉም ጋር መገናኘት ግን አልቻሉም:: ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎች በሕይወት ባለመኖራቸው፣ አንዳንዶቹም በጤና እክል እየተሰቃዩ መሆናቸው፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ብቸኝነትን በመምረጣቸው መሆኑን ጠቁመዋል::

በአካል ከተገናኙት ውስጥ አብዛኞቹ ጡረታ የወጡ፣ ቀሪዎችም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሠማሩ መሆናቸውን ያነሳሉ:: አንዳንዶች ከጡረታ በኋላ ያለው ሕይወታቸው የተመቻቸ፣ ሌሎቹ ደግሞ ባልተመቸ ሁኔታ ውስጥ ኑሮን እየገፉ ለመሆናቸው አካላዊ ገጽታቸው እንደሚናገር መታዘባቸውን የመረጃ ምንጩ ያስነብባል:: ትዝብታቸውንም “የሕይወት ሁለት መልክ ማሳያዎች” ሲሉ ነው የገለጹት:: አድዝሃር “የእርጅና ዘመኔን ያለፉ ስህተቶቼን ለመጠገን በመጣር ብቻ ማሳለፍ አልፈልግም። ይልቁንም አሁኑኑ የተበላሹ ነገሮችን ለማስተካከል የምችለውን ሁሉ ማድረግ እሻለሁ። ያንን ማድረግ ባልችል እንኳ በምትኩ ሌላ መልካም ነገር በማድረግ ካሳ ለመክፈል እጥራለሁ” ሲሉም ሐሳባቸውን ያጠናክራሉ:: የወጣትነትን የዕድሜ ዘመን ወርቃማ የዕድሜ ዘመን የሚሉት ጎልማሳው ጉልበትን መቆጠብ፣ ያገኙትን ገንዘብ እንደፈለጉ መበተን፣ ከጊዜ ጋር አለመፍጠን እና ነገሮችን በጊዜያቸው አለማከናወን “በእርጅና ዕድሜ ጸጸትን ይወልዳል” ይላሉ:: ምክንያቱም  የነገ መሠረት የሚቀመጠው ዛሬ ነውና:: እርሳቸውም የወጣትነት ዘመናቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ዛሬን በጽኑ መሠረት ላይ እንዳቆሙት ነው ተሞክሯቸውን ያካፈሉት::

ሕይወት ቀያሪ የቁጭት ጥያቄዎች

እርጅና ያጠፉትን ለማረም የሚጣርበት የዕድሜ ክልል ሳይሆን ሰዎችን ማስታረቅ፣ ሰብዓዊነት እና መሰል ተግባራት ላይ ትኩረት በማድረግ የሚከናወኑበት ጊዜ መሆኑን የሥነ ልቦና ምሁሩ ሲግመንድ ፍሩድ ያስገነዝባሉ። ነገሮችን በትክክል ለማድረግም ሆነ ለማስተካከል የወጣትነት ዕድሜ ላይ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባልም ይላሉ:: የእርጅና ዘመንን መውቀስ እና መክሰስ እንደማይገባ የሚያብራሩት ምሁሩ ይህ የዕድሜ ክልል “ይልቁንስ የእረፍት እና የእፎይታ ዘመን ነው” ይላሉ:: የሰው ልጅ የዕድሜውን ከግማሽ በላይ ሲደርስ ጥቂት ትላልቅ ጥያቄዎች ወደ አዕምሮው መመላለስ እንደሚጀምሩ ለማሌዢያ ቱዴይ ተሞክሯቸውን ያካፈሉት አድዝሃር ይናገራሉ::

ጥያቄዎቹም ትኩረት ሳይሰጠው ባለፈው የሕይወቱ ዘመን ቁጭትን የሚፈጥሩ ወይም ደግሞ ባለው ቀሪ ዘመኑ ያለ የሌለ ኃይሉን አሟጦ እንዲጠቀም የሚያበረታቱ ናቸው:: “እስካሁን ሕይወቴን እንዴት ኖርኩት?፣ ቀጣዩ ሕይወቴስ ምን ሊመስል ይችላል? የሚሉት ወሳኝ የሕይወት መዳረሻን የሚወስኑ ጥያቄዎች መሆናቸውን የመረጃ ምንጩ አስነብቧል:: ቀጥሎ ምን እንደሚመጣ ማናችንም አናውቅም፤ ቢሆንም ግን እስካሁን የነበረን ቆይታ ዋጋ እና ትርጉም ያለው እንዲሆን፣ የቀሩት ዓመታት ደግሞ የተደላደሉ እንዲሆኑ ተስፋን ሰንቆ መጓዝ ግድ ይላል:: የኖርኩት ሕይወት ለፍርድ ቢቀርብ ፍርዱ መልካም ወይስ የሚያስወቅስ ነው ብሎ ማሰብም ተገቢ እንደሚሆን ምሁሩ አክለዋል::

ነገን መተለምና መጋፈጥ

አድዝሃር ኢብራሂም “ሕይወት ቸር ሆና ከቆየች የቀሩትን ዓመታትን ሁልጊዜ ልናደርጋቸው ስንመኛቸው የነበሩ፤ ነገር ግን ያላደረግናቸውን ነገሮች የማድረግ ዕድል ሰጥታናለችና ዛሬውኑ መነሳት ይኖርብናል” ሲሉ ይመክራሉ:: “አነሳስህ ያማረ እንዲሆን ደግሞ አስቸጋሪ ጊዜያት ሲመጡ በምትወዳቸው ሰዎች ላይ ሸክም አለመሆንን ማሰብ ያስፈልጋል” ነው ያሉት:: የእርጅና ዘመንን ያማረ ለማድረግ የሚያስችል ምጣኔ ሐብታዊ አቅምን ለማሻሻል ከመጣር ባለፈ ለጤና ትኩረት መስጠትም ያስፈልጋል:: የነገ ሥንቅ የሚያዝበትን ወርቃማ ጊዜ በአጉል ሱሰኝነት፣ ባልተገባ ድርጊት ማሳለፍ ለዕድሜ ዘመን የሕይወት ብልሽት እንደሚዳርግ የአድዝሃርን ተሞክሮ ዋቢ አድርጎ ያስነበበው የማሌዢያ ቱዴይ መረጃ ነው:: የሥነ ልቦና አባት በመባል የሚታወቁት ሲግመንድ ፍሩድ ደግሞ ወጣትነት የትኩስ ጉልበት ባለቤት በመሆኑ ነገን ለማሳመር የሚሠራበት ወርቃማ ዘመን ይሉታል:: “ምድር ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ እጅግ አስደናቂ ነው፤ ነገር ግን ውድ እና ተሰባሪም ነው።  የምትችለውን ያህል ተመልከት፤ የአቅምህንም ያክል በመሥራት የነገ ሕይወትህን ያማረ ለማድረግ መጣርን ተለማመድ” ይላሉ ስኬታማው አድዝሃር።

የሰው ልጅ እሱ በፈለገው መንገድ ሕይወትን በመምራት ኑሮውን ማሻሻል አይችልም፤ ይልቁንም ሕይወት በራሷ አዙሪት ውስጥ በመቆጣጠር   ነው  የነገ  ሕይወትን የምትወስነው:: በቁም ነገር ውስጥ ቀልድን፤ በቀልድም ውስጥ ቁም ነገርን በማፈራረቅ ሕይወትን የተሻለ ማድረግ ለሰው ልጅ የተሰጠ ኃይል መሆኑን አድዝሃር ይናገራሉ:: ሕይወትን ቀለል አድርጎ ለመኖር መዝናናት፣ አዳዲስ እና የዓላማ ጓደኞችን ማፍራት፣ መረዳዳትን እና መተጋገዝን ማዳበር አስፈላጊ ነው::

የወርቃማው ዘመን ውጤታማነት ምክረ ሐሳቦች

ወጣቶች የመልካም ሰብዕና እና የዓላማ ሰው መሆን እንዲሁም ጠንካራ ግንኙነትን በመፍጠር ብሩህ የወደፊት ሕይወትን ዛሬውኑ መቅረጽ ይኖርባቸዋል፤ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም የራስን ነገ ከማሳመርም ባለፈ ለሀገር የራስን የተሻለ አሻራ ለማሳረፍ ትልቅ አቅም ይሆናል:: ዓለም የምትለማውም ሆነ የምትጠፋው በወጣቶች አቅም በመሆኑ የወጣትነትን ጉልበት እና የመማር ብቃት በአግባቡ በመጠቀም በጠንካራ መሠረት ላይ ማሳረፍ ይገባል:: መልካም ሰብዕና የወርቃማው ዘመን ዋና መገለጫ መሆንም ይኖርበታል:: ራስን መግዛት፣ ትዕግሥተኛት እና ጀግንነት ያሉ መልካም ዕሴቶችን ማዳበር ደግሞ በወርቃማው ዕድሜ ላይ ግብን ለማሳካት ወሳኝ ናቸው::

ትርጉም ባላቸው ተግባራት ላይ መሰማራት፣ አዳዲስ ክህሎቶችን መማር፣ የራስን የፈጠራ ዝንባሌ ማሳደግ እና በኅብረተሰቡ ውስጥ በጎ ተፅዕኖ መፍጠርም ይገባል። በሕይወት ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር አለመፍራት፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን እና ሥራ ፈጠራን የሚያሳድጉ ዘርፎችን በማበረታታት ችግር የመፍታት ብቃትን ማሳደግ ይገባል።

 

ለዛ

‘‘ሕይወት ትርጉም የሚኖረው ሁሌ ንቁ ስትሆን፣ ግብ ስታበጅ እና በየጊዜው ዓላማህን ከግብ ለማድረስ የሚያስፈልገውን መስዋዕትነትት ስትከፍል ነው’’፡፡ ሌስ ብራውን

‘‘የወደፊቱን ለመተንበይ የተሻለው ዘዴ ወደፊትን መፍጠር ነው’’፡፡  አለን ኬይ

‘‘የዛሬ ዓመት ምናለ ዛሬ ጀምሬ ብሆን ኖሮ ብለህ ትመኛለህ’’ ፡፡ ካረን ላምብ

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የታህሣስ  20  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here