ቢሊየነሩ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች

0
196

ይህን የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋች ብዙዎች የኤስሚላን እና የአርሴናል ደጋፊዎች ያስታውሱታል። በታጋይነቱ፣ በአይደክሜነቱ፣ በታክቲክ አረዳዱ እና በታታሪነቱም ይታወሳል። በሁሉም የመሀል ሜዳ ስፍራ  በመጫወት ሁለገብ ተጫዋች እንደነበርም አይዘነጋም- ማቲዮ ፒየር ፍላሚኒ።

የመሀል ሜዳው ሰው በ1984 እ.አ.አ ነው በፈረንሳይ ማርሴ ከተማ የተወለደው። የእግር ኳስ ህይወቱን በማርሴ ክለብ የጀመረ ሲሆን በፈረንሳዩ ክለብ ጎልብቶ ለታላላቆቹ አርሴናል እና ኤስሚላን በመጫወት ረጅም የእግር ኳስ ህይወቱን አሳልፏል። የቀድሞው አማካይ ለመድፈኞች በአጠቃላይ 246 ጨዋታዎችን አከናውኗል። በኤምሬትስ ቆይታውም ሦስት የኤፍ ኤ  እና አንድ የኮሚኒቲ ሺልድ ዋንጫ አንስቷል።

በአምስት ዓመታት የኤስሚላን ቆይታው ደግሞ እ.አ.አ በ2011 የሴሪ ኤ ዋንጫ አሳክቷል። ፍላሚኒ ከልጅነት ክለቡ ማርሴ ጋርም የኢሮፓ ሊግ ዋንጫ ማሳካቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። የ40 ዓመቱ አማካይ ለስፔኑ ክለብ ጌታፌ፣ ለእንግሊዙ ክለብ ክሪስታል ፓላስ፣ ለቱርኩ ክለብ ጋላታሰራይ እና ለአሜሪካው ክለብ ኤል ኤ ጋላክሲ ክለብም ተጫውቶ አሳልፏል። ማቲዮ ፍላሚኒ በ2019 እ.አ.አ ነበር ከ17 ዓመታት የእግር ኳስ ህይወቱ የተገለለው።

የቀድሞው አማካይ ከእግር ኳስ ሙያው ይልቅ በሌላኛው ሙያው ውጤታማ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። ከእግር ኳስ ሙያው ጎን ለጎን ኩባንያ አቋቁሞ ሲሠራ የቆየው ፍላሚኒ አሁን ላይ አትራፊ የንግድ ሰው መሆኑን ሜል ስፖርት አስነብቧል። እ.አ.አ በ2008 ኤስሚላንን ከተቀላቀለ በኋላ ከቅርብ ወዳጁ ፓስካል ግራናታ ጋር የአሁኑን ግዙፍ ኩባንያ አቋቁሟል።

ኩባንያው ፔትሮሊየም የሚያስቀር አማራጭ ኃይል የሚያመርት ድርጅት ነው። “ጂኤፍ ባዮኬሚካልስ” የሚሰኝ ሲሆን በዋናነት የአየር ንብረት ብክለትን ለመከላከል ታስቦ እንደተቋቋመ ባለአክሲዮኑ እና ሥራ አስኪያጁ ፍላሚኒ ይናገራል። ኩባንያው ሲቋቋም ለምርምር፣ ለቤተ ሙከራ እና ለመሰረተ ልማት ግንባታ በርካታ ሚሊዬን ዩሮ ወጪ አድርገዋል። ከ16 ዓመታት በኋላ ይህ ኩባንያ እጅግ ትርፋማ ሆኖ 30 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚገመት የሚል ስፖርት ዘገባ ያስነብባል። የዚህ ግዙፍ ኩባንያ መቀመጫ በሀገሩ ፈረንሳይ ሲሆን 60 በመቶ የአክሲዮን ድርሻውም የማቲዮ ፍላሚኒ ነው።

“በልጅነቴ ሁለት ህልሞች ነበሩኝ፤ እግር ኳስ መጫወት እና የአየር ብክለትን መከላከል። ያደኩት በማርሴ ሲሆን በአቅራቢያችን ባህር አለ፤ ይህ ባህር በፕላስቲኮች እና በኬሚካሎች የተበከለ ነበር፤ በልጅ አዕምሮዬ አካባቢው መበከል የለበትም የሚል ጥያቄ አነሳ ነበር” ሲል ተደምጧል ፍላሚኒ። የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋች አሁን ህልሙን እየኖረ እንደሆነ ይናገራል። ድርጅቱ የአየር ብክለትን ለመከላከል ከፔትሮሊየም ውጪ አማራጭ የኃይል አቅርቦት ይዞ ብቅ ብሏል። ጂኤፍ ባዮኬሚካልስ አማራጭ የኃይል አቅርቦትን በጅምላ በማቅረብ በዓለማችን የመጀመሪያው ኩባንያ ነው። ከወዳደቁ የፕላስቲክ እና የኮስሞቲክስ እቃዎች ነው የሚመረተው።

ከዚህ ድርጅት በተጨማሪ ከቀድሞው የአርሴናል ኮከብ መሱት ኦዚል ጋርም ሌላ ድርጅት አቋቁመው እየሠሩ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል። “ዩኒቲ ፐርፎርማንስ ላብ” የሚባል ድርጅት አቋቁመዋል። ተቋሙ በዲጂታል የጤና ምክር አገልግሎት፣ በአካል ብቃት እና የኑሮ ዘይቤ ላይ በብቁ ባለሙያ በመታገዝ አገልግሎት ይሰጣል። አገልግሎቱን በተለይ ለአሰልጣኞች እና ለታላላቅ ስፖርተኞች ተደራሽ እንደሚያደርጉ መረጃዎች አመልክተዋል። በተጫዋችነት ዘመኑ ለተደጋጋሚ ጉዳት ተጋላጭ የነበረው ፍላሚኒ ይህ ድርጅት ተጨዋቾች የሚደርስባቸውን አካላዊ ጉዳት እንደሚቀንስላቸውም ተናግሯል።

ኦሎምፒክ ማርሴ እና አርሴናል በልቤ ውስጥ የነገሡ ክለቦች ናቸው የሚለው ፈረንሳያዊው ቢሊዬነር ወደፊት እነዚህን ክለቦች የመግዛት ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል። አሁን ላይ የፍላሚኒ ሀብት ከሮናልዶ በ40 እጥፍ እንደሚበልጥ መረጃዎች አመልክተዋል።

ፍላሚኒ በእግር ኳስ ህይወቱ ትልቁ ሳምንታዊ ደሞዙ 140 ሺህ ፓውንድ በኤስሚላን ይከፈለው የነበረው ነው። በእግር ኳስ ሙያው እና ከማስታወቂያ  ይከፈለው የነበረውን ገንዘብ በማጠራቀም ነው በ17 ሚሊዮን ዩሮ ገንዘብ ግዙፉን የጂኤፍ ባዮኬሚካል ኩባንያ ማቋቋም የቻለው። ይህ ሥራም አሁን ቢሊየነር አድርጎታል። በዓለማችን በንግድ ሥራ ስኬታማ ከሆኑ ስፖርተኞች መካከልም ቀዳሚውን ስፍራ መያዝ ችሏል። አሁን ላይ ድርጅቱ በየዓመቱ ትልቅ እድገት እያሳየ ነው። የገጠመውን የቴክኖሎጂ ችግር በመቅረፍ ወደ ግዙፍ ኩባንያ ተሸጋግሯል።

በአውሮፓ ሀገራት በሚገኙ በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የባዮ ኢኮኖሚ ትምህርት በሁለተኛ  ዲግሪ ደረጃ እንዲሰጥ ማድረግ ችሏል፤ የኩባንያው መቋቋም። ሰነ ምህዳርን ለመጠበቅም ባዮ ጆርናል የተባለ መጽሔት እያዘጋጀም ያሰራጫል። ፍላሚኒ ደግሞ በግሉ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የሚያስችሉ እና የሚያነቃቁ የተለያዩ መልዕክቶችን እና ምስሎችን በማህበራዊ የትስስር ገጹ ያጋራል።

እ.አ.አ 2002 ጆቫኒ ዶ ሳንቶስ ራሚሬዝ የአትላንቲክ ውቅያኖስን አቆራርጦ ከሜክሲኮ አውሮፓ ምድር የደረሰበት ወቅት ነው። ታዳጊው ጆቫኒ አውሮፓ ምድርን እንደረገጠ የታላላቆች መፈልፈያ የሆነውን ላሜሲያ አካዳሚን ተቀላቀለ። በላሜሲያ አካዳሚ  ውሎ ያደረውን  ታዳጊ የተመለከቱ የባርሴሎና ወዳጆች ሁሉ የሊዮኔል ሜሲ እና የሮናልዲንሆ ተተኪ ነው እያሉ ማሞገስ ጀመሩ፡፡

በእርግጥም ታዳጊው ፈጣን፣ ሁለገብ እና የላቀ ክህሎት ያለው  አጥቂ ነበር። በግብ ጠባቂዎች እና በተከላካዮች የሚፈራ፤ ለቡድን ጓደኞቹ ያልተዛነፉ ኳሶችን የሚያቀብል አስደናቂ ተጨዋች ነበርም ይሉታል። ይሁን እንጂ ካታሎናውያንን ያስጨበጨበ ክህሎት እና ተሰጥኦ ቢኖረውም በኑካምፕ ከአንድ ዓመት በላይ አልቆየም። ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማቅናት ቶትንሀም ሆትስፐርስን ተቀላቅሏል።

ባለተሰጥኦው ሁለገብ አጥቂ በሰሜን ለንደኑ ክለብ ግን አቅሙን አውጥቶ መጠቀም አልቻለም። የመጪው ዘመን ኮከብ ይሆናል ብሎ ዓለም  የጠበቀው ጆቫኒ ሳንቶስ በእግር ኳሱ ሳይሳካለት ቀርቷል። በስፔን፣ በእንግሊዝ፣ አሜሪካ  እና ቱርክ ሊግ  ተዘዋውሮ ሲጫወት ያገኘውን ገንዘብ በማጠራቀም ወደ ንግዱ ዓለም ገብቷል። በሀገሩ ሜክሲኮ በፔትሮሊየም ንግድ ላይ በመሰማራት እየሠራ ይገኛል።

የ35 ዓመቱ የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋች በዚህ የንግድ ሥራ በዓመት የተጣራ ከ400 እስከ 500 ሺህ ዶላር ትርፍ እንደሚያገኝ የቢን ስፖርት መረጃ ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪም በመኪና ሽያጭ ላይ መሰማራቱም ተገልጿል። ቅንጡ መኪኖችን በመግዛት እና በመሸጥ የተሳካለት የንግድ ሰው መሆኑም ተጠቅሷል። እንደ ነበረው ተሰጥኦ በእግር ኳሱ ስኬታማ መሆን ያልቻለው ጆቫኒ አሁን በንግዱ ስኬታማ ከሚባሉ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋቾች ተርታ ስሙ ይጠራል።

በሀገራችንም በተለይ በአትሌቲክሱ ዘርፍ የምናውቃቸው የቀድሞ ስፖርተኞች ንግድ ውስጥ ገብተው ለሀገራችን ኢኮኖሚ እድገት የድርሻቸውን እየተወጡ ነው። ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ገዛህኝ አበራ እና የመሳሰሉት ኢንቨስትመንት ውስጥ ከተሰማሩት የሚጠቀሱ ናቸው። በእግር ኳስ እና በሌሎች ስፖርቶች የሚገኙ የቀድሞ ስፖርተኞች ግን በጡረታ ሲገለሉ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ከስፖርቱ ሲወጡ ከጥቂቶች በስተቀር በእንደዚህ  ዓይነት ሥራ ሲሰማሩ አይስተዋልምና በስፖርት ሙያቸው ካልተሰማሩ ይህ መንገድ መለመድ አለበት የሚል እምነት አለን።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here