ባህል ስፖርት ወይስ ፌስቲቫል?

0
405

21ኛው የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ውድድር እና 17ኛው የባህል ፌስቲቫል  በቅርቡ ተደርጎ መጠናቀቁ የሚታወስ ነው። በዚህ ውድድር 12 ክልሎች እና ሁለት ከተማ አሥተዳደሮች በ11 የስፖርት አይነቶች ውድድራቸውን አከናውነዋል። የአማራ ክልል የባህል ስፖርት ቡድን የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል። በተጨማሪም አማራ ክልል በውድድሩ  ባሳየው ስፖርታዊ ጨዋነት የዋንጫ ተሸላሚም መሆኑ አይዘነጋም።

ባሕላዊ ስፖርት የአንድን አካባቢ ባህል እና ትውፊት ወደ ሌላው አካባቢ ለማወራረስ እና ያልተበረዘውን የኢትዮጵያውያንን ማንነት ለማንጸባረቅ ያግዛል። የባህል ስፖርት ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው እና በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሀገራችን ይዘወተር እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ።

በአጠቃላይ 294 የባህል ስፖርት ዓይነቶች እንዳሉ መረጃዎች አመልክተዋል። ከእነዚህ የባህል ስፖርቶች መካከል 13ቱ ሕግ እና ደንብ ወጥቶላቸው በአገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ ውድድር የሚካሄድባቸው ናቸው።

እስከ 1997 ዓ.ም ሕግ እና ደንብ ወጥቶላቸው ይካሄዱ የነበሩ ስፖርቶች በቁጥር ሰባት እንደነበሩ አይዘነጋም። ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወዲህ ግን ተጨማሪ ስድስት የባህል ስፖርቶች ሕግ እና ደንብ ወጥቶላቸው ለውድድር በቅተዋል።  ገና ጨዋታ፣ ፈረስ ጉግስ፣ ቀስት ኢላማ፣ ገበጣ፣ ኩርቦ፣ ቡብ እና ሻህ በሀገራችን ውድድር ከሚደረግባቸው ባህላዊ ስፖርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

ባህላዊ ስፖርቶቻችን ለዘመናዊ ስፖርቶች መነሻ እንደሆኑ ይነገራል። ለአብነት በሀገራችን በተለይም በገና ሰሞን የሚዘወተረው የገና ስፖርት፣ ካናዳውያን በዘመናዊ መንገድ በማሻሻል የበረዶ ሆኪ በሚል ስያሜ እ.አ.አ በ1875 ገደማ በሀገራቸዉ አስተዋውቀውታል። የበረዶ ሆኪ ስፖርት ከገና ስፖርት ጋር ተመሳሳይ ነው።

ከሃያኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በካናዳ ክለብ ተቋቁሞ የሊግ ጨዋታዎች መደረግ ጀምረዋል። ከዛ በኋላም በእንግሊዝ፣ በአየርላንድ እና በሌሎችም የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ሀገራት ስፖርቱ  ተስፋፍቷል። እ.አ.አ ከ1920 ጀምሮ ስፖርቱ በኦሎምፒክ ተካቶ እየተካሄደ ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ በፓራለምፒክም ውድድር በመካተቱ ተወዳጅ ስፖርት ለመሆን በቅቷል።

የማንነታችን መገለጫዋች የሆኑት ገና እና የመሳሰሉት   ባህላዊ ስፖርቶቻችን ግን ባሉበት መሻሻል ሳይታይባቸው ዘመናትን ተሻግረዋል፣ እየተሻገሩም ናቸው።  በ1990 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ ዜጎች በባህላዊ ስፖርት መሳተፍ እንዳለባቸው የተቀመጠ ሕግ ቢኖርም ዘርፉ ከመንግሥት እየተደረገለት ያለው ድጋፍ ግን በቂ እንዳልሆነ ይነገራል። በተለይ ደግሞ በሀገራችን የገጠሩ ማኅበረሰብ ክፍል የባህላዊ ስፖርት ዋናው ባለቤት ቢሆንም በስፖርቱ ግን ተጠቃሚ አይደለም ማለት ይቻላል።

ለአብነት የአማራ ክልል ስፖርት ምክር ቤት ጉባኤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሲያከናውን ለመታዘብ እንደሞከርነው በክልሉ በየዓመቱ  የስፖርት ሀብት ሲሰበሰብ ከአርሶ አደሩም ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚሰበሰብ በጉባኤው ሲነገር አድምጠናል። ታዲያ ለስፖርቱ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው ማኅበረሰብ ግን መዘንጋቱም በተደጋጋሚ ተነግሯል።

የአሚኮ በኩር ስፖርት  ዝግጅት ክፍል በባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ አካዳሚ፣ የስፖርት ሳይንስ መምህር ከሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር በእውቀቱ ቸኮል ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ቆይታ አድርጓል።

ለባህል ስፖርቶች የሚሰጠው ዝቅተኛ አመለካከት እና ግንዛቤ ለስፖርቱ እድገት አንደኛው መሰናክል መሆኑን የስፖርት ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር በእውቀቱ  ያስረዳሉ። ማኅብረሰቡ የባህል ስፖርቶች ላይ ያለው የባለቤትነት ስሜት ዝቅተኛ መሆን ስፖርቱ ለውጥ እንዳያመጣ እና አሉታዊ ተጽእኖ ስር እንዲወድቅ ሆኗልም  ይላሉ።

እንዲሁም ማኅበረሰቡ በዘመናዊ ስፖርቶች እሳቤ ቅኝ የተገዛ በመሆኑ የራሱን መገለጫ የሆኑትን ስፖርቶች በመጥላት እና በመሸሽ ዘመናዊ  ስፖርቶች ጋር እንዲጣበቅ ሆኗል። ይህ የሆነው ደግሞ በባህላዊ ስፖርቶች ውስጥ የሚገኙት አመራሮች፣ ዳኞች፣ መምህራን እና በአጠቃላይ የባህላዊ ስፖርት ባለሙያዎች የቁርጠኝነት እና የግንዛቤ እጥረት ስላለባቸው ነው ብለዋል።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር እና ሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በቅርበት እና በጋራ ተቀናጅተው አለመሥራታቸው፣ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ስለ ዘርፉ በቂ ግንዛቤ እንዳይኖረው አድርጓል። ስፖርቱን የሚመራው አካል ለዳኞች፣ ለአሰልጣኞች እና ለባለሙያዎች ተገቢ የሆነ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠናዎች አለመኖራቸውም ስፖርቱን ወደ ኋላ አስቀርቶታል።

እንደ ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር በእውቀቱ ማብራሪያ ቋሚ የሆነ የውድድር ሥርዓት አለመኖርም ስፖርቱ ለውጥ እንዳያሳይ ሌላኛው ምክንያት ተደርጎ ይነሳል ይላሉ። በሀገራችን የሚደረግ የሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና ፌስቲቫል በየዓመቱ እንደሚከናወን ይታወቃል። ይህ የባህል ስፖርት ውድድር እና ፌስቲቫል ምንም እንኳ የውድድር መድረክ እንደሆነ ቢታወቅም በድፍረት  አዎ ነው! ለማለት ግን አያስደፍርም። ሚዛኑ ወደ ፌስቲቫልነት ያጋድላል ማለት ይቻላል።

በሀገር ውስጥ በመላው ጨዋታዎች እና በትምህርት ቤቶች ውድድር ላይ ባህላዊ ስፖርቶችን በማካተት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠይቃል። በሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ እና የውድድር ሥርዓት (Format) ተዘጋጅቶለት ሊሠራ እንደሚገባም ነው የስፖርት መምህሩ የሚናገሩት። በሀገር ውስጥ የሊግ ወይም መሰል መደበኛ የባህል ስፖርት ውድድሮች እንዲጀመሩ በቂ የሆነ ተሳታፊ ሊኖር ግድ ይላል እና ይህም ሊታሰብበት ይገባል።

የባህል ስፖርቶችን ለማሳደግ ከታች በታዳጊዎች ላይ በመሥራት  በሁለቱም ጾታዎች ተተኪዎችን ማፍራት ስፖርቱን ለማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ። ኢትዮጵያ በዓለም እና በአህጉር አቀፍ ደረጃ ከዚህ በፊት የባህል ስፖርቶችን ያስተዋወቀችበት ጊዜ እንደነበረ ታሪክ ያወሳል። ታዲያ አሁን ላይ ይህን ለማድረግ ግን መጀመሪያ ስፖርቱን ማስፋፋት ይጠይቃል ይላሉ ባለሙያው።

“በሀገር ውስጥ ስፖርቱ ከተስፋፋ እና ከተለመደ በኋላ ከሀገር ውጪ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ለትምህርት፣ ለሥራ እና ለጉብኝት በሚሄዱ የሀገራችን ዜጎች በሚሄዱበት ሀገር ስፖርቱን እንዲያስተዋውቁ ማድረግ ይቻላል” ብለዋል። ይህን ለማድረግ ግን ለባህል ስፖርቶች የተሰጠው አመለካከት እንዲቀየር የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች መሠራት አለባቸው።

ለስፖርቱ የሚሆኑ መሰረተ ልማቶችም መሟላት አለባቸው። የማዘውተሪያ ሥፍራ እና የስፖርት ቁሳቁስ መሟላት ይኖርባቸዋል። ለአብነት በሀገራችን የገና ስፖርት የራሱ የሆነ የማዘውተሪያ ሥፍራ ስለሌለው  ውድድር የሚከናወነው በእግር ኳስ ሜዳዎች መሆኑ ይታወቃል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በዘርፉ ጥናት እና ምርምር በማድረግ ለስፖርቱ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል። ሕግ እና ደንቦችን በማርቀቅ እና በማዘጋጀት እንዲሁም በማስተዋወቅ  ስፖርቱን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በዘመናዊ ስፖርቶች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ የሚያደርጉ ባለ ሀብቶች ለባህል ስፖርቶች እድገትም የድርሻቸውን ቢወጡ ስፖርቱን ማሳደግ ይቻላል የባለሙያው አስተያየት ነው።

የባህል ስፖርቶች በማኅበረሰባችን ላይ የሚፈጥሩት በጎ ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ ዘርፉን ሕዝባዊ መሰርት ማስያዝም ይገባል። በየዓመቱ ለስፖርቱ የሚበጀተው በጀት አነስተኛ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቅሬታዎች ይነሳሉ። ታዲያ ስፖርቱ ለውጥ እንዲያሳይ ከተፈለገ በጀቱ መስተካከል እንዳለበትም ተጠቁሟል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here