ባለ ልጓም ስሜት

0
56

ብሩስ ሊ አንድ ጥሩ አባባል አለው፤ “ስሜት ጠላት ሊሆን ይችላል፣ ለስሜትህ ከተሸነፍህ፣ ራስህን ታጣለህ። ከስሜትህ ጋር አንድ መሆን አለብህ፤ ምክንያቱም አካል ሁልጊዜ አዕምሮን ይከተላል” ይላል።

ስሜት ብልሃትን የሚጠይቅ መሆኑ በተደጋጋሚ የተነገረለት ጉዳይ ነው። የደስታም ይሁኑ የኀዘን ስሜቶች በአግባቡ ካልተያዙ ውጤታቸው አጥፊ ነው። “ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ” የሚለው አባባል በደስታ ጊዜ የሚፈጠር የፈንጠዝያ ስሜት ካልገሩት ገደል መሆኑን የሚያመለክት ነው። የራበው ሰው አርፎ ይቀመጣል። ስሜቱ ዝቅተኛ ነው። የጠገበ ሁሉን የሚያደርግ መስሎት ከፍተኛ መነቃቃት ውስጥ ገብቶ ሊሰበር ይችላል:: “ጥጋብ ወደ ርሀብ ይነዳል” የሚባለውም ከዚህ የተነሳ ነው።

የኀዘንም ስሜት ቢሆን ቀለል ካላደረጉት ተጨማሪ ኀዘንን ይወልዳል። አንዲት ክስተት ተፈጥራ አዕምሯችንን ትቆጣጠረዋለች። ስሜት ቁጥጥር እና እንክብካቤ የሚፈልግ ነገር ነው። ብዙ ጊዜ ስጋዊ ስሜት ሰዎችን የማይመልሱት ችግር ውስጥ ይከታል።

ሰው በቦታ፣በጊዜ እና በሁኔታዎች ስሜቱ የሚለዋወጥ ፍጡር ነው። የስሜት መለዋወጥ ይፈራረቅበታል። ስለዚህም ስሜቱን በብልህነት መምራቱ ከስህተት ያድነዋል፤ ከሚፈልግበት ቦታ እንዲደርስ ያስችለዋል፤ በመንገዱ እንዳይሰናከል ያግዘዋል፤ ጠላቶች ወይም ተፎካካሪዎቹ ጥቃት እንዳይከፍቱበት እና የሴራ ሰለባ እንዳይሆን ይረዳዋል።

ስሜታችን ብዙ ጊዜ ይሸውደናል። በጣም ስንደሰት ወይም በጣም ስንከፋ የምንወስናቸው ነገሮች ከስሜቱ ስንወጣ የሚያስቆጩን ይሆናሉ። ለዚህ ነው በስሜት የተዋከቡ ውሳኔዎች ማለቂያቸው የማያምረው። በረድ፣ ቀዝቀዝ ማለት የሚጠቅመው ለዚህ ነው። ስሜታዊ ስንሆን ሁሉ ትክክል ይመስለናል። ከስሜቱ ስንወጣ ሁሉም ነገር ትክክል እንዳልነበር ይገባናል:: የወጣትነት ውሳኔ በጉርምስና ትክክል ሆኖ አይታይም።

ስሜታችንን ማመን የማይገባው ለዚህ ነው። አሳስቆ ወስዶ ኀዘን እና ጸጸት ውስጥ ይዘፍቀናል። ስሜታችንን ስንጠቀምበት ጥሩ ነው። እሱ ሲጠቀምብን ግን እቃ ያደርገናል። እኛ በልጓም ስንይዘው የት መድረስ እንዳለበት እንመራዋለን። እሱ ሲመራን ገደል ውስጥ ሊጨምረን ይችላል።

ማያ አንጀሎ “ሰዎች የተናገርኸውን እና ያደረግኸውን እንደሚረሱ ተምሬያለሁ። ነገር ግን ሰዎች ስሜትህን እና  እንዴት እንዳደረግህ መቼም አይረሱም” የሚል አባባል አላት።

ስሜታዊነት በየደቂቃው የሚገጥመን ክስተት ነው፤ የሚቀርም አይደለም። ለነገሮች የምንሰጠው ትርጉም ግን የሚፈጠርብንን ስሜት ይቀይረዋል። በጠዋቱ አሉታዊ መልዕክቶችን የሰማ ሰው ቀኑ በአሉታዊ ስሜት ተሞልቶ ይውላል። ከሰዎች ጋር የሚኖረው ግንኙነትም አሉታዊ ይሆናል። ሰዎች ፈገግ ብለው ሲያዩን ፊታችን ይበራል፤ ስሜታችን ይነቃቃል፤ ሲያለቅሱ እንከፋለን፤ አብረን እናለቅሳለን። ስሜት አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ  ተላላፊ ነው፤ የአንዱ በሌላው ይጋባል።

ሐሳባችን ከስሜታችን እና ከሕይወታችን ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ስሜትን ማስተዳደር ተገቢ የሚሆነው ለዚህ ነው። “ሀሳቦቻችሁን ተጠንቀቁ፤ ቃላት ይሆናሉ፤ ቃላታችሁን ተጠንቀቁ፤ ተግባር ይሆናሉ፤ ተግባሮቻችሁን ተጠንቀቁ፤ ልማድ ይሆናሉ። ልማዶቻችሁን ተጠንቀቁ፤ ባህሪ ይሆናሉ፤ ባህሪያችሁን ተጠንቀቁ፤ እጣ ፈንታችሁ ይሆናል” ሲል ፍራንክ አውትላው የተባለ ሥራ ፈጣሪ ሰው ተናግሯል።

ስሜቶች ኃይል አላቸው። እንደ ሰው ሁላችንም ስሜታዊ ፍጥረቶች ነን። ስሜቶቻችን የምንወስናቸውን ውሳኔዎች፣ የምንከተለውን የሕይወት ጎዳና፣ የምንደሰትባቸውን ፊልሞች እና ሙዚቃዎች፣ የምንወደውን ጥበብ ይወስናሉ።

ድባቴ ሲሰማን የሙዚቃ ምርጫችን ጨፍጋጋ ይሆናል። ስንደሰት እንዲሁ አዎንታዊነት ያላቸው ዘፈኖችን እንመርጣለን። የምንሰማው ዜና እና ወሬያችንም አዎንታዊ ይሆናል። ያንንም በዙሪያችን ባሉ ሰዎች እናስተጋባለን። ፍራንክ አውትላው ተጠንቀቁ የሚለን ለዚህ ነው፤ ስሜት ተላላፊ ነው::

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ማሪያ ማኔስ በቴድ ኤክስ መድረክ ላይ ቀርባ ንግግር ስታደርግ “ብልህ ሕዝብ ምልክቱ ስሜቱን በምክንያታዊነት የመቆጣጠር ችሎታው ነው” ብላለች::

ስሜታዊ ብልህነት የግል እና የሌሎች ሰዎችን ስሜቶች በብቃት መቆጣጠር እና መረዳትን ይጨምራል:: ስሜታዊ ብልህነት  ጭንቀትን ለማቃለል፣ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመግባባት፣ የሌሎችን ስሜት ለመረዳት፣ ፈተናዎችን ለማለፍ እና ግጭትን ለማርገብ የሚያግዝ ችሎታ ነው፤ ሕይወትን ለመምራት፣ ጠንካራ ግንኙነቶችን ለመገንባት እና ስኬትን ለማግኘት ወሳኝ የሆነ ክህሎት ነው። በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ብዙ ችግሮች በታጋሽነት፣ በማስተዋል እና በፈጠራ እንድንወጣ ትጥቅ ሆኖ ያገለግለናል።

ዳንኤል ጎልማን “ኢሞሽናል ኢንተለጀንስ” በሚለው መጽሐፉ ስሜትን በብልሀት ስለ ማስተዳደር ሀሳቦችን አንስቷል:: “የስሜት ብልህነት የተፈጥሮ ችሎታ ሳይሆን በትምህርት የሚገኝ ነው” ይላል ጎልማን:: ይህም ሲባል ትምህርት ስሜቶቻችን ከየት እንደሚመጡ፣ የልጅነት ጊዜያችን እንዴት እንደሚቀርጸን እና ፍርሃቶቻችንን እንዲሁም ምኞቶቻችንን እንዴት ማስተናገድ እንደምንችል ስለሚያስገነዝበን ነው።

“በአሁኑ ጊዜ ዓለም ከፍተኛ ቴክኒካዊ እድገት ቢያሳይም፣ የስሜት ብልህነት ትምህርትን ችላ ማለታችን፣ አዲስ አደጋዎችን ሊያስከትል ይችላል” ሲል ስጋቱን ይናገራል::

ዳንኤል ጎልማን አራት ቁልፍ  ነጥቦችን በማንሳት ስሜታዊ ብልህነትን ያብራራል:: የመጀመሪያው ራስን ማወቅ ነው፤ ቀጥሎ ራስን ማስተዳደር ነው፤ መተሳሰብ እና ማህበራዊ ክህሎቶች ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃዎች ናቸው::

ራስን ማወቅ የግላችንን ስሜት እና ምክንያቶቻቸውን መረዳት ነው:: ይህም ጥሩ ግንዛቤ እና ውሳኔ የማድረግ መሠረት ነው፤ የሞራል መመሪያ ሆኖም ያገለግላል።

ራስን ማስተዳደር የሚያበሳጩ ስሜቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መቆጣጠርን ያካትታል:: እንዳያደክሙን ለመከላከል እና አዎንታዊ ስሜቶችን በማሰባሰብ ተግባራትን ከፍላጎቶች ጋር ማጣጣምንም ይጨምራል::

መተሳሰብ የሌላ ሰውን ስሜት የመረዳት ችሎታ ነው::  ሌላ ሰው ሲከፋው፣ ሲደሰት፣ ስሜቱ  ሲለወጥ  በርህራሄ  ስሜት  ማየት  ነው:: ጎልማን ማህበራዊ ክህሎቶች የሚላቸው ደግሞ እነዚህን ሁሉ ቀሪዎቹን ሦስት ደረጃዎች በሰለጠነ ግንኙነት ውስጥ በማቀናጀት ከሰዎች ጋር  መልካም  ግንኙነት  መፍጠር መቻልን ነው::

የሳቲያ ናዴላ የስሜት ብልህነት ማይክሮሶፍትን እንዴት እንዳነቃቃው ቀጥሎ እንመልከት:: እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2014  ሳቲያ  ናዴላ የማይክሮሶፍት  ሦስተኛ ዋና  ሥራ  አስፈፃሚ  ሆኖ የ ተሾመበት ጊዜ ነበር:: በወቅቱ ኩባንያው በጠንካራ፣ በውድድር እና በተናጠል የሥራ ባህል የሚታወቅ ነበር። ይህ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ በፍጥነት በሚለዋወጠው የኢንዱስትሪው ዓለም አብሮ ለመራመድ እየታገለ ነበር። በዚህ ያልተደሰተው ሳቲያ ናዴላ የማይክሮሶፍት የኩባንያውን መሰረታዊ ባህሪ የቀየረ አስደናቂ ለውጥ  ማሰብ ጀመረ:: ናዴላ በጥልቅ ስሜት ብልህነት ተጉዞ በኩባንያው ውስጥ “አዳጊ እሳቤን” ማራመድ ጀመረ:: ሁሉን አዋቂ ከመሆን ይልቅ በመማር እና በመላመድ ላይ አተኮረ። የቀድሞውን የውድድር ባህል በቀጥታ የተገዳደረ ልምምድ ገነባ:: ሠራተኞች ሳይሳካላቸው ቢቀሩ እንኳ ሳይፈሩ አዳዲስ ፈጠራዎችን እንዲያቀርቡ አበረታቷቸዋል።

የናዴላ የአመራር ዘይቤ በስሜት ብልህነት መሠረት በሆነው በርህራሄ ላይ የተመሠረተ ነው። ርህራሄ የደንበኞችን ያልተሟሉ እና ያልተገለፁ ፍላጎቶችን ለመረዳት ስለሚያስችል ለፈጠራ ወሳኝ ነው ብሎ ያምናል። ይህ የርህራሄ ትኩረት ለሠራተኞቹም ጭምር ጠቅሟል። ከዚህ ቀደም የተለያዩ ክፍሎችን እርስ በርስ የሚያጋጩትን የውስጥ ግድግዳዎች በማፍረስ የበለጠ የትብብር መንፈስ ያለበት የሥራ አካባቢ መፍጠር ቻለ:: ቀደም ሲል ተቀናቃኞች የነበሩ ቡድኖች ዕውቀታቸውን እና ሀብታቸውን ማጋራት ጀመሩ፤ ይህም ይበልጥ የተቀናጁ እና ስኬታማ ምርቶችን ለማምረት አስችሏል::

ናዴላ ለስሜታዊ ብልህነት ቅድሚያ በመስጠት ማይክሮሶፍትን ከውድቀት ማዳን ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ውድ ኩባንያዎች አንዱ እንዲሆን አድርጎታል። የናዴላ አመራር የስሜት ብልህነት ወሳኝ የመሪነት ጥበብ መሆኑንም ያሳየ ነው። የራሱን ስሜት የመረዳት እና የመቆጣጠር፣ ለሌሎች የመራራት፣ እንዲሁም የመተማመን እና የትብብር ባህል የመገንባት ችሎታውን አዳብሯል:: አንድ የስሜት ብልህነት ያለው ሰው እንዴት ትልቅ ተጽዕኖ መፍጠር እንደሚችል የሚያሳይ ተጠቃሽ ምሳሌ ሆኖ ሲጠቀስ ይኖራል::

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here