አንድ ሰው ሆኖ ሳለ እንደወጣ መቅረቱ ከአራት አስርት አመታትም በኋላ ዛሬም የገነገነና ትኩስ ወሬ ይመስል በድምቀት ይወራለታል። የሀገር መሪዎች፣ የደህንነት ሹማምንት፣ ባለስልጣናት፣ ምክትል ፕሬዝደንቶች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጭምር ስለጉዳዩ ከጋዜጠኛ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ ተጠየቅ ተብለውበታል። በመጽሐፋቸው ጽፈውለታል። ደራሲያን አብነት አድርገው ይጠቅሱታል፤ ተርከውታል፤ ተወያይተውታል። “በህይወት አለ ወይስ የለም? ካለስ የት አለ? ከሞተስ መች? የት? እና እንዴት ሞተ?” የሚለውን ጉዳይ ዛሬም ወጥረዉ የሚከራከሩበት እልፎች ናቸው:: ይሄን ሁላ ዋጋ ለመውሰድ በዓሉ ግርማን መሆን ይጠይቃል:: በእርግጥም በዓሉ በክፍለ ዘመናችን ተንቦግቡገዉ ከበሩ ጮራቸዉ ፈንጥቆ ወዲያው ከጠፉ ስመጥር ጸሐፍት እና ጋዜጠኞች መካከል ምናልባት ግንባር ቀደሙ ሳይሆን አይቀርም።
በዓሉ ግርማ በወርሀ መስከረም በ1929 ዓመተ ምህረት በኢሉባቡር ከተማ (አሁን ኢሉ አባቦራ) ሱጴ ተብላ በምትጠራ ገጠር ተወለደ። በዓሉ በአባቱ ህንዳዊ ሲሆን በእናቱ ኢትዮጵያዊ ነው:: የበዓሉ እውነተኛ አባት ስም ግርማ ሳይሆን ጂምናዳስ ይባላል:: ሞልቬር ‘ብላክ ላየንስ’ በሚለው መጽሐፉ ግርማ የእንጀራ አባቱ እንደሆነ ሲገልጽ እንዳለጌታ ደግሞ ‘በዓሉ ግርማ ሕይወቱ እና ሥራዎቹ’ በሚለዉ መጽሐፉ ግርማ አባቱ ሳይሆን በዓሉ ከሱጴ ተነስቶ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ተቀብሎ ያሳደገው ነው ይላል::
ጂምናዳስ፣ የተወለደው ህንድ ውስጥ ጉጅራት በተባለ ከተማ ነው:: በዚያ ከተማ ውስጥ ዝርያችን ከኢትዮጵያ ይመዘዛል የሚሉና ራሳቸውን “ሀቢሲስ” ወይም “ሲዲስ” ብለው የሚጠሩ ሰዎች አሉ:: ሀቢሲስ ማለት ከሃበሻ ሀገር የመጣ ህዝብ ማለት ሲሆን ሲዲስ የሚለው ደግሞ ስድስተኞቹ የኢትዮጵያ ትውልዶች ማለት ነው::
የበዓሉ እናት ያደኔ ቲባ የምትባል የሱጴ ቦሩ ተወላጅ ናት:: በጊዜው አባቷ በሚነግዳቸዉ ንግዶች ስር ትሠራ የነበረ ሲሆን ጂምናዳስ ደጋግሞ በቀየዉ ሲያመራ በውበቷ ተማርኮ በወጉ መሠረት ሽማግሌ ልኮ ነበር የተጋቡት:: ጂምናዳስ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረ ጊዜ ከአዲስ አበባ ኢሉባቡር እየተመላለሰ ሸቀጣ ሸቀጥ ይነግድ ነበር::
ህንዳዊ አባቱ ለልጁ ያወጣው ስም “ባሉ” የሚል ሲሆን ትርጓሜውም ከህንድ ቋንቋዎች ባንዱ “እድለኛ” ማለት ነው:: ሰዎች ስያሜዉ አዲስ ስለሆነባቸዉ ለአጠራር እንዲቀላቸዉ በዓሉ እያሉ ይጠሩት ጀመር:: ስሙም በዛው ቀጥሎ መደበኛ መጠሪያው ሆነ:: የሚጠራው በወላጅ አባቱ ሳይሆን በአሳዳጊው ስም ነው::
ያደኔ ቲባ እና ጂምናዳስ በዓሉን ብቻ አይደለም የወለዱት:: ከበዓሉ ቀጥሎ ሶሎሞን የሚባል ልጅም ወልደው ነበር:: ነገር ግን ሶሎሞን ሁለት ዓመት ከመንፈቅ እንደሆነዉ በተነሳው ፈንጣጣ በሽታ ህይወቱ አልፏል::
በዓሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በኢሉባቦር፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተከታትሏል:: ከዛም በመቀጠል ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪዉን ከያዘ በኋላ ወደ አሜሪካ በመሄድ ሁለተኛ ዲግሪዉን አግኝቷል::
በዓሉ ትምህርቱን እንደጨረሰ፣ ሥራ የጀመረዉ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ነበር:: በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ሳለም ዜና ያነብ ጋዜጣም ያዘጋጅ ነበር:: የ’መነን’ና ‘አዲስ ሪፖርተር’ መጽሔቶች የ’አዲስ ዘመን’ና ‘ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ’ አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል:: በእነዚህ ጋዜጦች ላይ ከፍ ያለ ለውጥ እንዳመጣም ይነገርለታል::
በዓሉ በጋዜጦቹ ከመንግሥት አቋም ውጪ የሆኑ ጽሑፎችን ወይም የዘውድ ስርዓቱን እና የመንግሥት ባለስልጣኖችን የሚተቹ ጽሑፎችን ያስተናግድ ነበር። በእነዚህም የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከ መሰጠት እና ከሥራ እስከ መታገድ ደረጃ ደርሷል:: በግሉም ሌሎች ማለትም እንደ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር እና ሰለሞን ደሬሳ አይነት ተጋባዥ ጸሐፊዎችን እያስተባበረ የግል ጋዜጦችን እና መጽሔቶችን ለማቋቋም ቢፈልግም በመንግሥት ይታገድበት ነበር::
ከዚህ ባሻገርም፣ ከአብዮቱ በኋላ የዜና አገልግሎት ኃላፊ፣ በኋላም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በመሆን አገልግሏል። ከአብዮቱ በኋላ በዓሉ ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር ጥብቅ ግንኙነት መስርቶ እንደነበር ይነገራል:: ራሳቸው ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም ለገነት አየለ እንደነገሯት ከሆነ የበዓሉ ግርማ እና የመንግሥቱ ትውውቅ ሰባ ደረጃ አካባቢ በሚገኝ አንድ ባር ውስጥ ነው:: በዓሉ እዚያ ባር ውስጥ ወዳጁ ከነበረችው ድምጻዊት ብዙነሽ በቀለ ጋር ይመላለስም ነበር::
በዓሉ ከመንግስቱ ጋር በነበረው ጥብቅ ግንኙነት የኤርትራው የቀይ ኮከብ ዘመቻ አጋዥ እስከመሆን ደርሶም ነበር:: ከዚህ ዘመቻ በፊት የእሱ “የቀይ ከከብ ጥሪ” መጽሐፍ ወጥቶ ስለነበር የዘመቻው ጥሪም ከዚህ መጽሐፍ ርዕስ እንደተቀዳ ይነገራል:: በዚህ ዘመቻም ሊቀ መንበሩ በዓሉን ወደ ዘመቻው ይዘውት ሄደው ነበር:: የመጨረሻ የሆነው ‘ኦሮማይ’ የተሰኘውን ልቦለዱን የጻፈው ያንን በ1974 ዓ.ም ኤርትራ ክፍለ ሀገር የተካሄደውን ዘመቻ መሠረት አድርጎ ነው::
በዓሉ ቆንጆ ሴት አይቶ አድናቆቱን ሳይገልፅ የማያልፍ ነበር:: ከተወዳጇ ድምጻዊት ከብዙነሽ በቀለ ጋርም ፍቅር ውስጥ ገብተው እንደነበርም ይነገራል:: ሆኖም ብዙነሽ በቀለና በዓሉ ግርማ በግልፅ ባልታወቀ ምክንያት ተለያዩ:: ከብዙነሽ የተለያየው በዓሉ ብዙም ሳቆይ አሜሪካ ሄዶ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን ሲጨርስ አልማዝ ከምትባል የካዛንቺስ አካባቢ ልጅ ተወዳጀ:: አልማዝ ቆንጆ እና ዳንስ የምትወድ ሴት ነበረች:: በዓሉ በትዳራቸው ውስጥም ይሄ የሴት ሙያ ነው:: ይሄ የወንድ የሚለው ሥራ አልነበረውም:: ሲያሻዉ ወደ ማእድ ቤት ገብቶ ምግብ ያበስልም ነበር:: ከአልማዝ ጋር ተጋብቶ ሦስት ልጆችንም ወልዷል:: ከሦስቱ ውስጥ ሁለቱ ወንዶች ሲሆኑ ዘላለም በዓሉ እና ቢኒያም በዓሉ ይባላሉ:: ሴቷ መስከረም በዓሉ ትባላለች::
ስለ በዓሉ ግርማ በሀገራችን አያሌ ጸሐፍያን በጋዜጣም በመጽሔትም ብዙ ብለዋል:: በራዲዮና በቴሌቪዥን ያልተነሳበት ዓመትና ወርም የለም (ማለት ይቻላል):: የደራሲያንን ታሪክ የያዙ መጽሐፍት በዓሉን በቀጥታም በተዘዋዋሪም አያልፉትም:: የደርግ ባለስልጣኖች በተለያየ ስፍራ ሆነው በሚጽፉት መጽሐፍም በዓሉን ያነሳሱታል:: እንዳለጌታ ከበደ ግን በ2008 ዓመተ ምህረት ያሳተመው “በዓሉ ግርማ ህይወቱና ሥራዎቹ” የሚለው ባለ 440 ገፅ መጽሐፍ ከሁሉም የተለየና የደራሲውን ህይወትና ሥራዎች” በዝርዝር የተመለከተ ነው:: በዚህም መጽሐፉን “ሃውልት ላልቆመለት ደራሲ የቆመ የመጽሐፍ ሃውልት” የሚሉት ብዙዎች ናቸው::
በዓሉ ግርማ ለብዙዎች መነቃቃትን የፈጠረ በሳል፣ ደፋር እና ንቁ ጋዜጠኛ እና ብዕረኛ ነበር:: በዓሉ በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ውስጥ የራሱን አሻራ ያሳረፈ፣ በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ በሀገራችን የድርሰትና የሚድያ ሥራ ውስጥ የጎላ ድርሻ የነበረው ነው:: ከበዓሉ ግርማ ልቦለድ ድርሰቶች መካከል ኦሮማይ ፣ ከአድማስ ባሻገር፣ የህሊና ደወል የቀይ ኮከብ ጥሪ፣ ሐዲስ እና ደራሲው ይገኙበታል::
ዛሬም ግን በዓሉ ግርማ በማን ተገደለ? ለሚለው መልስ የለም:: ገና የ47 ዓመት እድሜ ሳለ የተሰወረው በዓሉ በድርሰት ሥራዎቹ መላ ኢትዮጵያውያን ያነሱታል:: በአጫጭር አረፍተ-ነገሮቹ የስነ-ጽሑፍ ባለሙያዎች ስሙን ከፍ አድርገው ያነሱታል:: በዓሉ ግርማ በተለይ ‹‹ኦሮማይ›› በተሰኘ ድርሰቱ በመላ አንባቢያን ለመደነቅ የቻለ ነው::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም